ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራው፣ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር
የምርጫ 97ን ቀውስ ተከትሎ ወደ እስር ቤት ከገቡት የቀድሞዎቹ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ (ቅንጅት) አመራሮች መካከል አንዱ የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሺፈራው፣ በቅርቡ የአንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡ ስለአዲሱ ሊቀመንበርነታቸው፣ ስለመጪው ዓመት ምርጫና ሌሎች ጉዳዮች ነአምን አሸናፊ አጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አንድነት የወጣቶች ፓርቲ ነው ይባላል፡፡ ነገር ግን አመራሩ ላይ ወጣቶች አይታዩም በማለት የሚተቹ አሉ፡፡ የእርስዎን ዳግም ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥንም እንደ ምሳሌ ያነሱታል፡፡ ለምንድነው ወጣቶች ወደ አመራር የማይመጡት?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ይህንን ጥያቄ መጠየቅ ያለባቸው መራጮች ናቸው፡፡ መራጮችንና የአንድነት አባላትን መጠየቅ ነው፡፡ በመሠረቱ አንድነት የወጣቶች ፓርቲ ነው፡፡ ባለፈው ሥራ አስፈጻሚም ሆነ በብሔራዊ ምክር ቤቱ የወጣቱ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው ሰባ በመቶ አካባቢ ወጣት ነው፡፡ የተወዳደርኳቸው ሰዎችም ወጣቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህ ነገር መጠየቅ ያለባቸው አባላትና ጉባዔው ናቸው፡፡
መጠየቅ ያለበት እኔ ፍላጎት ኖሮኝ ወጣቶችን ወደታች ገፍቼ ድርጅታዊ ሥራ ሠርቼ ብመጣ ኖሮ ነበር፡፡ ወጣቶችን ወደታች ተጭነሃል ማለት ይቻል ነበር፡፡ ዋናው ማየት ያለብን ጠቅላላ ጉባዔውና አጠቃላይ ሒደቱ ዲሞክራሲያዊ ነበር ወይስ አልነበረም ነው፡፡ በእኔ ግምት አንድነት ፓርቲ ለዲሞክራሲያዊ አሠራር ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ፓርቲዎች የሚበልጠው ያለ አይመስለኝም፡፡ ለዚህም የምገልጸው በምክር ቤታችንም በሕገ ደንባችን መሠረት የምንሰበሰበው በሦስት ወር አንዴ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ግን በዓመት እስከ 20 ጊዜ ይሰበስባል፡፡ ምክንያቱም የጀመርነውን አጀንዳ በምናደርገው ሰፊ ውይይት መጨረስ አንችልም፡፡ አጀንዳ ጨርሰን አናውቅም፡፡ አራት አጀንዳዎች ቀርበው እንደሆን ሁለቱን ጨርሰን ሁለቱን ደግሞ ለሚቀጥለው ጊዜ እናስተላልፋለን፡፡ ይህ ደግሞ የዲሞክራሲያዊ ውይይት ነፀብራቅ ነው፡፡
እኔ እንዲያውም ቅስቀሳ አላደረግኩም፡፡ የእኔ ተወዳዳሪዎች ቅስቀሳ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ ምርጫው ዲሞክራሲያዊ ነው ወይም አይደለም? የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ነበር፡፡ ለምን ወጣቶች አልመጡም ለሚለው የእነሱ ምርጫ ነው፡፡ እኔ በአብዛኛው የተመረጥኩት በወጣቶች ነው፡፡ ምናልባት ከዚህ በፊትም እንዳደረግኩት ወጣቶችን የማሳተፍ አመለካከትና ባህሪ አለኝ፡፡ እኔ አመራር በነበርኩበት ጊዜ በሕገ ደንቡ መሠረት በሥራ አስፈጻሚ 13 አባላት ነው የሚኖሩት፡፡ እኔ ግን ወጣቶች ወደፊት እንዲቆጠሩ ስድስት አባላት ድምፅ የመስጠት ሥልጣን ሳይኖራቸው አስገብቻለሁ፡፡ ደንቡ ስለማይፈቅድልኝ ነው እንጂ ባለድምፅ ሆነው መግባት ይችሉ ነበር፡፡ ደንቡ ግን አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ ድምፅ አልባ ከመሆናቸው በስተቀር ሙሉ በሙሉ የአመራር አባል ነበሩ፡፡
