ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን ቁጥራቸው እየበረከተ የመጡት ቀያይ ሲኖትራክ ከባድ መኪናዎች በመንገደኞች ላይ አሰቃቂ አደጋ እያደረሱ ሲሆን ነዋሪዎችም “ቀይ ሽብር” የሚል ቅጽል ስም እንደሰጧቸው ይናገራሉ፡፡
ኮልፌ አካባቢ በ350 ብር ቤት ተከራይታ የምትኖረው የ31 ዓመቷ ማህሌት አሸናፊ፤ በወሲብ ንግድ ነበር የምትተዳደረው፡፡ ቀን ቀን የሁለት ዓመት ልጇን ስትንከባከብ ትውልና ምሽት ላይ ልጇን ለሞግዚት ሰጥታ “ቢዝነስ” ትወጣለች። ማህሌት ቦሌ ሩዋንዳ ከሚኖሩት ወላጆቿ ጋር የተለያየችው በእርግዝናዋ ሳቢያ ነው፡፡ ዘወትር “ቤተሰቤን ያጣሁበት ነው” ለምትለው ልጇ ያላት ፍቅር ልዩ ነው፡፡ ማታ ማታ ለ”ቢዝነስ” ስትወጣ እንኳን እንደሌሎች ባልደረቦቿ አታድርም፡፡ ቢዝነስ ቀናትም አልቀናትም ቢበዛ እስከ ሰባት ሰዓት አምሽታ ልጇ ጋ ትመለሳለች፡፡
ዘንድሮ አዲስ ዓመት ላይ ከወሲብ ንግድ ወጥታ ሌላ ስራ ለመቀጠር የወሰነችውም ለልጇ በማሰብ ነው – “እያደገ ሲመጣ ስሜቱ ይጎዳል” በሚል፡፡ እናም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፈሯ በሚገኝ ካፌ ውስጥ ተቀጥራ መስራት ጀመረች፡፡ .....
ለረዥም ጊዜ አይታቸው ከማታውቀው እናቷ መልዕክት የደረሳትም ይሄኔ ነው፡፡ በጠና መታመማቸውንና ዓይኗን ለማየት እንደጓጉ ሰማች፡፡ የእናትን አንጀት ታውቀዋለችና አላስቻላትም፡፡ ወደ እናቷ ቤት ለመሄድ ተነሳች፡፡ ግን ፍርሃት ፍርሃት ብሏት ነበር፡፡ “ልቤ ፈራ—እናቴ ሞታ እንዳይሆን…” ስትል ስጋቷን ለልጇ ሞግዚት አካፍላታለች፡፡ ከቤት ከመውጣቷ በፊት ልጇን አገላብጣ ሳመችው – ሩቅ አገር እንደሚሄድ ሰው፡፡ ምናልባት እናቷ አርፈው ከሆነ ማደርም ሊኖር ይችላል ብላ ያሰበችው ማህሌት ካፌ ለምትሰራ ጓደኛዋ ልጇን እንድታይለት አደራ ስትላት ለምን ይዘሽው አትሄጅም የሚል ሃሳብ አቅርባላት ነበር፡፡ ማህሌት ግን “ምናልባት ችግር ካለ በእኔ ብቻ ይለፍ” አለችና ወደ እናቷ ቤት ለመሄድ ጉዞ ጀመረች፡፡ዘንድሮ አዲስ ዓመት ላይ ከወሲብ ንግድ ወጥታ ሌላ ስራ ለመቀጠር የወሰነችውም ለልጇ በማሰብ ነው – “እያደገ ሲመጣ ስሜቱ ይጎዳል” በሚል፡፡ እናም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፈሯ በሚገኝ ካፌ ውስጥ ተቀጥራ መስራት ጀመረች፡፡ .....
