ከኖርዌ/ኦስሎ
ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀፀላ እና ጋዜጠኛ ደረጀ ሐ/ወልድ በተገኙበት ኢሳት የኔ ነው ምሽት በኦስሎ ከተማ በድምቀት ተከናወነ። በማርች 1, 2014 የተዘጋጀው የኢሳት ምሽት ከተለያዩ የኖርዌይ ከተሞች በመጡ ታዳሚዎችና በኦስሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑ በርካታ የኢሳት ቤተሰቦች የተገኙበት ሲሆን ዝግጅቱ በኖርዌ የኢሳት ም/ሰብሳቢ በሆኑት አቶ ሙባረክ ንግግር በኖርዌጅያን ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ 16፡00 ተጀምርዋል። በማስከተል የኢሳት ኖርዌ ዋና ተወካይ ጋዜጠኛ አበበ ደመቀ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የኢትዮጵያ ማህበር በኖርዌ ሊቀመንበርና ሌሎችም ግለሰቦች በየተራ ስለኢሳት ያላቸውን ስሜት ሲገልፁ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች ኢሳት መረዳት ያለበት ነፃ ሚዲያ በመሆኑና የመረጃ እረሃብ ላለበት ወገናችን እኛን ጨምሮ ትክክለኛ መረጃ የሚያቀርብልን የዜና ድርጅት ስለሆነ መሆኑን ገልፀዋል። ኢሳት የኢትዮጵያውያን አይንና ጆሮ መሆኑንም ታዳሚዎቹ የተስማሙበት በመሆኑ ብዙ የኢሳት ቤተሰቦች በቋሚነት ኢሳትን ለመደገፍ የተዘጋጀውን ቅፅ በመሙላት ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ አረጋግጠዋ።
ጋዜጠኛ ደረጀ የህዝብን ልብ የሚሰብር ስደትን የተመለከተ ግጥም ለታዳሚዎቹ ያቀረበ ሲሆን ጋዜጠኛ መታሰቢያም ሃገራችን በመረጃ እጥረት ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ሁኔታዎች ቁልቁል እየወረደች ያለች ሃገር መሆኗን የሚገልፁ መረጃዎችን ለህዝብ በማቅረብ ሃገራችንን መታደግ ያለብን እኛው እራሳችን መሆናችንን ጠቁማለች። ስለ ሃገራችን የተለያዩ አስተማሪና አሳዛኝ ግጥሞች ከተለያዩ ግለሰቦች የቀረበ ሲሆን ምግብና መጠጥ፤ የኢሳት አርማ ያለበት ቲሸርት እና የተለያዩ ቁሳቁሶች ለሽያጭ ቀርበዋል። በተጨማሪም ሐይለኛ ፉክክር የተደረገበት የጨረታ ጊዜም ነበር።
ለኢሳት ጋዜጠኞችና ለኢሳት ያላቸውን ክብር ለመግለፅ እንዲሁም ሁልጊዜም ከኢሳት ጎን መሆናቸውን ለማረጋገጥ ኢሳት የኔ ነው የሚል ፅሁፍና በእረንጓዴ ቢጫ ቀይ የኢትዮጵያ ባንዲራ ያሸበረቀ ኬክ ጋዜጠኞቹ እንዲቆርሱ ምህረትና ሄለን ያቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም የኢሳት አርማ ያለበት ኬክም በኢሳት ኖርዌ ተወካይ ወ/ሮ ትንሳኤ ቀርቦ ለዝግጅቱ ከፍተኛ ድምቀትን ሰጥቷል።
በአጠቃላይ ፕሮግራሙ እጅግ የተሳካና ከታቀደው በላይ የገቢ ማሰባሰቢያ የተገኘበት እንደሆነ ከአዘጋጅ ኮሚቴው የተገለፀ ሲሆን ዝግጅቱ ከምሽቱ 16፡00 ተጀምሮ ከምሽቱ 22፡00 ተጠናቋል። ይህንን መድረክ ከመጀመሪያ እስከመጨረሻ ይመሩ የነበሩት አርቲስት እንዳለ ጌታነህ ነበሩ።
ህዝባቸን ከአምባገነኖች ጫንቃ ተላቆ ነፃ እስኪወጣና ትክክለኛ መረጃ አግኝቶ የመናገር የመፃፍ ህጋዊ መብቱ ተረጋግጦ፤ በሃገራችን የህግ የበላይነት ተከብሮ እስክናይ ድረስ ኢሳት የህዝብ አይንና ጆሮ ሆኖ እንዲቀጥል የሁላችንም ድጋፍ እንዳያቋርጥ በዚሁ አጋጣም ለማስገንዘብ እወዳለሁ።
በእኛ ድጋፍ ኢሳት የኢትዮጵያውያን አይንና ጆሮ ሆኖ ይቀጥላል
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር
No comments:
Post a Comment