BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Sunday, 2 March 2014

መንግሥት ለምን ይደበቃል?

በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ሕዝባዊ ጥያቄ እያስነሱ ያሉት የአገልግሎት መሳከሮችና መቆራረጦች ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማት ማብራሪያም ሆነ ይቅርታ ሲጠየቅባቸው አይሰማም፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ ክልሎች የውኃ አቅርቦት ለበርካታ ቀናት ሲቋረጥ ምክንያቱ አይነገርም፡፡ ይቅርታ አይጠየቅም፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ለቀናት ሲጠፋ ማብራሪያ የለም፡፡ ይቅርታ አይባልም፡፡ የመስመርና የሞባይል ስልክ አገልግሎት ሲቋረጥ ምክንያቱ በውል አይታወቅም፡፡ ይቅርታ የሚጠይቅ አይታይም፡፡ የኢንተርኔት አገልግሎት ሲቆም ምላሽ የሚሰጥ የለም፡፡ ይቅርታ ማለት ሞት ሆኗል፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ጠፍቶ ሕዝብ ፀሐይ ላይ ሲንቃቃ ወይም በዝናብ ሲደበደብ ችግሩን የሚያስረዳ የለም፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ አገልግሎት ፈላጊዎች መስተናገድ ሲያቅታቸው እንኳን ይቅርታ ሊባል የተፈጠረውን ችግር የሚናገር የለም፡፡ በርካታ ችግሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ 
በእርግጥ በማንኛውም ሥራ ውስጥ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን ችግሮችን ተናግሮ መፍትሔ ከማፈላለግ ይልቅ መደበቅ እየበዛ ነው፡፡ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮች ሲፈጠሩ ሕዝብን ይቅርታ ጠይቆ በትዕግሥት እንዲጠባበቅ ከማሳወቅ ይልቅ ለአላስፈላጊ መላምቶችና ውዥንብሮች መዳረግ እየበዛ ነው፡፡ ችግሮችን ቢቻል በግንባር ካልሆነም በሚዲያ ቀርበው ማስረዳት የሚጠበቅባቸው ሹማምንት መደበቅን የተለመደ ተግባር በማድረጋቸው፣ ማብራሪያና ይቅርታ የደረሱበት ጠፍቷል፡፡
ሕዝቡ በውኃ እጦት ምክንያት ምግቡን ማብሰል፣ ንፅህናውን መጠበቅ፣ ሕፃናት ልጆችን መንከባከብ፣ ሕሙማንን ማስታመም፣ ወዘተ ሲያቅተው በግልጽ እየታየ ነው፡፡ አረጋውያንና ሕፃናት ሳይቀሩ ውኃ ፍለጋ ባልዲና ጀሪካን ተሸክመው በሌለ ጉልበታቸው ሲባዝኑ በአደባባይ ይታያል፡፡ ችግሩ እንዲህ ገዝፎ እንዴት ማብራሪያ መስጠት ይቸግራል? ይቅርታ ማለትስ ማንን ገደለ? የችግሩን መጠን በግልጽ አሳይቶ ሕዝቡን የመፍትሔ አካል ለማድረግ ለምን አልተፈለገም? ሌላው ቀርቶ ችግሮቹ እስኪቀረፉ ድረስ መንግሥት ራሱ ሕዝቡ እንዲታገስ ለምን ጥሪ አያቀርብም?
የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ከአንድ ግለሰብ እስከ ትላልቅ የግልና የመንግሥት ማምረቻ ተቋማት ድረስ እየፈጠረ ያለውን አበሳ እያየን ነው፡፡ በቀን ለበርካታ ጊዜያት ብልጭ ድርግም እያለ የተለያዩ ማሽኖችን፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን፣ ፍሪጆችን፣ ቴሌቪዥኖችን፣ የሲዲ ማጫዎቻዎችን፣ የማብሰያና መሰል ዕቃዎችን እያቃጠለ የዜጎችን ንብረት በማውደም ለከፍተኛ ኪሳራ ሲዳርግ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ይባላል፡፡ በኃይል መቋረጥ ምክንያት ምርት ሲቆምና ዜጎች ማግኘት የሚገባቸውን ክፍያ ወይም ጥቅም ሲያጡም እንዲሁ ዝም ነው፡፡ ማብራሪያ ወይም ይቅርታ የለም፡፡

No comments:

Post a Comment