BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Friday, 31 January 2014

አትውረድ


ዳንኤል ክብረት


አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በዋናው በር በኩል ወደ አውራ ጎዳናው ይወጣል፡፡ ጥቂት እንደተጓዘ ደግሞ እዚያ አካባቢ ቆመው አላፊ አግዳሚውን ከሚላከፉ ጎረምሶች ጋር ይጨቃጨቃል፡፡ ጭቅጭቁ በምን እንደተጀመረ ማናችንም አላወቅንም፡፡ እነዚያ ጎረምሶች ግን በመምህሩ ላይ ‹ሙድ› ይዘውበታል፡፡ ‹እሺ - - ሊቁ› እያሉ በስድብ ጠረባ ይረፈርፉታል፡፡ እርሱ ደግሞ ስድቡን አልቻለበትም፡፡ ‹‹ያልተማራችሁ፣ ማይሞች፣ ከስድብ በቀር ሌላ የማታውቁ፣ ደደቦች›› ይላል ሥሩ እስኪገታተር ድረስ በቁጣ፡፡ በትከሻው ያንጠለጠለው ቦርሳ ይወዘወዛል፣ መነጽሩም ልውደቅ ልውደቅ ይላል፡፡..............
‹‹እሺ ሊቁ፣ ለምን ላፕቶፕሺን ከፍተሺ ዕውቀት አትጭኝብንም›› እያሉ ጎረምሶቹ ይሳሳቁበታል፡፡እርሱ ይበግናል፡፡ ‹ኤፍ ብቻ ነው እንዴ ቦርሳሽ ውስጥ የያዝሺው፤ በናትሺ አንድ አምስት ኤ የለሽም›› ይሉታል፡፡ እርሱ ይንዘፈዘፋል፡፡ ‹‹አንድ ሁለት ኤ ብትሰጭን ቸብ አርገን በርጫ እንገዛበት ነበር›› ይሉታል፡፡ ሰው እየተሰበሰበ፣ እየከበበው ይሄድና የጎረምሶቹን ስድብ እንደመዝናኛ ቆጥሮት አብሯቸው ይሳሳቃል፡፡ እርሱን ኮሜዲ ፊልም እንደሚሠራ ተዋናይ ቆጥረውት በነጻ ይኮመኩማሉ፡፡ ጎረምሶቹ አንድ ተረብ በወረወሩ ቁጥር ከብቦ የተሰበሰበው ‹አስገቡለት› እያለ እንደ ጎጃም ልቅሶ ያጅባቸዋል፡፡ 
 እየቆየ ከበባው እየሰፋ፣ ሳቁ እየደራ፣ የመምህሩ ንዴት ወደ እሳተ ገሞራነት እየተቀየረ ሄደ፡፡ መምህሩ ከዚያ ከበባ ልውጣ ቢል እንኳን ሰው በጎረምሶቹ ተረብ ስለተዝናና በቀላሉ የሚያስወጡት አይመስልም፡፡ የተከፈለው አዝማሪ መስሏል፡፡ የሚያውቃቸው ስድቦች አልቀውበት አሁን ጣቱን ማውጣትና ‹‹አሳይሃለሁ›› እያለ መዛት ጀምሯል፡፡ የአንዳንድ የእንግሊዝኛ ስድቦችን ሲሳደብም
የኛ ሙሽራ ኩሪባቸው
በእንግሊዝ አናግሪያቸው›› ብለው ሳቁበት፡፡ በልቡ አንዳች የፖሊስ ኃይል መጥቶ እንዲገላግለው እየተመኘ ነበር፡፡ ወደ ስድቡ ሜዳ አስቦ ስላልገባ አስቦ ሊወጣ አልቻለም፡፡
በዚህ መካከል በግራ እጃቸው ጋዜጣ አጣጥፈው የያዙ አንድ አዛውንት ሁላችንንም እየገፈተሩ፣ እንደ ሙሴ የሕዝቡን ባሕር ለሁለት እየከፈሉ ወደ መካከል መጡና ያንን መምህር እጁን ይዘው በዝምታ ጎትተው ከከበባው አወጡት፤ ጎረምሶቹም ‹ሼባው ልቀቀው እንጂ›› እያሉ ተረቧቸው፡፡ እርሳቸው ቀናም አላሉ፣ መልስም አልሰጡ፡፡ እየሰነጠቁ እንደገቡ፣ እየሰነጠቁ ወጡ፡፡
ከዚያም ወደ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መታጠፊያ ዘወር አደረጉትና ‹‹ለምን ልጄ፣ ለምን?›› አሉት፡፡
‹‹ከዩኒቨርሲቲ ስወጣ ለከፉኝ፣ እኔም መልስ ሰጠኋቸው››
‹‹ተማሪ ነህ?››
‹‹የዩኒቨርሲቲ መምህር ነኝ››
‹‹እና መምህር ሆነህ ነው ከእነርሱ ጋር ስድብ የገጠምከው፤ ጥፋተኛው አንተ ነህ›› አሉት፡፡ እኛ ትንሽ ራቅ ብለን የሚሉትን መስማት ጀመርን፡፡
‹‹ተመልከት እዚያ›› አሉት በአመልካች ጣታቸው ወደ አንበሳ ግቢ አቅጣጫ እያመለከቱ፡፡ ‹‹እዚያ ግቢ ውስጥ ምን አለ?›› አሉና ጠየቁት፡፡
‹‹አንበሳ ነዋ››
‹‹አንበሳ ግን መኖሪያው ግቢ ውስጥ ነው እንዴ?››
‹‹አንበሳማ የዱር እንስሳኮ ነው፤ ምን ዓይነት ጥያቄ ነው የሚጠይቁኝ፤ የዩኒቨርሲቲ መምህር ነኝ እያልኩዎ›› መምህሩ ተናደደና ጥሏቸው ሊሄድ ከጀለ፡፡ እርሳቸውም ከእናቱ ጋር መንገድ እንደሚሻገር ሕጻን እጁን አጥብቀው ያዙት፡፡ ‹‹ወዳጂ፣ ሰው በሁሉም ነገር ሊቅ አይሆንም፡፡ በአንዱ ሊቅ ሲሆን በሌላው ማይም ነው፤ በአንዱ መምህር ሲሆን በሌላው ተማሪ ነው፤ በአንዱ ጎበዝ የሆነ ለሌላው ሰነፍ ነው›› አሉት፡፡ ትንሽ ቀዝቀዝ አለ፡፡
‹‹አንበሳው በገዛ ጫካው ውስጥ ቢሆን ኖሮ ማን ይደፍረው ነበር? ማን ጀግና ነበር ሃምሳ ሳንቲም ከፍሎ በሃምሳ ሜትር ርቀት የሚያየው? ማን ጀግና ነበር ቀርቦ ፎቶ የሚያነሣው? ማን ጀግና ነበር ከአንበሳው ጋር ፎቶ ሲነሣ የሚውለውጫካው የእርሱ ክልል ነው፤ የእርሱ ሠገነት ነው፡፡ እዚያ የቀለበቱ ጌታ (Lord of the Ring) እርሱ ነው፡፡ ከተማው ግን የአንበሳ መደብ አይደለም፣ እርሱ ለከተማ አልተፈጠረም፣ ከተማውን አይችልበትም፤ በግቢ ውስጥ መኖር፣ በአጥር መከለል፣ ከአንበሳው ተፈጥሮ ውጭ ነው፡፡ ስለዚህ ከሚያውቀው ወደማያውቀው፣ ከሠገነቱ ወደ ባርነቱ፣ ከሚያሸንፍበት ወደሚሸነፍበት፣ ከሚችልበት ወደማይችልበት፣ አወደርነውና፤ በከተማ፣ ግቢ ውስጥ አሥረን እንደልባቸውን እንጫወትበታለን፡፡ አሁን የሚፈልገውን አድኖ ሳይሆን የምንሰጠውን ይበላል፣ በፈለገው ሰዓት ሳይሆን በሰጠነው ሰዓት ይመገባል፣ ወደፈለገው ቦታ ሳይሆን ወደፈለግነው ቦታ ይሄዳል፣ የፈለገውን ሳይሆን የፈቀድንለትን ብቻ ያያል፡፡ ለምን? ወደኛ ሜዳ አውርደንዋላ፣ ሜዳውን ትቶ መጥቷላ፤››
ዝም አሉና ቀና ብለው አዩት፡፡ ቦርሳውን ወደ ላይ ገፋ ገፋ እያደረገ ይመለከታቸዋል፡፡ እኛም መጨረሻውን ለማወቅ ጓጉተን አፍጠን እናያቸዋለን፡፡ ስድብና ድብድብ ለማየት ተሰብስቦ የነበረው ሰውም ነገሩ ዕውቀትና ቁም ነገር ሲሆንበት ጊዜ ቀስ በቀስ ‹‹ሼባው ነገሩን ትምሮ አደረጉት›› እያለ ከአካባቢው ሸሸ፡፡ ‹‹የሚቧቀሱ መስሎኝ ነበር፤ ሼባው አበላሸው፡፡ ስድድቡ ተመችቶኝ ነበር ›› እያሉ በቁጭት ጥለዋቸው ሄዱ፡፡
