BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Saturday, 15 February 2014

ኢትዮቴሌኮም: “የምትታለብ ላም”

– አብርሃ ደስታ

7c196-1001168_485348238212789_1719160956_nአዎ! የኢህአዴግ መንግስት የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት በMonopoly መቆጣጠሩ ይታወቃል። ለዚህም ምክንያት አለው። በህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍልስፍና መሰረት ስልጣን የሁሉም ነገር መሳርያ ነው። ስለዚህ ስልጣንን መቆጣጠር ግድ ነው። ስልጣን ለመቆጣጠር ደግሞ ኢኮኖሚውን መቆጣጠር ያስፈልጋል። ለዚህም ነው ስልጣን ለመቆጣጠር ሲሉ ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠሩት።
ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ትርፋማ የሆኑ ሴክተሮችና የኢኮኖሚን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ ተቋማት በmonopoly መያዝ ያስፈለገው። ትርፋማ ከሆኑ ሴክተሮች ኢትዮቴለኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርጅት ይገኙባቸዋል። የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ተቋም ደግሞ ባንክ ነው። ባንክ፣ ኢትዮቴሌኮምና አየር መንገድ በኢህአዴግ ቁጥጥር ስር ናቸው። ለምን? ምክንያቱም የኢኮኖሚ ምንጭ ናቸው።

ትርፋማ የኢኮኖሚ ሴክተሮች በመንግስት እጅ ሲወድቁ (በተለይ ደግሞ በሞኖፖሊ ሲሆን) ለሀገር ኢኮኖሚ ጎጂ ነው። ምክንያቱም (አንድ) የመንግስት ቢሮክራሲ የግሉን ዘርፍ ያህል efficient and effective ስላልሆነ የተፈለገውን ትርፍ ላይገኝ ይችላል። የመንግስትና የግል ዘርፎች በተመሳሳይ ፍጥነት አይጓዙም። ምክንያቱም የመንግስትና የግል ዘርፉ ዓላማዎች ይለያያሉ። (ሁለት) ሙሰኛ መንግስት የኢኮኖሚ ዘርፍን በሞኖፖል ሲቆጣጠር ኢኮኖሚውን ክፉኛ ይጎዳዋል። በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሙስና ካለ ኢኮኖሚው ይሽመደመዳል። ምክንያቱም በሞኖፖል ምክንያት የተሰበሰበው ትርፍ በሙስና ምክንያት የግል ባለስልጣናት ሲሳይ ሲሆን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ይጎዳል።
(ሦስት) የኢኮኖሚ ዘርፍን በሞኖፖል መያዝ በራሱ የኢኮኖሚ ዉድቀትን ያመጣል። ሞኖፖሊ ሕብረተሰብን (ተገልጋዮችን) በጣም ይጎዳል። ባለሞኖፖሊው ደግሞ ያከብራል። ምክንያቱም ሞኖፖሊ ካለ ዉድድር አይኖርም። ውድድር ከሌለ የአገልግሎት ጥራት ሊቀንስ በተቃራኒው ደግሞ የአገልግሎቱ ዋጋ ሊጨምር ይችላል። ተገልጋዩ ሌላ አማራጭ ስለሌለው የዘርፉ ባለቤት ባዘዘው ዋጋ ይሽምታል፤ የአገልግሎት ጥራቱ ቢቀንስም ሌላ የምሄድበት አማራጭ የለውም። የኢትዮቴሌኮም ጉዳይ የሚገለፀው በዚሁ መልክ ነው።
የኢትዮቴሌኮም አገልግሎት የወረደ ነው። አሁን አሁንማ አገልግሎት እየሰጠ አይደለም ማለት ይቻላል። ጥሩ አገልግሎት ባይሰጥም ግን ያው እኛ ተገልጋዮች ሌላ አማራጭ እስከሌለን ድረስ የኢትዮቴሌኮም ተጠቃሚዎች መሆናችን አይቀርም። ኢትዮቴሌኮም ጥራት ያለው አገልግሎት ሳይሰጠን ገንዘብ ግን ይበላል። እንደዉጤቱም ተገልጋዩ ደንበኛ ይጎዳል። ህዝቡ ጥሩ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለማግኘቱ የኢኮኖሚ እንስቅስቃሴው ይሽመደመዳል። ምክንያቱም ቢዝነስ ለመስራት የስልክ ኮሙኒኬሽን አስፈላጊ ነው። ማህበራዊ ህይወታችንም ይቆራረጣል። ባጠቃላይ የህዝብ ደህንነት ይጎዳል።