በተለምዶ 18 ማዞሪያ በሚባለው አካባቢ መንገድ ለመሻገር ቆማ ሳለ፣ ከጦር ሃይሎች አቅጣጫ የመጣ አንድ ሲኖትራክ መንገድ ይስትና ማህሌትንና ሌሎች ሦስት መንገደኞችን ይገጫል፡፡ እሷ ወዲያው ህይወቷ ያለፈ ሲሆን የቀሩት ከባድና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው የፖሊስ መረጃ ያመለክታል፡፡
የ26 ዓመቱ ወጣት ቴዎድሮስ አበራ፤ የ4ኛ አመት ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበር፡፡ ለቤተሰቡ ብቸኛ ልጅ ስለሆነ ወላጆቹ እንደ አይናቸው ብሌን ነው የሚያዩት፡፡ ባለፈው ህዳር አንድ ጠዋት ላይ ነው፡፡ ከዩኒቨርስቲ ጓደኞቹ ጋር የጥናት ቀጠሮ ቢኖረውም መጀመርያ የታመሙትን እናቱን ወይዘሮ እቴነሽ ሳህሉን ወደ ሆስፒታል መውሰድ ነበረበት፡፡ ሳሪስ አዲሱ ሰፈር ከሚገኘው መኖርያ ቤታቸው እናቱን በሃች ባክ መኪና ይዞ ወጣ፡፡ ስለመንገዱ መጨናነቅ ለእናቱ እያወራ ነበር የሚያሽከረክረው፡፡ ዘንባባ ሆስፒታል መታጠፊያ ጋር ሲደርሱ ከፊት ለፊት የሚመጣው ሲኖትራክ ያላማራቸው እናት፤ ልጃቸው ጥግ እንዲይዝ ይነግሩታል፡፡ ጥግ ከመያዙ በፊት ግን ያለአቅጣጫው እየተክለፈለፈ የመጣው ከባድ መኪና፣ ሃች ባክዋን በሹፌሩ በኩል ክፉኛ ገጭቶ ከመንገዱ ውጭ ወረወራት፡፡
የቴዎድሮስ እናት ወ/ሮ እቴነሽ ሳህሉ፤ ሆስፒታል ከገቡ ከረዥም ሰዓት በኋላ ነበር ራሳቸውን ያወቁት። ሲነቁ አንድ እግራቸው ከጥቅም ውጭ ሆኗል። ወዲያው ስለልጃቸው መጠየቅ ጀመሩ፡፡ ማንም እውነቱን ለመንገር አልደፈረም – በድንጋጤ አንድ ነገር እንዳይሆኑ በመፍራት፡፡
አደጋው በደረሰ በአስረኛው ቀን እናት ልጃቸው መሞቱን ተረዱ፡፡ በድንጋጤ ዳግም ራሳቸውን ስተው ለተጨማሪ አስር ቀን እዚያው ሆስፒታል ውስጥ ተኙ፡፡ አሁንም ስለአደጋው ሲያስታውሱ ስቅስቅ ብለው የሚያለቅሱት ወ/ሮ እቴነሽ፤ “ምናለ እኔን ወስዶ ልጄን ቢያተርፍልኝ” እያሉ በቁጭት ይቆዝማሉ፡፡
ህዳር 18 ቀን 2006 ዓ.ም ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት ገደማ ነው፡፡ ሃይሉ አበራና ቴዎድሮስ አበራ የተባሉ ወጣት የጐዳና ተዳዳሪዎች፣ የዘወትር ማረፍያቸው በሆነውና ፒያሳ በሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ደጃፍ ላይ ጐናቸውን አሳርፈዋል፡፡ አቶ አበራ ተሰማ እና አቶ ሞላ አበራ ደግሞ ቤታቸው እዚያው አካባቢ ሲሆን ወደ ስራ ሲሄዱ “ሰላም አውለኝ” ለማለት ጊዮርጊስ ቤ/ክርስቲያን ጎራ ይላሉ፡፡
ውጭ ደጃፉ ላይ እንደቆሙም አንድ ሲኖትራክ ከየት መጣ ሳይባል መንገድ ስቶ አራቱንም ይገጫቸዋል፡፡ ከፖሊስ በተገኘው መረጃ መሰረት፤ ሁለቱ የጎዳና ተዳዳሪዎችና አቶ አበራ ተሰማ ወዲያው ህይወታቸው ሲያልፍ፣አቶ ሞላ አበራ የተባሉት ግለሰብ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በህይወት ተርፈዋል፡፡
