BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!
Friday, 31 January 2014
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች አዲስ ማኅበር መሰረቱ
በተለያዩ የሕትመት፣ የብሮድካሰትና የድረገጽ ጋዜጠኞች በጋራ በመሆን “የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ” በሚል ስያሜ አዲስ ማኅበር መሰረቱ፡፡ ሐሙስ ጥር 22 ቀን 2006 ዓ.ም በአስታራ ሆቴል በተካሄደ ጠቅላላ ጉባኤ ማኅበሩን የሚመሩ ሰባት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትና የማኅበሩን ጠቅላላ ጉባኤ የሚመሩ አፈ-ጉባኤ፣ ምክትል አፈ-ጉባኤና ፀሐፊ መርጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ(ኢጋመ) (Ethiopian Journalist Forum) EJF በሊቀመንበርነት ለመምራት ጋዜጠኛ በትረ ያዕቆብ የተመረጠ ሲሆን፤ .......
በምክትልነት ጋዜጠኛ ስለሺ ሐጎስ፣ በፀሐፊነት ጋዜጠኛ ነብዩ ኃይሉ፣ በህዝብ ግንኙነት ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሙሉጌታ፣ በጥናትና ምርምር ጋዜጠኛ ብስራት ወ/ሚካኤል፣ በሒሳብ ሹምነት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ፣ በገንዘብ ያዥነት የገጣሚና ደራሲ በእውቀቱ ስዩም ወንድም የሆነው ጋዜጠኛ ሀብታሙ ስዩም በመሆን ተመርጠዋል፡፡ የማኅበሩ አፈ-ጉባኤ በመሆን የተመረጡት አንጋፋው ጋዜጠኛ አያሌው አስረስ፣ ምክትል አፈ-ጉባኤ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ እንዲሁም በፀሐፊነት ጋዜጠኛ ብሩክ ከበደ ተመርጠዋል፡፡ ለኦዲትና ኢንስፔክሽን ደግሞ ጋዜጠኛ ብዙአየሁ ወንድሙ ተመርጧል፡፡ ከምርጫ ስነ-ስርዓቱ በፊት 14 ገጽ ያለው መተዳደሪያ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱም ላይ የሚሻሻሉ አንቀጾች ላይ ማለትም ስያሜ፣ ዓላማ፣ የተባባሪ አባላት አቀባበልና ማንነት፣ የአባላት መዋጮና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ በምርጫው ስነ-ስርዓት ላይ ከአሜሪካና ከእንግሊዝ ኤምባሲ የተጠሩ ተወካዮች፣ ሀሳብን በመግለፅ ነፃነት ላይ የሚሰሩ አክቲቪሰቶችና የማኅበራትና ኤጀንሲ ተወካይ ተገኝተው የጠቅላላ ጉባኤውን ሂደት ተከታትለዋል፡፡ ምርጫውም ግልፅና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ተጠናቋል፡፡ በቀጣይ ማኅበሩ በርካታ አባላትን በመመልመል አድማሱን እንደሚያሰፋም ተመልክቷል፡፡ ባለፉት አራት ወራትም ማኅበሩን ለመመስረት ከ20 በላይ ስብሰባዎች ተካሂደዋል፡፡
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment