BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Sunday, 2 March 2014

የሐሳብ ነፃነትና የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ፈታኝ ጉዞ



በጉተማ ዘለዓለም
ዜጎች መረጃ የማግኘት፣ የማሰራጨትና የማሰተላለፍ መብት ሊያገኙ የሚችሉት የሐሳብ ነፃነት ያለገደብ ሲረጋገጥ ነው፡፡
ሐሳብን በነፃነት መግለጽ (Freedom of Expression) እውን ሆነ ማለት ደግሞ የሰው ልጅ ዲሞክራሲያዊ መብቶች (መምረጥ፣ መመረጥ፣ መደራጀት፣ ሠልፍ ማድረግ፣ የፈለጉትን አቋም የመያዝ…) መብቶች የመከበር ዕድል ይሰንፍላቸዋል፡፡ ለዚህም ነው በብዙ የዓለማችን አገሮች ሕገ መንግሥቶች የሐሳብ ነፃነት እንደ ዲሞክራሲ ምሰሶ እየተወሰደ ያለው፡፡ በዚያው ልክ የሐሳብ ነፃነትና የመረጃ ፍሰትን ለመገደብ የሚሞክሩ መንግሥታትም ገዳቢና ፀረ ዲሞክራሲያዊ ካባ ተደርቦላቸው የሚስተዋሉት፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ1946 ባፀደቀው ድንጋጌም ሆነ ከሁለት ዓመት በኋላ ባፀደቀው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ አንቀጽ 19 የሐሳብ ነፃነት ጉዳይ የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶች የማዕዘን ድንጋይ መሆኑ ተገልጿል፡፡ (Freedom of Expression is a Fundamental Human Right and … The Touchstone of All the Freedom) ሲል ገልጾታል፡፡ እርግጥ ይህ ድንጋጌ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ሰነድ ሙሉ ዕውቅና ከማግኘቱ በፊት የሐሳብና የመረጃ ነፃነትን ጉዳይ በሕገ መንግሥታቸው በግልጽ ያስቀመጡ አገሮች አሉ፡፡
በቀዳሚነት የምትጠቀሰው ስዊድን ስትሆን እ.ኤ.አ. በ1766 በፀደቀው ሕገ መንግሥቷ የመረጃ ነፃነትን ጉዳይ ከዲሞክራሲ መብቶች ጋር አገናኝታ አፅድቃለች፡፡ የአሜሪካ የ1791 ሕገ መንግሥት ጉዳዩን ነጥሎ ባይመለከትም የሐሳብ ነፃነት በኮንግረሱ አሠራሮች ሙሉ ዕውቅና ያለው ጉዳይ ነው፡፡ ህንድ እ.ኤ.አ. በ1982፣ ደቡብ ኮሪያ እ.ኤ.አ. በ1989፣ ደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ1996 በሕገ መንግሥታቸው ውስጥ በማካተት የሕዝባቸውን የመረጃ ነፃነት አረጋግጠዋል፡፡ ታይላንድ እ.ኤ.አ. በ1997 ጃፓንም እ.ኤ.አ. በ2001 ትልቁን የዲሞክራሲ ጉዳይ በፅናት መተግበር መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ለአብነት ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ሳይሆኑ ዛሬ ዛሬ በርካታ የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገሮች ሳይቀሩ የሐሳብ ነፃነትን በሕገ መንግሥትና በሕግ ማዕቀፍ ደግፈው ለመተግበር እየተሯሯጡ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ላይ ካረጋገጠው ሁለት አሥርት ዓመታት መቆጠራቸው በግልጽ ይታወቃል፡፡ ከዚህም አልፎ በአዋጅ 590/2000 ‹‹የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት›› ሕግ በማውጣት፣ ቀደም ሲል በነበሩት የፕሬስ ሕጐችና ሌሎች ተያያዥ ድንጋጌዎች የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላት በሚል ጥረት ማድረጉን መንግሥት ይገልጻል፡፡