አቶ ግርማ ሰይፉም የዚያ አባል ነበሩ፡፡ ሌላው ወጣቱን ለዚህ ቦታ ማንም አልከለከለውም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተሳሳተ አመለካከት አለ፡፡ ሜካኒካል ይሆናል፣ ኮታ ይሆናል፡፡ ወጣቶች መምጣት አለባቸው፡፡ የኮታ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህ የመብት ጉዳይ ነው እንጂ የሚሰጣቸው ስጦታ አይደለም፡፡ ስለዚህ በአንድነት ፓርቲ ለወጣቶችም ሜዳው ክፍት ነው፡፡ ነገ ጠዋት የላቀ ከመጣ ምክር ቤቱ በወጣት ሊተካ ይችላል፡፡ ከፖለቲካም አንፃር መታየት ያለበት ስብጥሩ ነው፡፡ ከወጣቶችም፣ ከጐልማሶችም፣ ከአዛውንትም ያ ስብጥር ነው መሆን ያለበት፡፡ ወጣትም ሆኖ ሽማግሌም ሆኖ የራሱ የሆነ ችግር አለበት፡፡ ያንን የሚያቻችለው መቀላቀሉ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተቃዋሚውም ሆነ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያሉት የ60ዎቹ ትውልድ አባላት አመራርነት የሚያበቃውና ወጣቶች በሰፊው ወደ መሪነት የሚመጡት መቼ ነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- በእኔ በኩል በአመዛኙ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ የ60ዎቹ ትውልድ ፖለቲካ የሚለው አይሠራም፡፡ ባለፈው አላየነውም አሁንም አይታይም፡፡ የአንድነት ዕድሜ ስድስት ዓመት ነው፡፡ በስድስት ዓመት ጊዜ ውስጥ አራት ፕሬዚዳንቶችን ለውጧል፡፡ የመጀመሪያዋ ብርቱካን ሚደቅሳ ነበረች፡፡ የወጣቶች ተወካይ ነበረች፣ የ60ዎቹ አይደለችም፡፡ ከዚያ እርሷ ስትታሰር እኔ ተጠባባቂ ሆኜ ኃላፊነቱን ተረከብኩ፡፡ ከዚያ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሆነ፣ አሁን እኔ መጣሁ፡፡ ማንም ፓርቲ በስድስት ዓመት ውስጥ አራት ፕሬዚዳንት የቀየረ የለም፡፡ ይህ የሚያሳየው የአንድነትን ዲሞክራሲያዊነት ነው፡፡ በመሠረቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቃት ባለው ከ60ዎቹ በኋላ ባለው ትውልድ መተካት አለበት፡፡ ያ የእኔ እምነት ነው፡፡ የ60ዎቹ ፖለቲከኞች መጪውን ትውልድ አብቅተው መተካት እንዳለባቸው እምነቴ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን አንድነትን እንደ ምሳሌ ከወሰድነው መጀመሪያ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ወጣት መሪ ነበሩ፡፡ ከዚያ እሳቸው ሲታሰሩ እርስዎ መሪ ሆኑ፡፡ ቀጥሎ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አሁን ደግሞ ተመልሰው እርስዎ መጡ፡፡ በአንድነት ውስጥ ከወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ውጪ ያው የ60ዎቹ ትውልድ አባላት ስለሆናችሁ ከዚያ አንፃር ለማለት ፈልጌ ነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ትክክል ያልሆነ ምዘና ነው፡፡ ምንድነው የ60ዎቹ ፖለቲከኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ስብጥሩን ነው ማየት ያለብን፡፡ ብርቱካን በነበረችበት ጊዜም ሆነ አሁን ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ የነበሩ ግለሰቦች ጥቂት ናቸው፡፡ ምናልባት በጣት የሚቆጠሩ [እኔ፣ ነጋሶ፣ አስራት]፡፡ ነገር ግን ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ የነበሩት አብላጫዎቹ ከ60ዎቹ በኋላ የመጡ ትውልዶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ብሔራዊ ምክር ቤት ውስጥ ከ35 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉት 72 በመቶ ናቸው፡፡ የ60ዎቹ አሉበት፡፡ ነገር ግን በአብላጫው ወጣቶች ናቸው፡፡ በእኔ ካቢኔ ውስጥ የ60ዎቹ ትውልድ ያለነው ሁለት ሰዎች ነን፡፡ ከ15 ሰዎች አንድ ሰው የ60ዎቹ ሆኖ ላይ ስለተቀመጠ የ60ዎቹ ተፅዕኖ አለ ለሚባለው ምዘናው ትክክል አይመስለኝም፡፡ መታየት ያለበት ይዘቱ ነው፡፡ የ60ዎቹ ትውልድ አባላት እንዲያውም የት እንዳሉ ግራ ይገባኛል፡፡ አንዳንድ ቦታ መሪ ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ የፓርቲው መዋቅር መፈተሽ ካለበት የ60ዎቹ የፖለቲካ ተሳፊዎች ወጥተው ዳር የቆሙ ይመስለኛል፡፡ ደግሞም የተፈጥሮ ሒደት ነው፣ የፖለቲካም ሒደት ነው፣ የታሪክም ሒደት ነው፡፡ መታየት ያለበት የግለሰቦች የ60ዎቹ ትውልድ መሆን ሳይሆን ስብጥሩ ውስጥ ስንት አሉ የሚለው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን እንደ አዲስ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው መጥተዋል፡፡ ለፓርቲው ምን አዲስ ነገር ይዘው መጡ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- እኛ ፓርቲያችንን የምንመራው በሥርዓት ነው፡፡ ፓርቲው በ2002 ዓ.ም. የስትራቴጂ ዶክመንቱንና የአምስት ዓመት ዕቅዱን በመጽሐፍ መልክ አውጥቶታል፡፡ የአነድነት ፓርቲ መሠረታዊ ራዕይና ግብ በዚያ ውስጥ ነው የሚታየው፡፡ እዚያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ነው ሁላችንም በቀጣይነት እየገነባን የምንሄደው፡፡ ነገር ግን በ2002 እና በ2003 ዓ.ም. ያወጣነው የስትራቴጂ ግንባታ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር መዛመድ አለበት፣ መቀነባበር አለበት፡፡ ስለዚህ በዚያ መንገድ አንዳንድ ለየት ያሉ ሙከራዎች አካሂዳለሁ፡፡
የመጀመሪያው ሙከራዬ አንድነት ምናልባት ካሉት ፓርቲዎች በጉልህ ጠንክሮ የሚታይና መዋቅሩ ታች ድረስ የወረደ ነው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እንዲያው እንደ ሌላው ጉልበት ወይም አቅም አለን ባንልም በቂ የመንቀሳቀስ ችሎታ አለን የሚል ግምት አለኝ፡፡
ይህንን የአመራር መርህ ከአንድነት አቅምና ሕዝባዊ ገጽታ አንፃር የተለየ (Rebranding) እንዲሆን አደርጋለሁ፡፡ ለምሳሌ አንዱ ያደረግኩት ሥራ አስፈጻሚውን በአብዛኛው ወጣትና አዲስ ነው ያደረግኩት፡፡ በትምህርታቸው ብቁ የሆኑ ናቸው፡፡ በትምህርት ብትሄድ አሁን ከ15 ሰዎች ስድስቱ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡ ሰባቱ የመጀመርያ ዲግሪ አላቸው፡፡ ሁለቱ ደግሞ ዲፕሎማ አላቸው፡፡ አሁን ይኼ አዲስ ምልክት (New Branding) ነው፡፡ ሁለተኛ እነዚህን ሰዎች ስመድብ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ችሎታ እንዲኖራቸው አንዱ መሥፈርት ነበር፡፡ አሁን ዘመኑ ወደዚያው እያመራ ነው፡፡ ስለዚህ በኢንፎርሜሽን ግንኙነታችን ከውጭው መረጃ እኩል አንድነት መራመድ አለበት፡፡
ሌላው ትኩረት የምሰጠው ወጣቶችን የማብቃት ሥራ ነው፡፡ ወጣቶች በቅተው ፓርቲውን እንዲመሩ አደርጋለሁ፡፡ አሁን እኔ እዚህ ሆኜ ወጣቶችን ነው ወደፊት እንዲሮጡ የማደርገው፡፡ ይህን ካደረግኩ በኋላ በእኔ እምነት ክርክርም መካሄድ አለበት፡፡ እስካሁን የተካሄደው የተቃዋሚ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ውጤት አላስገኘም፡፡ ይኼ ምንም የምንክደው አይደለምና ይህ ለምንድን ነው የሚለው ብዙ ጊዜ ይረብሸኛል፡፡ ወይ ማቆም አለብን ወይ መሥራት አለብን፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተበጣጠሱ ዘጠና ፓርቲዎች አሉ፡፡ ከዘጠናዎቹ ደግሞ ጉልህ የሆኑት አሥር አይሆኑም፡፡ አሥሩም አብረው መሥራት አልቻሉም፡፡ በጥምረትም በግንባርም አልተቻለም፡፡ ለምንድን ነው? ለአሥሩም ቢሆን አሥር መሪዎች አሉ፣ አሥር ፕሮግራሞች አሉ፡፡ አሥሩም እንግዲህ አሥር መሪ ኖሮዋቸው ፖለቲካ ይመራሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስለዚህ በብሔራዊ ምክር ቤትና በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ አስገኛለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡
በእኔ እምነት እንግዲህ አንድነት ፓርቲ ግንባርና ጥምረት ውስጥ አይገባም፡፡ ወደ ውህደት አንድ አመራር አንድ ፕሮግራም ወዳለው እንቅስቃሴ እንገባለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ የእኔ ሐሳብ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስብሰባ ላይ ፈንጥቄያለሁ፡፡ ይህ መሆን አለበት፡፡ የተጀመሩት ውህደቶች በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ማለቅ አለባቸው ብሎ ጠቅላላ ጉባዔው ወስኗል፡፡ ወይ እንዋሀዳለን ወይ እንለያያለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ሁኔታ አንድ የማየው እስከ 2007 ዓ.ም. ወይም በዚህ ዓመት ለእኔ የውህደት ዓመት ነው ብዬ የምገምተው፡፡ ወይ እንዋሀዳለን አለበለዚያ በሰላም ተለያይተን ሁላችንም ጉልበታችንን በየአካባቢው በትብብር እናጠናክር የሚል አመለካከት አለኝ፡፡
ይህን ካደረግኩ በኋላ ከኢሕአዴግ ጋር ገንቢ ግንኙነት (Constructive Engagement) እንዲኖረን እፈልጋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጥላቻ ፖለቲካ ማብቃት አለበት፡፡ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን የሚያያቸው እንደ ጠላት ከዚያም አልፎ እንደ ሽብርተኛ ነው፡፡ ይኼንን ነገር ለሚያስብ ሰው እኮ በጣም ነው የሚያስደነግጠው፡፡ በእኛም በኩል ኢሕአዴግን የምናየው እንደ አውሬ ነው፡፡ ምናልባት የሠራውን ሥራ ሁሉ ዋጋ (Credit) ያለመስጠት አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካችን ኢሕአዴግን መቃወም ብቻ ሆኖአል፡፡ ያ መቆም አለበት፡፡ ትልቁ ኳስ ያለው ኢሕአዴግ ዘንድ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ወደፊት በማደርገው እንቅስቃሴ ገንቢ ግንኙነት አድርገን ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር ለሁላችንም እኩል ማድረግ አለበት፡፡ ኢቴቪ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ ለምንድነው የኢሕአዴግ ብቻ የሚሆነው? መብት እኮ አለን፡፡ ለኢቴቪ ደብዳቤ ጽፈናል፡፡ የጻፍነው ምንድነው የኢሕአዴግን ኮንፈረንስ ከባህር ዳርና የኢሕአዴግን ብሔራዊ ምክር ቤት በቀጥታ ስታስተላለፉ ነበር፡፡ የእኛን ግን አልዘገቡም፡፡ ለኢሕአዴግ 99 በመቶ ሰጥተው ለእኛ ግን አንድ በመቶ እንኳን አይሰጡንም፡፡ ይኼ ሁሉ ቁልጭ አድርጐ የሚያሳየው የኢሕአዴግን ድክመትና ስህተት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ለብዙ ፓርቲዎች የእንዋሀድ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቀደም እንደታየው ብዙ ውህደቶች ምርጫ ሲደርስ ከመሰባሰብ በዘለለ ብዙም ሲገፉበት አይስተዋልም፡፡ የ97ቱን ቅንጅት ማስታወስ ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን እርስዎ የሚያቀርቡት ሐሳብ በምን ይለያል? ከዚህ ቀደም ተሞክረው እንደከሰሙት እንደማይሆንስ ማረጋገጫው ምንድነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- የቅንጅት ራሱን የቻለ ጉዳይ አለው፡፡ ቅንጅት አልተዋሀደም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ቅንጅት ግንባር ደረጃ አልደረሰም የሚባለው፡፡ ለቅንጅት ከፍተኛውን ድቀት ያስከተሉት የኢሕአዴግና የቅንጅት መሪዎች ናቸው፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ ያልጠበቀው የፖለቲካ አድማስ ነው የመጣበት፤ በ97 ምርጫ አልጠበቀውም ነበር፡፡ አራቱ ፓርቲዎች ማለትም መኢአድ፣ ኢዴፓ፣ ቀስተ ደመናና ኢዴሊ ሆነው ቅንጅት የተመሠረተው ኅዳር ላይ ነበር፡፡ ኅዳር ላይ ተመሥርተን ግንቦት ላይ ነው ከፍተኛ ዕርምጃ ያሳየነው፡፡ ያ ሁኔታ ኢሕአዴግ ያለውን ግምት በጣም ነው ያዛባው፡፡ ኢሕአዴግ አቅም አይፈጥሩም የሚል ግምት ነበረው፡፡ ገና ስንፈጠር በምርጫው አካባቢ አዲስ አበባን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠርን፡፡ የምርጫው ዕለት ምሽት በአጠቃላይ የምርጫው ሒደት ተናጋ፡፡ በዚያ ምክንያት ቅንጅት ከፍተኛ ውድቀት ውስጥ ገባ፡፡ ኢሕአዴግ ትኩረት አደረገብን፡፡
