ጥር ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ባለፉት 15 ዓመታት ከኤጀንሲው ፈቃድ የወሰዱ 6ሺህ 500 ፕሮጀክቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ወደሥራ ባለመግባታቸው የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸውን ለመሰረዝ መወሰኑ ታወቀ፡፡ በዚሁ መሠረት 2 ሺህ 500 ፕሮጀክቶች ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ ታውቋል፡፡
ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው የቱርክ፣የሕንድና የቻይና ባለሃብቶች በአገሪቱ በግብርና............
በማኒፋክቸሪንግ እና በአገልግሎት ዘርፎች ለመሰማራት በቅደም ተከተል ፍላጎት እያሳዩ ቢሆንም በተለይ የአውሮፓና አሜሪካ ባለሃብቶች መካከል ብዙዎቹ ፈቃድ ከወሰዱ በኃላ በዚያው የውሃ ሽታ ሆነው የሚቀሩበት ሁኔታ መከሰቱ መንግስትንአሳስቧል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ 51 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 2ሺህ 164 ያህል ፕሮክቶች ፈቃድ የወሰዱ ቢሆንም እስካሁን ወደማምረት ደረጃ የተሸጋገሩት 637 ያህል ፕሮጀክቶች ብቻ እንደሆኑ የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል፡፡
በኢንቨስትመንት ህጉ መሰረት አንድ የውጪ ባለሃብት የኢንቨስትመንት ፈቃዱን ከወሰደ በኋላ በየስድስት ወሩ ለኤጀንሲው ሪፖርት በማድረግ በየአመቱ ደግሞ ፈቃዱን ማደስ የሚጠበቅበት ሲሆን ይህ ካልተሟላ ግን ከሁለት አመታት በኋላ ፈቃዱ ይሰረዛል ይላል፡፡
ይህም ሆኖ ግን ብዙዎቹ ባለሃብቶች መሬት ተረክበው ጭምር ወደ ስራ አለመግባት፣ሳያሳውቁ ዘርፍ መቀየር፣መሬት በመሸጥ በመለወጥ፣ከመንግስት ባንኮች ተበድሮ በመሰወር ወንጀሎች ውስጥ ጭምር መገኘታቸው የኤጀንሲው መረጃ ይተነትናል፡፡ መንግስት በሁለት ዓመት ውስጥ ፈቃድ መሰረዝ ቢችልም ከ10 ኣመታት በላይ ብዙዎቹን መታገሱን መረጃው ጠቁሞ ከዚህ በላይ መታገስ ስለማይቻል ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ መወሰኑና ከዚህም በሃላ እንዲህ ዓይነት የማስታመም ዕድል እንደማይሰጥ ዝቷል፡፡
ብዙዎቹ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ከወሰዱ በሃላ እንደመሬት፣የባንክ ብድር የመሳሰሉ ጉዳዮችን ለመፈጸም ከፍተኛ መንገላታት እንደወሰደባቸው፣ ለፕሮጀክት ያሰቡትን በጀት ለጉቦ ጭምር ለመክፈል መገደዳቸውን በየጊዜው በመግለጽ ቅሬታቸውን ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን ጥቂት የማይባሉትም በመሰል ችግሮች ከስረው ወደአገራቸው መመለሳቸው፣አንዳንዶቹም ወደኬንያና ኡጋንዳ ለመሄድ መገደዳቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት የህንድ እና የቻይና ባለሃብቶች ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በመሞዳሞድ በተለይ በብዛት በተሰማሩባቸው በግብርና፣ በማኒፋክቸሪንግ፣በመንገድ ግንባታ፣ በቴሌኮም እና በኤሌክትሪክ ሃይል ዘርፎች ከፍተኛ ህገወጥ ጥቅም እያገኙ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
No comments:
Post a Comment