አማራጭ የቴሌኮሙኒካሽን አገልግሎት ሰጪ ተቋም ቢኖር ኑሮ ግን ይህን ያህል ባልተጎዳን ነበር። ምክንያቱም (አንድ) ኢትዮቴሌኮም ሲበላሽ ሌላ አማራጭ እንጠቀማለን። የኢኮኖሚና ማሕበራዊ አገልግሎቶች እናገኛለን። በዚህ መሰረት ኢኮኖሚያችን አይጎዳም፣ ማህበራዊ ህይወታችንም አይበጣጠስም። (ሁለት) ሌላ አማራጭ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ አካል ካለ ኢትዮቴሌኮም ከውድድር እንዳይወጣ በመስጋት ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠቱ አይቀርም (ጨው ለራስ ህ ስትል … ይሆናል)። በውድድር ምክንያት የቴሌ ዋጋም ይቀንሳል። ዉድድር ሲኖር የአገልግሎት ጥራት ይጨምራል፣ የአገልግሎት ዋጋ ይቀንሳል። ሁለቱም ሁኔታዎች ለተገልጋዩ ደንበኛ ጥሩ መልሶች ናቸው። በዚህ ሁኔታ ህዝቡ ተጠቃሚ ይሆናል።
አንድ ዘርፍ በሞኖፖል ከተያዘ ተጠቃሚው ባለ ሞኖፖሉ ነው። ባለሞኖፖሉ መንግስት ሲሆን ደግሞ ብዙ ገንዘብ ቢሰበስብ እንኳ የተፈለገውን ያህል ትርፋማ አይሆንም። ምክንያቱም ለግልና ለመንግስት ስንሰራ የመስራት መንፈሳችን ይለያያል። ባለሞኖፖሉ መንግስት ሙሰኛ ሲሆን ደግሞ የባሰ ኪሳራ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም (አንድ) ህዝብ ጥራት ያለው አገልግሎት አላገኘም። (ሁለት) ህዝብ ብዙ ገንዘብ ይከፍላል፣ ህዝብ ይከስራል፣ ላልተገለገለበትም ይከፍላል፣ አገልግሎትም አላገኘም። እናም የኢኮኖሚ ኪሳራ ይደርስበታል። (ሦስት) ያለ አግባብ ከህዝብ የተሰበሰበውን ገንዘብ ግለሰቦችን በሙስና ይወስዱታል። ገንዘቡ በሙስና ሲወሰድ ለሀገርም ለህዝብም ጎጂ ነው። ስለዚህ አጠቃላይ የህዝብም የሀገርም ኪሳራ ይሆናል።
ሙሰኛው መንግስት በሞኖፖል የያዛቸው ኢትዮቴሌኮምና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርጅት ያልተመጣጠነ ዋጋ በተገልጋዩ ላይ በመጫን ትርፋማ ነን ይሉናል። በተለይ ኢትዮቴሌኮምን በሞኖፖል መያዝ አዋጪ መሆኑ ፀሃዩ መንግስታችን በተደጋጋሚ ያስረዳናል። አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ እንዲሆም ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በተደጋጋሚ እንደገለፁት “ኢትዮቴሌኮም የምትታለብ ላም ነች” ትርፋማ ነች። አዎ! “የምትታለብ ላም ነች”። ምክንያቱም በመንግስት በሞኖፖል ተይዛለች። በሞኖፖል የተያዘ ሁሉ ትርፋማ ነው፤ የሚታለብ ላም ነው። የሚሰጠው አገልግሎት ወሳኝ እስከሆነ ድረስ።
ኢትዮቴሌኮም የምትታለብ ላም መሆኗ እኔም እመሰክራለሁ። መንግስትም እንደ ግለሰብ ትልቁ የአገልግሎት ተቋምን በሞኖፖል በመያዝ ህዝብን አለአግባብ ማለቡ ግን ያስተዛዝባል። መንግስት ስለሚሰበስበው ገንዘብ እንጂ ስለሚሰጠው አገልግሎት የሚጨነቅ አይመስለኝም። ምክንያቱም ኢትዮቴሌኮም እየሰጠን ያለው አገልግሎት እናውቀዋለን፤ ለደካማ አገልግሎቱ የምንከፍለው ገንዘብ እንዲሁ እናውቀዋለን። መንግስት እንዲህ በግልፅ “ኪራይ ሰብሳቢ” መሆኑ ሲነግረን መልካም ነው። እንዲህ ግልፅነት ልመዱ ነው የምንለው።
