BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Monday, 3 March 2014

የተምቤን ስብሰባችን ጉድ አደረገን

 (አብርሃ ደስታ)
ህወሓቶች በተለያየ አከባቢ የሚገኙ ወጣቶች ሰብስበው እያነጋገሩ ነው። የስብሰባው ዓላማም “በተቃዋሚዎች እንዳትሸወዱ፣ ከህወሓት ዉጭ ሌላ አማራጭ የላችሁም፣ ስራ እንሰጣችኋለን፣ በተቃዋሚዎች ስብሰባ እንዳትሳተፉ …” ወዘተ እያሉ ወጣቶቹን ለማስጠንቀቅ ነው።
ህወሓቶች ከልክ በላይ ፈርተዋል። ዓላማቸው ሁሉ ህዝብ በዓረና ስብሰባ ላይ እንዳይሳተፍ ማድረግ ነው። ለምን ይህን ያህል ፈሩ? የተምቤን ስብሰባችን ነው ጉድ ያደረገን። በተምቤን ዓብይዓዲ ስብሰባ በጠራንበት ግዜ ህወሓቶች የተከተሉት ስትራተጂ መጀመርያ ህዝብ ወደ ስብሰባ እንዳይገባ መከልከል፣ በድፍረት በስብሰባው ለመሳተፍ ከገባ ግን የህወሓት ካድሬዎችን በመላክና “ጠንካራ” ጥያቄዎችን በማንሳት የዓረና መሪዎችን ህዝብ ፊት ማዋረድ፣ ካድሬዎቹ የመከራከርና የመጠየቅ ዕድል ከተነፈጉ ደግሞ “ዴሞክራሲያዊ አይደሉም” በማለት በህዝብ ፊት ማጋለጥ የሚል ነበር።


ህዝብ በስብሰባው እንዳይሳተፍ የነበረ ዕቅድ አልተሳካም። ምክንያቱም ህዝቡ የካሬዎች ማስፈራራት ሳይበግረው ገባ። ካድሬዎችም ለመከራከርና ለመጠየቅ ገቡ። ጠየቁ፤ ተከራከሩ። እኛም በቂ መልስ ሰጠን። ተሳታፊም ገመገመን። በስብሰባው የተሳተፉ ካድሬዎች ሳይቀሩ በኛ ሐሳብ ተስማሙ። በህወሓት ስብሰባዎችም የዓረና አመራር አባላት ያነሱት ሐሳብ ተነሳ። እንዲረብሹን የተላኩ ካድሬዎች ጭራሽ የኛ ተወካዮች ሁነው በራሳቸው (በህወሓት) ስብሰባ የዓረና አጀንዳ እያነሱ መከራከር ጀመሩ። ህወሓቶች በዓረና ስብሰባ የተሳተፉ የህወሓት አባላት በሙሉ ዓረና ሁነዋል ብለው ደመደሙ። ከዛ በኋላ ማንም የህወሓት አባል ዓረና በሚጠራው ስብሰባ እንዳይሳተፍ ትእዛዝ ተሰጠ። (በየዞኑ ይካሄድ በነበረ የህወሓት ካድሬዎች ስብሰባ የተምቤን ካድሬዎች ጤነኞች አይደሉም በሚል ምክንያት ከሌሎች ጋር ሳይቀላቀሉ ለብቻቸው እንዲሰበሰቡ ተደርጓል)።

ከተምቤን ስብሰባ በኋላ ዓረና ህዝብ ሰብስቦ ማነጋገር አልቻለም። የሽረ፣ ዓዲግራትና ሑመራ ተረብሿል። አሁን ህወሓቶች እየተከተሉት ያለ ስትራተጂ ህዝብ በዓረና ስብሰባ እንዳይገኝ መከልከል ብቻ ነው። ምክንያት: በዓረና ስብሰባ የተሳተፈ ሰው (የህወሓት አባል ጭምር) ዓረና የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው የሚል ነው።
አሁን በብዙ አከባቢዎች እየተደረገ ያለው ጥረትም ህዝብ ሌላ አማራጭ የፖለቲካ ድርጅት ሐሳብ እንዳይሰማ በራሳቸው ፕሮፓጋንዳ ማደንቆር ነው። ዓረና ህዝብ እንዳይሰበስብ በመከልከል ራሳቸው ስብሰባ እየጠሩ በዓረና ስብሰባ እንዳይሳተፍ ያስጠነቅቁታል። ህዝብ ግን ለውጥ ይፈልጋል፣ ተነሳስቷል።
የትግራይ ህዝብ ለምንድነው የራሱ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዲያዳብር የማይፈቀድለት? ለምንድነው በህወሓቶች ትእዛዝ እንዲያስብ፣ እንዲጓዝ የተፈረደበት? የትግራይ እናት የህወሓት ሰዎች ወልዳ መክናለች ያለ ማነው? የትግራይ ህዝብ የፈለገውን የመከተል መብቱ የተነፈገው ብዙ መስዋእትነት ስለከፈለ ነው? በነፃነት ለመኖር መስዋእት መክፈል አያስፈልግም ማለት ነው? እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጎ፣ ብዙ መስዋእትነት የከፈለ ህዝብ ለምን በነፃነት እንዳያስብ ታፈነ? ወጣቶችን በመሰብሰብ ህወሓቶች ከሚጓዙበት መንገድ ዉጭ ሌላ አቅጣጫ መከተል ስህተት እንደሆነ መስበክ ለወጣቶቹ ያለንን ንቀት አያሳይም? ወጣቶችኮ የራሳቸው መንገድ አላቸው። ለምን ነፃ እንዲሆኑ አይፈቀድላቸውም?
አዎ! በዓረና ስብሰባ የተሳተፈ ሁሉ ዓረና እንደማደርገው አልጠራጠርም፣ የህወሓት አባላትም ጭምር። ያለኝ ዕቅድ በዓረና ስብሰባ የተሳተፈ ሁሉ ዓረና ማድረግ ነው፤ እንደ ህወሓት በጠብመንጃ በማስፈራራት ወይ ገንዘብና ስልጣን በመስጠት አይደለም። በሐሳብ በማሳመንና የለውጥ አስፈላጊነት በማስረዳት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የመገንባት ተልእኮአችን በመጠቆም እንጂ።
ወጣቶች ሆይ! በስብሰባ እንዳትሳተፉ የሚደረግ ማንኛውም ትእዛዝ አትቀበሉ። ምክንያቱም በየትኛውም ስብሰባ የመሳተፍ መብት አላቹ። በስብሰባ ለመሳተፍና ላለመሳተፍ የሚወስንላቹ ህወሓት ሳይሆን እናንተ ናችሁ። ምክንያቱም በህይወታቹ ላይ ተፅዕኖ ላለው ጉዳይ የመወሰን ነፃነቱ ሊኖራቹ ይገባል። ህወሓት ከናንተ በላይ ስለናንተ አያውቅም። በለውጥ ሂደቱ ተሳታፊ ሁኑ። ህልውናችሁን አረጋግጡ። ህወሓት እየሰራው ያለው ተግባር በራሱ ዓፈና ነው። ጭቆና ነው። ፀረ ዓፈና ተነሱ። ጭቆናን አስወገድን ነፃነታችንን እናስመልስ።
እዛው በነፃነት ሥፍራው እንገናኝ። እጠብቃችኋለሁ።

No comments:

Post a Comment