በዚያ ምክንያት እኛም ወደ እስር ቤት ገብተን ከዚያ ደግሞ ወጣን፡፡ ያው ነገሩ ትክክል ስላልነበር መውጣት እንደነበረብን እኔ አምናለሁ፡፡ ከወጣን በኋላ ደግሞ እኛ አንድ መሆን አልቻልንም፡፡ በእስር ቤት ውስጥ ብሶት ተፈጠረ፡፡ እንደገና ቅንጅትን ለአቶ አየለ ጫሚሶ ሰጡት፡፡ በዚያ በዚያ በመካከላችን ችግሩን በሰከነ ሁኔታ ለማራመድ አልቻልንም፡፡ በዚህ በኩል የራሱ የኢሕአዴግም የእኛም ድክመት ነበር፡፡ ከዚያ በፊትም በተፈጠሩት ስብስቦች እንደዚሁ የመሪዎች ብዛት ነው ችግሩ፡፡ አሁን እኔ የምለው ውህደት ከሆነ አንድ መሪ ሊኖር ይችላል፡፡ ውህደቱም መፈጸም ያለበት በዲሞክራሲያዊ መርሆዎች መሆን አለበት፡፡ ውህደት ላይ ዲሞክራሲያዊ ባህል መፍጠር አለብን፡፡ አመራር አንድ መሆን አለበት፡፡ ሕግ፣ ሥነ ሥርዓትና ደንቡ መታየት አለበት፡፡ እናም ዲሲፕሊን ሊኖረን ይገባል፡፡ የባህሪ ለውጥም ያስፈልገናል፡፡ ከዚህ አንፃር አንደኛ እኛ አመራሮች የባህሪ ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ያ እስከሆነ ድረስ እኔ ውህደት ይወድቃል ብዬ አላስብም፡፡ አልተሞከረም፡፡ በተጨባጭ ብሔራዊ ዕይታ ያለው ውህደት እኮ እስካሁን አልተካሄደም፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ከውህደቱ ጋር በተያያዘ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይስ እንዴት ነው የሚታየው? ብሔራዊ የሆነ ፓርቲ ይኖራል፤ ኅብረ ብሔራዊ የሆኑ ፓርቲዎችም ይኖራሉ፡፡ ይህስ ለውህደቱ እንቅፋት አይሆንም?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- እኔ ሁላችንም ወደ ብሔራዊ ምክክር መምጣት አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለምሳሌ ብሔር ተኮር የሆነ ፓርቲ ከእኛ ጋር ሲዋሀድ ብሔራዊ ቅርፅ መያዝ አለበት፡፡ አለበለዚያ ብሔር ተኮርና ኅብረ ብሔር ሊዋሀዱ አይችሉም፡፡ ምንድነው ጠቃሚው ነገር? ዲሞክራሲ እስከሆነ ድረስ ለምሳሌ የእኛ ፕሮግራም የግለሰብንም የቡድንንም መብት ያከብራል፡፡ የብሔረሰብ ጉዳይ ከሆነ የቡድን ጉዳይ ነው፡፡ ያ እስከተጠበቀ ድረስ ማንኛውም የብሔር ፓርቲ እኛን ይቀላቀላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያ ነው ጠቃሚው ነገር፡፡ የፕሮግራሙ ዕይታ ብሔር ተኮር የሆኑትን ፓርቲዎች ፍላጐት ማሟላት አለበት፡፡ የብሔረሰቡ ቋንቋ፣ የብሔረሰቡ የመወሰን መብትና ባህል ማሟላት አለብን፡፡ ይኼ የኢትዮጵያ ነፀብራቅ ነው፡፡ አንዴ ወደ ላይ አንዴ ወደ ታች የምንልበት ጉዳይ አይደለም፡፡ እኩልነት እስካለ ድረስ የብሔረሰብ ጉዳይ አይነሳም ባይ ነኝ፡፡ ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ እስካሉ ድረስ ችግር ያለ አይመስለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- አንድነት አሳካዋለሁ ወይም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አመጣዋለሁ የሚለው የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ምንድነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- የእኛ ሊበራል ዲሞክራሲ ነው፡፡ ሊበራል ዲሞክራሲ ሆኖ የቡድንና የግለሰብ መብትን አንድ ላይ እናከብራለን፡፡