‹‹አንተም እንደ አንበሳው ሆንክ›› አሉ ሽማግሌው፡፡ ወረድክ ከመደብህ፣ ከምትችለው የዕውቀት ክርክር ሜዳ፣ ከምታሸንፍበት የሃሳብ ክርክር ሜዳ፣ ከለመድከው የጥናት ክርክር ሜዳ፣ ወረድክላቸው፡፡ ጎበዞች ናቸው ደግሞ አድንቃቸው፡፡ አወረዱህና በሚችሉት ሜዳ ላይ በደንብ አድርገው ቀጠቀጡህ፡፡ አንተም ሞኝ ነህ በማታውቀው ሜዳ ላይ ትግል ገጠምክ፡፡
‹‹ሶምሶን ከፍልስጤማውያን ዐቅም በላይ ሲሆንባቸው፡፡ ፍልስጤማውያን ምን አደረጉ? በደሊላ በኩል ሶምሶን ወደማይችለው እነርሱ ግን ወደሚችሉት ሜዳ አወረዱት፡፡ በሚችሉት ሜዳ አውርደው ደኅና አድርገው ቀጥቅጠው ያንን ኃያል ሰው ወፍጮ ፈጭ አደረጉት፡፡
‹‹ብልጥ ከሆንክ አትውረድ፣ ጀግና ከሆንክ የወረዱትን አውጣቸው፡፡አሁን አሁን ብዙ ሰው በዚህ እየተሸነፈብን ነው፡፡ እስኪ ጋዜጣውን፣ መጽሔቱን፣ ፌስ ቡኩን፣ ሰልፉን፣ የፖለቲካ ክርክሩንም ተመልከተው፡፡ ብዙዎቹ ከሜዳቸው ወርደዋል፡፡ ብልጦቹ ከፍ ወዳለው ሃሳብ፣ ዕውቀት ወደሚጠይቀው ክርክር፣ በመረጃና በማስረጃ ወደሚደረገው ውይይት፣ ላቅ ወዳለ ትግል፣ ወደ ልዕልናና ወደ ሠለጠነ አስተሳሰብ ማደግ እንደማይችሉ ያውቁታል፡፡ በዕውቀትና በሃሳብ ክርክር፣ በሠለጠነና ደርዝ ባለው ትግል፤ ማንበብን፣ ማወቅን፣ መመራመርን፣ በሚጠይቅ መሥመር መጓዝ፣ ተጉዘውም ማሸነፍ እንደማይችሉ ያውቁታል፡፡ ስለዚህ አንተን መሰል ሰዎችን ወደ ሜዳቸው ‹ውረድ እንውረድ› ብለው ያወርዷችኋል፡፡ በእነርሱ አጀንዳ፣ በእነርሱ ዐቅም፣ በእነርሱ ተራ ነገር፣ በእነርሱ አሉባልታ፣ በእነርሱ ስድድብ፣ በእነርሱ ጠባብነትና ጎጠኝነት፣ በእነርሱ ወንዘኛነትና መንደርተኛነት፣ በእነርሱ ተረብ ይገጥሟችኋል፡፡ ከዚያም ያሸንፏችኋል፡፡ አሁንማኮ ሁላችንንም አወረዱን፣ እንደነርሱ እንድናስብ፣ እንደነርሱ እንድንጽፍ፣ እንደነርሱ እንድንደራጅ፣ እንደነርሱ እንድንናገር፣ እንደነርሱ እንድንዘፍን፣ እንደነርሱ እንድናምን፣ እንደነርሱ እንድንለብስ አደረጉንኮ፡፡

አትውረድ ልጄ፣ ዕውቀት ዋጋ ወደማታገኝበት፣ ሃሳብ ልዕልት ወደማትሆንበት፣ ችሎታ ወደሚያስቀጣበት አለማወቅ ወደሚያስከብርበት፣ ማይም አለቃ ወደሆነበት፣ ክርክር ተረብ ወደሆነበት፣ ውይይት እንደ ኮካ ኮላ ጠርሙስ አንድ ዓይነት ወደሆነበት፣ አላዋቂዎች ወደሠለጠኑበት፣ ከብት ካለው ይልቅ አፍ ያለው ወደተሾመበት ሜዳ አትውረድ፡፡ ከወረድክ ግን በማታውቀው ሜዳ፣ በማታውቀው ስልት፣ በወረደ ትግል ይደበድቡሃል፡፡ አትውረድ ልጄ፡፡ አትውረድ፡

No comments:

Post a Comment