BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Tuesday, 4 March 2014

ግንቦት ሰባት አንድነት/መኢአድ ለሚያደርጉት ሰላማዊ ትግል አጋርነቱን ገለጸ

 - ግርማ ካሳ

በግንቦት ሰባት ንቅናቄ ላይ ጠንካራ ትችት ከሚሰነዝሩት ወገኖች መካከል አንዱ ነኝ። በዋናነት ከዚህ ድርጅት ጋር ለበርካታ አመታት ሲያላትመን የነበረው፣ ድርጅቱ የትጥቅ ትግል ስለጀመረ ወይንም ጀምሪያለሁ ስለሚል አልነበረም። ምነው ሌሎች የትጥቅ ትግል እናደርጋለን የሚሉትን ለምን አልተቃወምንም ? ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባርን ተችተን ብዙ የጻፍንበት ሁኔታ የለም። ለምን ዜጎች ግፍና ቀንበር ከበዛባቸው የመሸፈት፣ ነፍጥ የማንሳት ሙሉ መብት አላቸውና። እኛ ያውም በዉጭ አገር ተቀምጠን ፣ ለምን የትጥቅ ትግል ያደርጋሉ የማለት አንዳችም የሞራል ብቃት የለንም።

ከግንቦት ሰባት ጋር ችግራችን የነበረው፣ በተለያዩ ጊዜያት የአመራር አባላቱ፣ አገር ቤት የሚደረገዉን ሰላማዊ ትግል ያጣጥሉና ያሳንሱ ስለነበረ ነዉ። «በሰላም አገዛዙን መቀየር የማይታሰብ ነው፤ ቀልድ ነው ፣ ምርጫ አትሳተፉ፣ ምርጫዉ ቦይኮት ይደረግ…ወዘተረፈ» እያሉ በማያገባቸው እየለፈፉ፣ በዉጭ ያለው ማህበረሰብ ተስፋ እንዲቆርጥ፣ ትኩረቱን ወደ አስመራ፣ ወደ እነርሱን ብቻ እንዲያደርግ ይፈልጉ ስለነበረ ነው። እንደዉም በቅርቡ ሰማያዊ ፓርቲ የሰላሙን ትግል ትቶ እነርሱን እንዲቀላቀለም በይፋ የጠየቁበትም ሁኔታ አለ። «ስለ ሰላሙ ትግል ማዉራት ትታችሁ ለምን ትጥቅ ትግላችሁ ላይ አታተኩርም ? » ነበር ስንላቸው የነበረው።

http://ecadforum.com/Amharic/archives/11307/

የኢካዴፍ ድህረ ገጽ፡ላይ ቀልቤን የሳበ አንድ መግለጫ አነበብኩ። ግንቦት ሰባት በቅርቡ የወጣ መግለጫ ነው። በመገለጫው ግንቦት ሰባት በይፋ፣ አገር ቤት እየተደረገ ላለው፣ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እዉቅና የሰጠበት ሁኔታን ታዘብኩ። ያ ብቻ አይደለም በአገር ቤት ለሚደረገዉም ሰላማዊ ትግል ያለዉን አጋርነቱንም ገልጿል። 


«ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው የየካቲት 16 ቀን 2006 ዓ.ምን ሕዝባዊ ተቃውሞ ላደራጁና በተቃውሞውም ለተካፈሉ ሁሉ ያለውን አክብሮት ይገልፃል። ሕዝብ ብሶቱን የሚገልጽበት ሕዝባዊ ተቃውሞ ማደራጀትና መምራት መቻል ትልቅ ነገር ነው። ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ወደ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የማደግ እድል አላቸው። ስለሆነም ግንቦት 7 ለባህርዳሩ ሕዝባዊ ተቃውሞ አደራጆችና ተሳታፊዎች “እንኳን ደስ ያላችሁ” በማለት የትግል አጋርነቱን መግለጽ ይሻል። » ሲል ነበር የግንቦት ሰባት መግለጫ ያተተው። 

ወደኋላ ተመልሰን፣ ብዙ ትንተና ማድረግ አስፈላጊ አይሆንም። ግንቦት ሰባት የሰላማዊ ትግል ሊሰራ እንደሚችል ማመኑ፣ ለዚያም አጋርነቱን ማሳየቱ፣ «የሰላማዊ ትግል ይሰራል፣ አይሰራም» እየተባባልን፣ ከግንቦት ሰባቶች ጋር ስናደርግ የነበረው የቃላት ጦርነነት እንዲያበቃ የሚያደርገው ይመስለኛል። 

አሁንም ግንቦት ሰባቶች፣ ከሻእቢያ ጋር መስራታቸው አይመቸኝም። የማታ ማታ እነርሱ እራሳቸው እንደሚጎዱ ማስጠንቀቁን እቀጥላለሁ። የትጥቅ ትግሉን ትተው ሙሉ ለሙሉ ወደ ሰላማዊዉ መንገድ እንዲመጡ እመክራለሁ። የወሰዱትን አቋም «ለምን ወሰዳችሁ ? » ልላቸው ግን አልችልም። የፈለጉትን የማድረግ ሙሉ መብት አላቸውና። ሙሉ ለሙሉ ወደ ሰላማዊው ትግል እንዲመጡ ለማሳመን ፣ ለማግባባት ከመሞከር ዉጭ፣ የኛን አቋም በነርሱ ላይ ልንጭን፣ ለነርሱ እኛ ልንወስንላቸው አንችልም። 

የሚያዋጥን ፍቅር ነው። የሚያዋጣን ችግሮቻችን በሰላምና በዉይይት መፍታታ ነው። የሚያዋጣን የጥላቻና የእልህ ፖለቲካ ሳይሆን የፍቅርና የመቻቻል ፖለቲካ ነው። አንድ ወቅት ዶር ብርሃኑ ነጋ ፣ ያኔ የቅንጀት አመራር የነበሩ ጊዜ የተናገሩትን ላስታወስ። ስለኢሕአዴግ ሲናገሩ «እነርሱ ጠመንጃ አላቸው። ያስራሉ፣ ይገድላሉ። እኛም የራሳችን ሽጉጥ (ኮልት) አለን። ፍቅር የሚባል። በዚያ እናሸንፋቸዋለን» ነበር ያሉት። አዎ፣ ዶር ብርሃኑ ትክክል ነበሩ። ምንጊዜም ፍቅር ያሸንፋል !

No comments:

Post a Comment