ሪፖርተር፡- በሊበራል ዲሞክራሲ የቡድንም የግልም መብት ይከበራል ብለዋል፡፡ ነገር ግን የፍላጐት መጋጨት አይኖርም? በቡድን መብትና በግለሰቦች መብት መካከል ማለት ነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ነው የሚወሰነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ስንት ሰዎች ናቸው እንደዚህ የሚሉት? ሊኖርም ይችላል፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ አሥር ሰዎች ሁለቱን አባረው ማካሄድ አይችሉም የሚል ይኖራል፡፡ 90 በመቶ ከደገፈው የ90 በመቶ ይሆናል ለሚለው የዲሞክራሲ ውሳኔ ነው የሚጠይቀው፡፡ እኛም ተወያይተንበታልና የሚወሰነው በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሚቀጥለው ዓመት የሚካሄድ አገር አቀፍ ምርጫ አለ፡፡ አንድነት እንደ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ በምርጫው ለመሳተፍና ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ምን ምን ሥራዎችን እየሠራ ነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- አንደኛ የራሳችንን አቅም እየገነባን ነው፡፡ ከጠቅላላ ጉባዔያችን ዕይታ አግኝተናል፡፡ በዚያ ዕይታ ለምሳሌ የውህደቱ አንዱ ዓላማ በምርጫ የማሸነፍ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድነት ብቻውን ከሚሮጥ ሦስትና አራት ፓርቲ ሆነን ልክ እንደ ቅንጅት ብንሮጥ የተሻለ ውጤት እናገኛለን በማለት፣ በውህደቱ ለምርጫው አንድ የጐለበተ አቅም ለመፍጠር የምናደርገው ስትራቴጂ ነው፡፡ ሁለተኛው ፕሮግራማችንንና ርዕዮተ ዓለማችንን ልክ እንደ ሚሊዮኖች ንቅናቄ ወደታች እናወርደዋለን፡፡ አንድ የሕዝብን ዕይታ የሚስብ ከምርጫ 2007 ጋር የሚገናኝ ፕሮግራም እናወጣለን፡፡ ሕዝብን ለማንቀሳቀስ ከዚህ በተጨማሪ አንድነት የዲሞክራሲ ምርጫ ፓርቲ ነው፡፡ ለማንኛውም ሁልጊዜ ለምርጫ ይዘጋጃል፡፡ አሁን ስትራቴጂያችንን ከልሰን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር አማራጭ ፖሊሲዎችን እንቀርፃለን፡፡ ከአማራጭ ፖሊሲዎች በመነሳት የምርጫ ማኒፌስቶ እናዘጋጃለን፡፡ በእኔ ዕይታ እስከ ሰኔ ድረስ ካለፈም እስከ ነሐሴ ድረስ አንዱና ትልቁ ሥራችን ይህንን የምርጫ ፖሊሲና ማኒፌስቶ ማዘጋጀት ነው፡፡ ከዚያ ብቁ የሆኑ ዕጩዎችን ከካቢኔያችን ውስጥ እንመለምላለን፡፡ ከየቦታው ብቁ የሆኑ ታዛቢዎችንም እንመርጣለን፡፡ ይህ ሒደት ነው፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባ እናካሂዳለን፡፡ እንደዚሁም ሕዝባዊ ንቅናቄ ይኖረናል፡፡ እየሄድን ራሳችንን ወደ ሕዝብ የምናወርድበት፡፡ ይህን ሁሉ ለማድረግ ግን የምርጫ ፓርቲ ብንሆንም ምርጫ ውስጥ ጥልቅ ብለን አንገባም፡፡ ሜዳው ለሁላችን እኩል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ ስለዚህ ከላይ እንዳልኩት ለዚህ ነው ገንቢ ግንኙነት (Constructive Engagement) ከገዥው ፓርቲ ጋር የምናደርገው፡፡ ይኼ ሜዳ ለሁላችንም እኩል እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ ኢትዮጵያ የጋራችን ነች፡፡ ኢሕአዴግ አንድ ፓርቲ ነው፡፡ እኛም አንድ ፓርቲ ነን፡፡
የምርጫው ሕግ በሕገ መንግሥቱና በምርጫ ቦርድ ሕግ መሠረት መካሄድ ስላለበት ያንን እንጠይቃለን፡፡ ምርጫ ቦርድ የኢሕአዴግ ከሆነ፣ ሚዲያው የኢሕአዴግ ከሆነ፣ የፍትሕ አካላቱ የኢሕአዴግ ከሆኑ እኛ ያን ጊዜ የምንወስነው ውሳኔ ይኖራል፡፡ ነገር ግን ከትዝብትም ጭምር እስካሁን ያሉት ተቋማት ለእኔ ዲሞክራሲያዊ አልነበሩም፡፡ የ2002 ምርጫ በጣም ያዘንኩበት ምርጫ ነበር፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን 99.6 በመቶ የሚያገኝ ፓርቲ የለም፡፡ በዓለም ላይ ዲሞክራሲያዊ በሆነና ውድድሩ በእኩል