“ኢትዮቴሌኮም የምትታለብ ላም ስለሆነች ለሌላ አሳልፈን አንሰጥም” እያሉን ነው። መንግስት ቢጠቀም ችግር አልነበረውም። ምክንያቱም መንግስት ገንዘብ ሲያገኝ ህዝብን የሚጠቅም ስራ ይሰራበታል ነው የሚባለው። ገራሚው ነገር ግን በኢትዮጵያ ለህዝብ የሚያስብ መንግስት አለመኖሩ ነው። አሁን በኢትዮጵያ መንግስት አለ ለማለት ያስቸግራል። አስተዳደር ሳይሆን ገዢነት ነው ያለው፤ በመንግስት እየተገለገልን ሳይሆን እየተገዛን ነን ያለነው። አሁን እየተዳደርን ያለነው በገዢው ፓርቲ እንጂ በመንግስት አይደለም። ስለዚህ በመንግስት ስም የሚሰበሰብ ገንዘብ ለህዝብ ጥቅም እንዲውል ህዝባዊ መንግስትን ሊረከበው ይገባል እንጂ የአንድ ፓርቲ ንብረት መሆን የለበትም። የመንግስት ሃብት የአንድ ፓርቲ ንብረት ከሆነ ገንዘቡ ህዝብን ለመጥቀም ሳይሆን ህዝብን ለመጨቆን ይውላል። እያየን ያለነውም ይሄ ነው።
የኢትዮቴሌኮም ወተት የተመቸው ፀሃዩ መንግስታችን የምትታለብ ላሟን ለግል ዘርፉ አሳልፎ እንደማይሰጥ ደጋግሞ እየነገረን ነው። ባለስልጣኖቻችን ለዚሁ ምክንያት ሲያቀርቡ ደግሞ ኢትዮቴሌኮም ወደ ግል ዘርፍ ከተሻገረ የቴሌኮም አገልግሎት ወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ላይዘረጋ ይችላል የሚል ነው። የሚያቀርቡት ምክንያትም የቴሌኮም አገልግሎት በገጠር አከባቢ መዘርጋት ለግል ዘርፉ አዋጪ ስላልሆነ የግል ባለሃብቶች ወደ ገጠር አከባቢ ላያስፋፉት ይችላሉ። መንግስት ግን ወደ ገጠርም የማስፋፋት ተልእኮ አለው የሚል ነው።
ጥሩ የህዝብ (የገጠር) አሳቢነት ነው። ነገር ግን “የቴሌኮም የገጠር ዝርጋታ ለግል ዘርፉ አዋጪ አይደለም” በሚለው ሐሳብ አልስማማም። ምክንያቱም የግል ዘርፍ የትርፍ የማግኘት ዓላማ ስለያዘ ለትርፉ ሲል ወደ ገጠርም መግባቱ አይቀርም። በገጠርም ቢሆን የስልክ ተጠቃሚዎች አሉ። ምናልባት ገጠሩ ለግል ሴክተሩ አዋጪ ካልሆነ መንግስት የግል ዘርፉን ለማበራራታት በገጠሩ አከባቢ መሰረተ ልማት ማፋጠን ይችላል። መንግስት በገጠር አከባቢ የተሟላ መሰረት ልማት ከገነባ ለግል ዘርፉ አበራታች የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም።
ምናልባት መንግስት ቴሌኮምን ወደ ግል ካዛወረና የግል ዘርፉ ደግሞ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት ላይዘረጋ ይችላል ብሎ ከሰጋ ከጅምሩ (ዝውውሩ ሲፈፀም ወይም ጨረታው ሲወጣ) አሸናፊው ሴክተር ወደ ገጠር እንዲገባና መስመሮች እንዲዘረጋ ስምምነት መፈራረም ይቻላል።
መንግስት የግል ዘርፉ ወደ ገጠር አከባቢ ላይንቀሳቀስ ይችላል፤ የገጠር ህዝብ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ላያገኝ ይችላል ብሎ ከሰጋ ደግሞ ኢትዮቴሌኮምን በእጁ ይዞ ሞኖፖሉ ግን ማስቀረት (liberalize ማድረግ) ይችላል። ከሞኖፖል ወደ ዉድድር መሸጋገር ይችላል (There must be a shift from Monopoly to Competitive Approach) ። ይህ ማለት መንግስት ኢትዮቴሌኮምን ለግል ባለሃብቶችን ከመሸጥ (Privatize ከማድረግ) ይልቅ ዘርፉ ለሌሎችም ክፍት ማድረግ (Deregulate ማድረግ) ይችላል። (Focus on the Difference Between Privatization and Deregulation).
የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ Privatize ከማድረግ (ዘርፉ ወደ ግል ከማዛወር ወይ ከመሸጥ) ይልቅ ሌሎች የግል ባለሃብቶች እንዲሳተፉ መፍቀድ (Deregulate ማድረግ) ጥሩ ይመስለኛል። ምክንያቱም መንግስት ኢትዮቴሌኮምን በእጁ ስላለ የግል ዘርፉ በማይስቡ አከባቢዎች (ግን የቴሌ አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ህዝቦች በሚኖሩበት አከባቢ) መዘርጋት ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች የግል ባለሃብቶች በቴሌ አገልግሎት ሰጪነት ከተሰማሩ ለህዝብ አማራጭ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ይሰጣሉ። የኢትዮቴሌኮምን የጥራት ችግር ሲገጥመን ሌላኛው ቴሌ እንጠቀማለን። ኢትዮቴሌኮምም በውድድር ላለምሸነፍ ሲል አገልግሎቱ ጥራት ይኖረዋል፣ ዋጋም እንደፈለገ አይጭንብንም። ምክንያቱም ዋጋ የሚጭንብን ከሆነ ሌላኛው ቴሌ እንጠቀማለን። ዉድድር ስለሆነ የሚሰጡት አገልግሎት ጥራቱ ይጨምራል፣ የሚያስከፍሉት ዋጋ ይቀንሳል። በዚሁ ሂደት ህዝቡ ተጠቃሚ ይሆናል።
መንግስት ኢትዮቴሌኮምን በሞኖፖል መቆጣጠሩ ግን ለማንም አይጠቅምም፤ ከገዢው ፓርቲ ዉጭ። ህዝብ በሚከፍለው ገንዘብ ህዝብ መገልገል አለበት። ህዝብ በሚከፍለው የገዢው ፓርቲ ሰዎች የሚጠቀሚ ከሆነ ግን ችግር ነው። ገዢው ፓርቲ በህዝብ ገንዘብ እየቀለደ ያለ ይመስለኛል። መፍትሔ ማፈላለግ አለብን። ምክንያቱም እኛ ገንዘብ የምንከፍለው ህዝብና ሀገር ለማገልገል እንጂ ለገዢው ፓርቲ አባላት የሃብት ምንጭ ለመሆን አይደለም።
በአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ለውጥ (ዕድገት) ለማምጣት ዜጎች መሳተፍ አለባቸው። ዜጎች በኢኮኖሚ ሙሉ ተሳትፎ በማድረግ ለውጥ እንዲያመጡ ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል። በኢኮኖሚው ነፃ ዉድድር መኖር አለበት። የዜጎች ነፃ ዉድድር እንዲኖር ነፃነት የሚፈቅድ ፍትሐዊ ህዝባዊ መንግስት መኖር አለበት። ህዝባዊ መንግስት ዜጎችን ተወዳድረው ለውጥ የሚያመጡበት የኢኮኖሚ ስርዓት ይዘረጋል እንጂ ራሱ ከግለሰቦች ጋር የሚወዳደር መሆን የለበትም። ትርፋማ ሴክተሮችን እየተቆጣጠረ ለግል ባለሃብቶች ዕንቅፋት የሚሆን መንግስት አያስፈልግም። መንግስት ዜጎችን ማበረታታት እንጂ መቆጣጠር የለበትም። መንግስት ተቆጣጣሪ ከሆነ ትርጉም ያለው ለውጥ ልናመጣ አንችልምና።
ስለዚህ ህዝባዊ (ለህዝብ ደህንነት የሚሰራ) መንግስት ይኑረን። ህዝብን እንደ ላም የሚያልብ መንግስት ሳይሆን ህዝብን የሚያገለግል መንግስት ነው የምንፈልገው። መንግስት አገልጋይ እንጂ ተገልጋይ መሆን የለበትም።

No comments:

Post a Comment