በእርግጥ የአዋጁን መውጣት የሕገ መንግሥቱን የመረጃ ነፃነት ድንጋጌ ‹‹ለመገደብ ነው›› በማለት የሚከራከሩም አሉ፡፡ ብዙዎችን የሚያስማማው ግን አዋጁን ሁሉም አካላት መንግሥታዊ ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኃንና ሕዝቡ በግልጽ ተገንዝበውት ቢወጣ ኖሮ፣ የዜጎች ትክክለኛ ሚዛናዊ መረጃ የማግኘት መብት ቢረጋገጥ እንደ ትልቅ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ይገልጻሉ፡፡
የዜጎችን መረጃ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ አዋጁ ሥልጣን የሰጠው የኢፌዲሪ ዕምባ ጠባቂ ተቋም (Ombudsman) በአዋጁና ተያያዥ ሥራዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችና አጋዥ መመርያና ደንቦችን በማውጣት ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌው ሳይሸራረፍ እንዲከበር እየሠራ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ተቋሙ ያለበት የአቅም ውስንነትና በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው ሚስጥራዊ ባህሪ በታሰበው መጠን አዋጁን ለመተግበር እንዳላስቻለ ባይካድም፡፡
በቅርብ ጊዜ ተቋሙ በጥናት ላይ ተመሥርቶ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ‹‹የመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች የሕዝብ መረጃን በአዋጁ መሠረት ተደራሽ በማድረግ በኩል ክፍተት እየታየባቸው ነው፤›› ሲል ገልጿል፡፡ በተለይ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሎችና ሙያተኞች መረጃን አደራጅቶና ተንትኖ በአመቺ ሁኔታ ለሕዝብ በማድረስ ረገድ ወደኋላ የቀሩ መሆናቸው ታይቷል፡፡
ጥናቱ፣ ‹‹ብዙዎቹ የሕዝብ ግንኙነቶች (ኮሙዩኬተሮች) በቂ መረጃ የላቸውም፡፡ በልበ ሙሉነት ለመገናኛ ብዙኃንም ሆነ ለሕዝቡ መረጃ የማድረስ ችግር አለባቸው፡፡ በተቋማት ክፍተቶችና ድክመቶች ላይ መረጃ መስጠት አይሹም፡፡ አዋጁ የማይከለክላቸውን መረጃዎች ‹ሚስጥራዊ› በማስመሰል ይይዛሉ፡፡ ይኼ ደግሞ ለሙስናና ለሌብነት ተጨማሪ ዕድል ይሰጣቸዋል) አንዳንዶች ከመረጃ ሥራ ውጭ ተጠምደው ይውላሉ…››  ሲል ገልጿቸዋል፡፡ መልካም የመረጃ ነፃነት ትግበራ ሥራ ዘላቂና አስተማማኝ ሥርዓት ለመዘርጋት ጥረት የሚያደርጉ አካላት ቢኖሩም ቁጥራቸው ውስን እንደሆነ በመጥቀስ፡፡ አንዳንድ የመንግሥት (በተለይ የክልል መንግሥታት) የሥራ ኃላፊዎችም መረጃ ለሕዝብ የማድረስ ግዴታ እንዳለባቸው ያለመገንዘባቸውና አስገዳጅነቱን መዘንጋታቸውም እንደመሰናክል ተወስቷል፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፍተቶችን ፈጥኖ ማረም ካልተቻለ ደግሞ ቀስ በቀስ ግለሰባዊ አምባገነንነት እየጎለበተና እየሰፋ እንደሚሄድ የሚሰጉ በዝተዋል፡፡
ጥናቱ በአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቱ ተነሳሽነት ተካሂዶ በመረጃ ነፃነት ትግበራ ላይ የመንግሥት አካላት ክፍተት ጎልቶ መታየት አንድ ነገር ያመላክታል፡፡ በርካታ የሥርዓቱ ተቺዎች የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች ጨምሮ ሌሎች አዋጆችና ደንቦች ሳይሸራረፉ በመተግበር ረገድ የመንግሥት አካላት የጎሉ ክፍተቶች አሉባቸው የሚሉት አባባል ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ እርግጥ ይህ ተግዳሮት የብዙዎቹ የአፍሪካ መንግሥታት በሽታ መሆኑን የሚጠቅሱ አሉ፡፡
በአዋጅ 590/2000 መሠረት የመንግሥት አካላት ሊከለክሉዋቸው የሚችሉ መረጃዎች ይታወቃሉ፡፡ የሦስተኛ ወገን መረጃ፣ የግለሰቦችና የንብረት ደኅንነት ጉዳይ፣ በቁጥጥርና በጥበቃ ሥራ፣ በመከላከያ፣ ደኅንነትና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በካቢኔ ሰነዶች፣ ወዘተ  ዓይነት መረጃዎች ይሆኑና ሲከለከሉ በሕገ መንግሥቱም አንቀጽ 27 መሠረት ግን ከሕዝብ ጥቅም ጋር መመዛዘን አለበት የሚለውን ማነፃፀሪያ ፍርድ ቤቶች ሳይቀሩ እንደሚዘነጉት በስፋት ይነጋገራል፡፡
አዋጁ፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ከማንኛውም መንግሥታዊ አካል መረጃን የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብትን›› አረጋግጧል፡፡ መረጃውም በማንኛውም መልክ ለሕዝብና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይሁንና የመንግሥት አካላት በቋሚነት መረጃን አትሞ የማውጣት ግዴታን ያለመተግበር እንቅፋቶች ይስተዋሉባቸዋል፡፡ በዚያው ልክ መረጃን ማዛባት፣ መከልከልና ማጉደል በሕግ የሚያስጠይቅና የሚያስቀጣ ሆኖ ሳለ ከዕንባ ጠባቂ ተቋም አልፎ በፍርድ ቤት የተከሰሱ መረጃ ከልካይ የመንግሥት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አለመኖራቸው ተጠቁሟል፡፡
የዲሞክራሲ ሥርዓት ዋነኛ መገለጫ የሆኑት የነፃነው ፕሬስ ባለሙያዎችና አሳታሚዎች እንቅስቃሴ ግን ከአዋጁና ከሌሎች ሕጐች ጋር የሚያፋጥጥ እየሆነ መምጣቱን ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ከፀረ ሽብር ሕጉ አንፃር በዜጎች ደኅንነት፣ በብሔራዊ ጥቅም፣ በብሔር ብሔረሰቦች የጋራና የተናጠል መብቶችና ጥቅሞች እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የሚያውኩና የሚያደፈርሱ የመረጃ ልውውጦች በሕግ የሚያስጠይቁ ናቸው፡፡ ከላይ በተጠቀሰው አዋጅ መሠረትም የተከለከሉ መረጃዎችን ማተምና ማሰራጨት ብቻ ሳይሆን ሐሰተኛ ዘገባዎችን ማቅረብ በሕግ የሚያስጠይቅ ነው፡፡ 
በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች እስካሁን ባለው የአገሪቱ የመረጃ ነፃነት ሒደት የተጠየቁና የተከሰሱ ጋዜጦች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ የመንግሥት ዕርምጃ ‹‹በመዝጋት›› አገር ጥለው የተሰደዱ ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች መኖራቸው በተደጋጋሚ የሚገለጽ ሲሆን፣ መንግሥት በበኩሉ ‹‹በሽብር ድርጊትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በአመፅ ለመናድ ከሚደረጉ ጥሪዎች ጋር በተያያዘ ከሚጠየቁ የስም ጋዜጠኞች በስተቀር፣ የሐሳብ ነፃነትና የመጻፍና የመናገር መብት በሚከለክል አግባብ የታሰሩም ሆነ የተከሰሱ ጋዜጠኞች የሉም፤›› ሲል በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡
የጋዜጠኞች መብት አስከባሪ ኮሚቴ (ሲፒጄ) የመሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግን በኢትዮጵያ የጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፖለቲካ ኃይሎች ነፃ እንቅስቃሴን የሚገድብ ጠባብ ሥነ ምኅዳር እንዳለ ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ በተለይ ከመረጃ ነፃነት አዋጁ በላይ የፀረ ሽብር አዋጁን ‹‹ገዳቢ›› ሲሉት ተደምጠዋል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎችና የግሉ ፕሬስ አባላትም ይኼንኑ ሐሳብ በስፋት ያራምዳሉ፡፡
ሲፒጄ እ.ኤ.አ. በ2012 በዓለም በተለይ በታዳጊ አገሮች ጋዜጠኞች ዙሪያ ያደረጋቸውን ጥናታዊ ጽሑፎች በዌብሳይቶች ላይ ለቋል፡፡ ዘጋርዲያን የተባለው ታዋቂ ጋዜጣም ጥናቶቹን ምንጭ አድርጐ በቅርቡ በድረ ገጹ በለቀቃቸው ጽሑፎች፣ ‹‹በዓለም ላይ ባለፉት አሥር ዓመታት በሥራቸው ምክንያት በተጋረጠባቸው የሕይወት ፈተናና ግጭት 348 ጋዜጠኞች ተገድለዋል፡፡ በአንዳንድ አገሮችም የጋዜጠኞችን ጉዳት ያጋለጡ ምስክሮች ጭምር ግድያና እስራት ያጋጥማቸዋል፤›› ሲል ጽፏል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ጋዜጠኞች በድምፅ አልባ ሳንሱር፣ ጫናና ክልከላዎች ሳቢያ የሕዝብ ድምፅ የመሆን ሚናቸውን ከመጫወት ይልቅ የጠላትነት ፍረጃ እንደሚገጥማቸውም ነው የገለጸው፡፡
ከሌላ ወገን በሚነሱ አስተያየቶች ደግሞ፣ ‹‹ጋዜጠኞች የማንኛውም ሚዛናዊ፣ ዋጋ ያለው (Valuable) ጠቃሚ መረጃ አስተላላፊ መሆን ሲገባቸው የሕግ መሠረት የሌላቸው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች መሣሪያ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ ለሽብርተኝነት፣ ለሕገወጥ ዝውውርና ለዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች አጋዥ ሆነው ይታያሉ፤›› ብለው እንዲ ዓይነት ፈጽሞ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ለሕዝብ ጥቅም የማይበጁ ድርጊቶች መወገድ እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡ (የአፍሪካ ጋዜጠኞች ኅብረት ጆርናል ላይ በቀረበ የጋዜጠኛ ኩዋን ተሮልን ጽሑፍ) 
በኢትዮጵያ ከተጀመረው የመረጃ ነፃነትና የመገናኛ ብዙኃን ሚና አንፃር ሁለት የተበላሹ መንገዶች በጥንቃቄ መፈተሽ እንዳለባቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል አንድ መምህር ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ከመስጠት ይልቅ መንግሥትን በመቃወምና በመደገፍ ጭፍን መረጃ የሚሰጡ የሁለት ዓለም መገናኛ ብዙኃን አሉ፤›› የሚሉት መምህር፣ መንግሥት ‹‹በልማታዊ ጋዜጠኝነት›› ስም በስኬታማ ታሪክ (Success Story) እና ወደሚፈልገው ሐሳብ የሚንቀሳቀሱ ሚዲያዎችን እየፈጠረ፣ ሁለተኛና አማራጭ ሐሳቦችን እየገደበ መሆኑን በግልጽ ተችተዋል፡፡ 
ሌሎች ደግሞ በግል ጋዜጣ ስም ‹‹ፅንፈኛ›› አቋም (ሙሉ በሙሉ ለሥርዓት ለውጥ የሚንቀሳቀስ ተቃውሞ) የሚያራምዱ የሕትመት ውጤቶች ተበራክተዋል ይላሉ፡፡ እነዚህኞቹ የፈለጋቸውን አመለካከትና እምነት የመያዝ መብት ቢኖራቸውም፣ በአገሪቱ ምንም በጎ ጅምር እንደሌለና የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ሳይቀር የሚጎዱ አስተያየቶችንና ትንተናዎችን ማቅረባቸው ብዙዎች አልወደዱላቸውም፡፡ ምንም እንኳ በመንግሥታዊ ተቋማት የተደረገ ዳሰሳ ቢሆንም፣ በቅርብ ጊዜ በመጽሔቶች ይዘት ላይ የወጣ የ‹‹አዝማሚያ›› ትንተና መመልከታችንም ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳን እንዲህ ዓይነቱ ትንተና ጠቃሚ ባይሆንም፡፡
‹‹ዲሞክራሲ ጉዞ ነው በሒደትም እያደገ መሄድ አለበት›› የሚል የጋራ ግንዛቤ ከያዝን ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም አካሄዶች ለአገር ሊጠቅሙ አይችሉም፡፡ በግልጽና በማያሻማ መንገድ ራሳቸውን አስተካክለው ሁሉም ለሕዝብና ለአገር ጥቅም መወገን አለባቸው፡፡ አንዳች ዓይነት ጥፋት ከታየ መንግሥትና የመንግሥት አካላት፣ ተቃዋሚዎችንና ሌሎችንም መተቸት፣ መውቀስና በመረጃ ላይ በተመሠረተ መንገድ መንቀፍ አለባቸው፡፡ በተቃራኒው በመልካም ሥራና በጎ ጅምር ላይ ያለውን የትኛውንም አካል ቢሆን በርታ ወይም ቀጥል መባል አለበት፡፡