የካቲት 1 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ አምስት ሰዓት ገደማ፣ በቦሌ ክ/ከተማ ልዩ ቦታው በሻሌ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አካባቢ አንዲት ባጃጅ፣ ሹፌሩን ጨምሮ ስድስት ሰዎችን ጭና እየተጓዘች ነበር – ዚያዳ አስፋው፣ ብሩክ ሲሳይ፣ ገብርኤላ ሙሉጌታ፣ ክርስቲያን ክፍሉ፤ መንግስቱ ጫፎ እና የባጃጁ ሹፌር። ባጃጇ ከሰሚት ተነስታ ፊጋ ተብሎ ወደጠራው ሰፈር እየተጓዘች ነበር፡፡ የባጃጁ ሹፌር “”ዛሬ ቀኑ ይከብዳል አይደል?” በማለት ባነሳው ወግ መነሻነት ጨዋታው ደርቶ ነበር፡፡ ድንገት ከተቃራኒ አቅጣጫ የመጣው ሲኖትራክ ግን እነሱንም ጨዋታቸውንም በታተናቸው፡፡ በአደጋው ሶስት ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ፣ በሶስቱ ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ ገልጿል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን ቁጥራቸው እየበረከተ የመጡት ቀያይ ሲኖትራክ ከባድ መኪናዎች በመንገደኞች ላይ አሰቃቂ አደጋ እያደረሱ ሲሆን ነዋሪዎችም “ቀይ ሽብር” የሚል ቅጽል ስም እንደሰጧቸው ይናገራሉ፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ ምርመራ ቡድን መሪ፣ ረዳት ሳጅን ቶሎሳ፤ ሲኖትራኮች ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ በየወሩ ከስድስት እስከ ስምንት አደጋዎች እያደረሱ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ረዳት ሳጅኑ ለአደጋው መብዛት እንደምክንያት ከጠቀሷቸው መካከል፤ የሹፌሮች ብቃት ማነስ፣ የተሽከርካሪዎቹ ፍሬን ቶሎ መሞቅ፣ ከተፈቀደላቸው ክብደት በላይ መጫንና በሃሰተኛ መንጃ ፍቃድ ማሽከርከር ይገኙባቸዋል። ሲኖትራኮች የተፈቀደላቸው የጭነት መጠን 132 ኩንታል እንደሆነ የሚናገሩት ረዳት ሳጅኑ፤ አብዛኛዎቹ ግን ከሁለት መቶ በላይ ኩንታል እየጫኑ መንቀሳቀሳቸው ለአደጋው መባባስ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል – ረዳት ሳጅን ቶሎሳ። አንዳንድ የሲኖትራክ አሽከርካሪዎች በበኩላቸው፤ የመኪኖቹ ጥራት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ይናገራሉ። ሲኖትራክ የቻይና ስሪት እንደሆኑ የጠቀሱት ረዳት ሳጅን ቶሎሳ፤ የመኪኖቹን የጥራት ደረጃና አጠቃላይ ይዞታ በተመለከተ ከአስመጪዎቹ ጋር በቅርቡ ውይይት እንደሚካሄድ ተናግረዋል። ሲኖትራክ የተባሉት ከባድ መኪኖች በአብዛኛው ቻይናዎች በተሰማሩባቸው የመንገድና የባቡር ሃዲድ ፕሮጀክቶች ላይ እያገለገሉ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡
Source: Addis admass
No comments:
Post a Comment