BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Monday, 27 January 2014

በአቀንቃኙ ቴዲ አፍሮ ጥቁር ሰው በተሰኘው አልበሙ “ተዋነይ” ተብሎ የሚወደሰው ግለሰብ ማን ነው?


ፈላስፋውና የቅኔውሊቅ ተዋነይ
(By: Biruk Sisay)
ተዋናይ አገሩ ጎጃም ይልማና ወረዳ ቆለላ ምክትል ሲሆን፤ የተወለደበት ደብር ወንደል ተክለሃይማኖት ይባላል። ይህም በጎንጅና በጽላሎ አጠገብ ነው። ሊቁ ተዋናይ የነበረውም በአፄ በካፋ ዘመነ መንግሥት ነበረ። አምላክ ሲፈጥረው ጥበብን ሁሉ ገልፆለታል። አንድም ያስቀረበት ነገር የለም። ሊቃውንቱ እንደሚናገሩትና ታሪክም እንደሚመሰክረው በደመና ተጭኖ አለምን እስከመዞር ደርሶ ነበር። ይህም ይታወቅ ዘንድ ባጭሩ ሀገሩ ጎጃም ጎንጂ ሲሆን፤ ጎንደር በአፄ በከፋ ጊዜ ንጉሡ ግብር አግብተው መኳንንቱን በሚያበሉበትና እሳቸውም ምሳ በሚበሉበት ጊዜ ሁሉ፡ ሊቁ ተዋናይ በ “ዕፀ መሰውር” ከጎጃም እየመጣ ማንም ሳያየው በቦታው በመገኘት ሁልጊዜም ከንጉሱ ጋር ይመገብ ነበር [ንጉሱም ሆነ ማንም ሳያየው የንጉሱን ድርሻ በስውር ይበላባቸው ነበር]። ታዲያ ለንጉሱ የሚሰጠው የተወሰነ ምግብ በመሆኑ ንጉሱም ሳይጠግቡ እየቀሩ ስጡኝም እንዳይሉ...........
ስለሚያፍሩ በረሀብ ሊሞቱ ሆኑ። በጣም ከሱ መነመኑ። በዚህም የተነሳ ሊቃውንቱና መኳንንቱ ከንጉሱ ቀርበው በምን ምክንያት ነው ሰውነትዎ እያለቀ የሄደው? አይበሉም እንዳንል ይበላሉ፤ ታመዋል እንዳንል አልታመሙም ደህና ነዎት፤ ምክንያቱ ምንድን ነው? ብለው ጠየቋቸው።

አፄ በከፋም ነገሩ እያስገረማቸው ከጠየቋቸው ዘንድ፤ ለእኔ የምትሰጡኝ ምግብ አላነሰኝም ነበር፤ ነገር ግን የሚወስደውን [የሚበላውን] ሳላውቀው ያልቅብኛል በዚህ ምክንያት እኔም አልጠግብም ብለው መለሱላቸው። ከዚህ በኋላ ንጉሡ ብዙ ሊቃውንትና ጠቢባን ስለነበራቸው ተመካክረው ጉዳዩን ይከታተሉት ጀመር። ታዲያ ከሊቃውንቱ አንዱ የነበረው አፈነገሥት ውሂብ በረቂቅ ጥበብ የታወቀ ሥለነበር፤ “ዕፀ መክሥት” ይዞ በማዕዱ ጊዜ ሲጠባበቀው ቀርቦ ታጥቆ ከንጉሡ ጋር ሊበላ ሲል ይይዘዋል፡ ለካስ ሊቁ ተዋናይ ኖሯል። ተዋናይም ደነገጠና እንደምንም ብሎ “ዕፀ መሰውሩን” ሰውሮ ፊትለፊት ከንጉሱ እና ከሊቃውንቱ ጋር ማውራት ጀመረ። አፄ በከፋም ሊቁ ተዋነይ ተመልሶ ወደ ጎጃም እንዳይሄድ በአፈ ነገሥት ውሂብ ጠባቂነት እንዲቆይ አደረጉ።

ጎንደር ለተወሰነ ዘመን እንደቆየ ወደ ጎጃም ተመልሶ “ዕፀ ሕይወት” የሚላትን እንጨት እንደምንም ብሎ ተመራምሮና ፈልጎ ካገኘ በኋላ፤ ለዘለዓለም ሕያው ሆኖ ለመኖር ሥለፈለገ በአዲሥ ሸክላ ከዘፈዘፈ በኋላ ከእልፍኝ ገብቶ አንዱን ልጅ በአካሌ አፍስስብኝ አለው። ልጁም የታየውን ነገር አይታወቀምና ደንግጦ ግማሽ አካሉ ላይ አፍስሶበት ግማሽ አካሉ ላይ ሳያፈስበት በመቅረቱ ያልፈሰሰበት አካሉ በድን ሙት ሁኖ ለሰባት አመታት ቆይቶ በሰባት አመቱ ቅኔ በንሰሐ መልከ ለእግዚአብሄር አቀረበ። እግዛብሄርም በሞት አሰናበተው።

ዝክረ ሊቃውንት ከሚል መጥሀፍ [መፅሀፍ] ያገኘሁት።

የኢትዮጵያ ደብተራወችና ደረሳወች ጥበብ በህይወቴ ከሚያስድንቁኝና ከሚገርሙኝ ነገሮች አንድ ነው። ግን ለምንድን ነው ይህን እውቀት ለመማር ትኩረት የማናደርገው? በተለይ ዘመናዊ ትምህርት የቀሰምን እና ዘመናዊነት[አውሮፓዊነት] የተሞላን ሰዎች እስኪ መለስ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ? ይህን ጥበብ [ባህላዊና አገራዊ ዕውቀት] ለማወቅና ለመመርመር ግዴታ ኦርቶዶክስ ወይም ሃይማኖተኛ መሆን እኮ አይጠበቅብንም? ዶግማ[ቀኖና] ከዚህ ጥበብና ዕውቀት ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያንም ብትሆን አርባ ቤተ ክርስትያን ከመደርደር እንዲህ አይነት የጥበብና የዕውቀት ትምህርት ቤቶችን ብትከፍት ምንኛ ባደነቅኳት? በእስልምናውም ቢሆን አገራዊዩንና ባህላዊዩን ጥበብና እውቀት የሚያውቁ፣ የሚመራመሩ ደረሳወችን ማፍራትና ተቋም መፍጠር ተገቢ ነው።

No comments:

Post a Comment