በእርግጥ በየትኛውም ዓለም የመረጃ ነፃነት ውስጥ ያሉ አዋኪ ጉዳዮች በገደብና  ያለገደብ የሚሰራጩ ሐሳቦች ናቸው፡፡ አንዳንዶች በእኛም አገር እየታየ እንዳለው በመንግሥታዊ መዋቅር መረጃ የሚከለክሉ፣ የሚገድቡ፣ የአስተዳደር ጥሰት የሚፈጽሙ፣ የፍትሕ መዛባትን የሚያደርሱ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ ያለገደብ ባገኙት መረጃ (በተለይ ጋዜጠኞች) ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ፤ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ድንጋጌዎችን የሚጥሱ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የሚበድሉ፣ ወዘተ ድርጊቶችን ይፈጽማሉ፡፡ መፍትሔው ሚዛናዊ፣ ሀቀኛና ለዲሞክራሲያዊ መርሆዎች መቆምና አገርን ማስቀደም ብቻ ነው፡፡
በዚህ ረገድ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ለመጥቀስ እወዳለሁ፡፡  ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት ፈተና የሚገጥመው በመንግሥት ሰዎች ዘንድ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱን ዋስትና ከወረቀት ጌጥነት እንዳያልፍ የሚፈልጉ ፀረ ዲሞክራሲ አመለካከት ያላቸውን አደብ ያስገዛ፡፡ መንግሥት የዜጎችን ነፃነት ማክበር ከተሳነው አገር የመምራት ኃላፊነቱን መወጣት ከቶም አይችልም፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል ሕገ መንግሥቱን ያክብር፡፡ በዲሞክራሲ ጉዳዮች (የመረጃ ነፃነትን ጨምሮ) ለዘብተኛ መምሰሉን ያቁም፣ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ፣ መዋቅሩን ይፈትሽ፣ ከመረጃ ውጪ የሆነ ማኅበረሰብ እንዳይፈጠር ይትጋ፡፡
በሌላ በኩል የመረጃም ሆነ የሐሳብ ነፃነት የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛ ምሰሶ የሆኑት መገናኛ ብዙኃን የግልና የመንግሥት ሳይባሉ አቅም ይገንባ፣ ይደግ፣ ሲሳሳቱ ያርም፣ ይቅጣ፡፡ የጥላቻና የሁለት ፅንፍ አስተሳሰብ እንዲወገድ ይሥራ፣ መቀራረብ ይምጣ፡፡ የጎራ ፍልሚያው ይብቃ!
በተጨማሪም ኢትዮጵያ አገራችን በልማትና በዕድገት ውስጥ ነች ሲባል ለቁሳዊው ዕድገት ብቻ ትኩረት መሰጠት የለበትም፡፡ ከምንም ነገር በላይ የሆነው የሰው ልጅ ነፃነት ክቡር ዋጋ ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ዋስትና የሰጣቸው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ከምንም ነገር በላይ በተግባር ሊረጋገጡ ይገባል፡፡ ዜጎች የፈለጉትን መደገፍ፣ መቃወም፣ ድምፅ መስጠትና መንፈግ፣ ሐሳባቸውን በነፃነት ማንፀባረቅ ተፈጥሮአዊ መብታቸው መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ እነዚህ መብቶች ባልተከበሩበት ስለልማትና ዲሞክራሲ ማውራት ትርጉም የለውም፡፡
ኢትዮጵያ አገራችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ እንድትሠለፍ የሚደረገው ጥረት በቁሳዊ ሀብት ብቻ የሚለካ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ  በዕውቀት የደረጀ፣ አካባቢውን የሚገነዘብ፣ ከጭፍንነትና ከጥላቻ የፀዳ፣ መብቱንና ግዴታውን የሚገነዘብ፣ ለእናት አገሩ ዘለቄታዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክት፣ የማንም ተላላኪ ያልሆነ፣ ወዘተ እንዲሆን ከፈለግን ነፃነቱን ማክበር የግድ ነው፡፡ ይህ ነፃነት ደግሞ በማንም የሚሰጥና የሚከለከል እንዳልሆነ ሁላችንም በሚገባ ማወቅ ይኖርብናል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጹሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው   Gzelalem@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

No comments:

Post a Comment