ሜዳ ላይ ተካሂዶ በእዚህ ውጤት ማሸነፍ አይቻልም፡፡ በዓለም ዙሪያ በአብዛኛው መንግሥት በቅንጅት እየተፈጠረ ነው፡፡ እንግሊዝን ውሰድ የኮንሰርቫቲቭና የሌበር ፓርቲ ቅንጅት ነው፡፡ ጀርመን፣ ጣሊያንና ኖርዌይም እንዲሁ ቅንጅት ነው፡፡ ምክንያቱ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ውድድሩ ነፃ ነው፡፡ እናም ስለዚህ 99.6 በመቶ በጭራሽ ሊሆን አይችልም፡፡ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያለ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና የኅብረተሰብ ክፍል ባህሪ ባለበት አገር ይኼ አይቻልም፡፡ ይኼ ነገር መለወጥ አለበት፡፡ እናም ለምርጫ እንዘጋጃለን፡፡ ነገር ግን ሜዳው ሁላችንንም እኩል ማስተናገድ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- የመጫወቻ ሜዳው ለሁላችሁም እኩል መሆኑን እንዴት ማረጋገጥ ትችላላችሁ?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ለምሳሌ በምርጫ 97 ሚዲያው ትንሽ ወደ ኢሕአዴግም ቢያደላ ተከፍቶ ነበር፡፡ እንዲያውም የእነሱ ሜዳ ከፍ የእኛ ሜዳ ዝቅ ቢልም፣ ነገር ግን የመወዳደርያ ቦታ ነበረው፡፡ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ክርክሮች ለሕዝብ የወጡት በ97 ምርጫ ነበር፡፡ በ2002 ምርጫ ሚዲያው ታፍኖ ነበር፡፡ ሚዲያው የሕዝብ ጥያቄ አላስተናገደም፡፡ ዝም ብሎ ለይስሙላ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተሂዶ አንዳንድ ነገሮች መነጋገራችንን ሕዝብ ሊሰማው ይችላል፡፡ ነገር ግን በሆነ እጅ ቁጥጥር ሥር የወደቀ ነበር፡፡ ያ መሆን የለበትም፡፡ እናም ትልቁ ምሳሌ የ97 ምርጫ የሚዲያ ጉዳይ ነበር፡፡ ሚዲያው ያን ጊዜ ተከፍቶ ነበር፡፡ በእኩልነትም ባይካሄድም ያን ጊዜ እንደ እኩል ነው የወሰድነው፡፡ እንደዚያ መሆን አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ አንድነት የፀረ ሽብር ሕጉ ይሰረዝ የሚል አቋም ይዞ እየተከራከረ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በመላው ዓለም ሽብርተኝነት ትልቅ ሥጋት ሆኗል፡፡ በእኛ አገር የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ አጠቃቀም ተቃዋሚዎችን ፀጥ ለማሰኘት ነው የሚለው እንዳለ ሆኖ፣ አንድነት እንደ ፓርቲ አማራጭ የፀረ ሽብር ሕግ አለው ወይ ይሰረዝ ሲል ምን ማለት ነው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- መጀመርያ ሽብርተኝነትን መዋጋት የኢሕአዴግ ብቻ አይደለም፡፡ የማንኛውም ዜጋ ነው መሆን ያለበት፡፡ ይኼ ሽብርተኝነት ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴው አስከፊ፣ ከሰው ልጅ ባህሪ በተለየ የሰው ልጅን መንፈስ የሚሰብር፣ የሰው ልጅነትን የሚቀንስ ነው፡፡ አንድነትም ሆነ እኔ እንደ አንድነት አመራር እንደዚሁም እንደ ዜጋም እንዋጋለን፡፡ የእኛ ችግር የፖለቲካ መሣሪያ አይሁን ነው፡፡ የአንድነት አባላትና እኔ ከኢሕአዴግና ከገዥው ፓርቲ በምንም መልኩ አናንስም፡፡ ይህን ችግር ለመዋጋት፡፡ ይኼ የዜግነት ግዴታዬ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ወገኑ እንደዚያ ሲጠፋበት ካልተዋጋ ከሰውነትም ከሰብዕናም መውጣት አለበት፡፡ ነገር ግን የእኛ አጽንኦት የፀረ ሽብር፣ የፕሬስና የመያዶች ሕግ የፖለቲካ መሣሪያ መሆን የለባቸውም ነው፡፡ የፖለቲካ መሣርያ ከሆኑ መሰረዝ አለባቸው ነው፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ያለበት ይሁን ነው፡፡ የሁላችንም የጋራ ሥጋት ነው፡፡ ሁላችንም መሳተፍ አለብን፡፡ የፀረ ሽብር አዋጅ ሲወጣ እኛ አልተሳተፍንበትም፡፡ ፓርላማውም እንደሰማሁት በጥልቀት አልተሳተፈበትም፡፡ ይህ አዋጅ የሕዝቡ አዋጅ መሆን አለበት፡፡ በኢትዮጵያ ማንም ከማንም ያነሰ የለም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ስትጠቃ እኔ የመጀመርያው ተዋጊ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- የፓርቲያችሁ ድረ ገጽ አብዛኛውን ጊዜ ቶሎ ቶሎ መረጃዎች ሲጫኑበት አይታዩም፡፡ በአብዛኛው የቆዩ መረጃዎች ናቸው ያሉበት፡፡ የእርስዎን ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ እንኳን በትኩሱ ይፋ አላደረገም፡፡ አሁን ደግሞ እንደዚህ ዓይነት የመረጃ ዘዴዎችን መጠቀም ወደ ሕዝብ ዘንድ ለመድረስ ዓይነተኛ ሚና ስለሚኖረው ድረ ገጻችሁ ለምንድነው መረጃዎችን ቶሎ ቶሎ ለሕዝብ የማያደርሰው?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ያለፉትን መውቀስ አይሁንብኝና ድክመታችን ነው፡፡ እኔም አይቼዋለሁ፡፡ ዘገምተኛ ነው፡፡ አሁን ‹‹አክቲቭ›› እናደርገዋለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ተነጋግረንበታል፡፡ ጠንካራ የሆነ የሚዲያ ግሩፕ አለን፡፡ ነገር ግን እነርሱ ያንን ረስተው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አንስቼ ተነጋግረናል፡፡ የተነጋገርነውም አንደኛ ድረ ገጾችን ዘገምተኛና የነቃ አይደለም፡፡ ሰዎችን የሚስብ ባለመሆኑ ይህ ድረ ገጽ በሥነ ሥርዓት አሁን ለኢትዮጵያውያንም፣ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም አንድነት የሚሠራውን በየቀኑ ማንፀባረቅ አለበት፡፡ ድረ ገጹ ወቅታዊነት ይጐድለዋል፡፡ ሁኔታዎችን ብልጭ የሚያደርገው ጊዜው ካለፈ በኋላ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት እንዲስተካከል የሕዝብ ግንኙነት ይሠራዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ላለፉት ዓመታት ፖለቲካው ላይ ብዙም አይታዩም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ እንደገና ተመረጡ ሲባል እሳቸው ፖለቲካ አልተውም እንዴ የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ እርስዎ ከፖለቲካ ወጥተው ነበር?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- አይደለም፡፡ አንደኛ ለአንድ ዓመት ያህል ተራ አባል ነበርኩ፡፡ ተራ አባል መሆንም አንዳንድ ጊዜ ወደ ላይም ወደታችም ያሳይሃል፡፡ ከዚያ ወደ ምክር ቤት አስገቡኝ፡፡ ብሔራዊ ምክር ቤት ከገባሁ አንድ ዓመቴ ነው፡፡ እዚያ በንቃት እሳተፍ ነበር፡፡ ነገር ግን ራሴን ከሚዲያ አግልዬ ነበር፡፡ እንዲሁ ዝም ብዬ የምናገረው ነገር የለኝም ብዬ ራሴን ከሚዲያው አውጥቼ ነበር፡፡ በመሠረቱ ወደዚህ መምጣትም መቶ በመቶ የእኔ ፍላጐት አልነበረም፡፡ የፓርቲ አባላት ፍላጐት ነው፡፡ የፓርቲ አባላት ፍላጐት በመሆኑ ምክር ቤትም እንደነበርኩ ይኼ ሐሳብ ተንሸራሽሮአል፡፡ ከዚያ በኋላ ያልጨረስከው ነገር ስላለ ግባና እስቲ ጨርሰው የሚል ነው፡፡ እኔ እንግዲህ ያመጣኝ ምርጫው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ፖለቲካ በቃኝ ብለው ነበር?
ኢንጂነር ግዛቸው፡- ፖለቲካ በቃኝ አላልኩም፡፡ የፖለቲካ አመራርነት ግን ይበቃኛል ብዬ ነበር፡፡ ከፖለቲካ አልወጣሁም ነገር ግን ከፖለቲካ አመራርነት ወጥቼ ነበር፡፡ ይህንን እኔ የማምንበት ነው፡፡ ሌላ ለምን አናይም? አንዳንድ ጊዜ ጥላ አጥልተን መኖሩንም እኔ አልፈልገውም፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ መሪዎች ጥላ ሁነው እነርሱ ብቻ ተሰይመው ታች ያለውን አጥልተውበት፣ ታች ያለው ዝም ብሏል፡፡ እንደዚያ መሆንም አልፈልግም፡፡ ያንን ጥላዬን ከአመራርነት አውጥቼ ልጆቹ ወደ ፀሐይ ወጣ ይበሉ ብዬ ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment