የተወሳሰቡ ነገሮችን የመረዳት አስፈላጊነትና የነፃነት ጥያቄ! - ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ
ማሳሰቢያ፣ የዚህ ጽሁፍ መልዕክት ያለንበትን የተወሳሰበ የዓለም ሁኔታ ለማሳየት ብቻ ነው። የዚህ ጽሁፍ ሌላውና መሰረታዊው ዓላማ የተወሳሰበውን ዓለም ሁኔታ እስካልተረዳን ድረስ ወይም ለመረዳት የማንፈልግ እስከሆነ ድረስ ለነፃነት የሚደረገው ትግል የተሟላ ሊሆን አይችልም። ጽሁፉ ማንንም ለማወናበድ የቀረበ ወይም ደግሞ አንድን ርዕዮተ-ዓለም ለማስፋፋት የታቀደና ወይም በጥላቻ ላይ ተመርኩዞ የቀረበ ሆኖ መወሰድ የለበትም። በማስረጃ የተደገፈ ነው። ሁለተኛ፣ ይህ ዐይነቱ ጽሁፍ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሮችና የኢንቬስቲጋቲቭ ጋዜጠኞች ስራ ነው። ስለሆነም ወደ ፊት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሮች እንደዚህ ዐይነቱንም ሁኔታ እያተቱ ቢያቀርቡ ብዙ ሃሳቦችን ማንሸራሸር ይቻላል። ሶስተኛ፣ ይህ ዐይነቱ አቀራረብ በጣም አድካሚ ስለሆነ ተግባሩን ለፖለቲካ ሳይንስ ምሁሮች አስተላልፋለሁ። ብዙ ነገሮችን እየተከፋፈልን ብንሰራ ድካምን ማቃለሉ ብቻ ሳይሆን እንደሚታወቀው የስራ ክፍፍል ጥራትንም ያመጣል። እያንዳንዱ በችሎታው ላይ ቢያተኩር ለኢንፎርሜሽን መለዋወጥ በጣም ያመቻል። አራተኛ፣ የዚህ ጽሁፍ መልዕክት እስካሁን ባደረግነው የትግል ዘዴ ለመቀጠል እንደማንችል ለማሳሰብም ነው። ርስ በራሳችን እየተባላን አገራችንን ከማጥፋት ይልቅ በከፍተኛ የንቃተ-ህሊና በመታገዘና በመሰባሰብ በጋራ እንድንታገል ነው። ስለዚህም ራሳችንም የጠላት መሳሪያ ላለመሆን ለማሳሰብ ብቻ ነው። የኛ አጉል መናቆርና መበላላት፣ ወይም እንደጠላት መተያየት የመጨረሻ መጨረሻ ለጠላት የሚያበጀውና አገራችንን የሚያወድም ነው። የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲና የሃይማኖት ሰለባ ከመሆን መጠንቀቅ አለብን። የነፃነቱ ቁልፍ በራሳችን ውስጥ ያለ ሲሆን፣ መቀዳጀትም የምንችለው ራሳችንን መልሰን መላልሰን በመጠየቅ ብቻ ነው።
መግቢያ
ከረዠም ዐመታት ጀምሮ ትግላችን የአምባገነን አገዛዝ በሚለው ላይ ያተኮረ ነው። ባለፉት 22 ዐመታት፣ መጀመሪያ በመለሰዜናዊ፣ ከአንድ ዐመት ወዲህ ደግሞ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራው አንድ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ የአገራችንን ህልውና ወሳኝ በመሆን ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በማፈን፣ ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በመቆጣጠርና፣ ጥቂቱ ብቻ እንዲበለጽግ በማድረግ፣ ገበሬውን ከእርሻው እያፈናቀለ መሬቱን በመንጠቅና አልሚ ነን ለሚሉ ነገር ግን ዕውነተኛ የሆነ ሀብረተሰብአዊ ሀብትን ለመፍጠር ለማይችሉና አካባቢን ለሚያወድሙ የውጭ ቱጃሮች በማከራየት፣ በዚያው መጠንም ድህነትን በማስፋፋት እንዳለ በየጊዜው ይጻፋል።....... በእኛ አገር ስላለው አምባገነናዊ አገዛዝ ብቻ ሳይሆን፣በብዙ የአፍሪካ አገሮች ከ20ና ከሰላሳ ዐመታት በላይ ስልጣንን የሙጥኝ ያሉ አገዛዞች አምባገነኖች እየተባሉና፣ ለዲሞክራሲያዊ መብቶች አለመኖርና ለሰብአዊ መብት ረገጣ ተጠያቂዎች እንደሆኑ ይነገራል። ሰሞኑን የተያዘው ፈሊጥ ደግሞ እነዚህ አምባገነን መሪዎች የግዴታ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ፊት ቀርበው አስፈላጊውን ቅጣት ማግኘት አለባቸው የሚል ነው።
ይኸኛው ውትወታ ትንሽ ዕውነት ቢኖረውምና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ መደገፍ ያለበት ቢሆንም የጥቂቶች በዓለም ፍርድቤት በሚባለው ፊት መቅረብ አፍሪካ ለገባችበትና አሁንም ላለችበት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና እሴታዊ ቀውስ ብቻውን እንደ በቂ መፍትሄ ሆኖ ሊቀርብ እንደማይችል ግልጽ ነው። የነሱ ትክክለኛውን ፍርድ አግኝቶ ለረዠም ዐመታት እስርቤት ውስጥ እንዲማቅቁ ማድረግ የአፍሪካን ህዝብ ነፃ እንደማያወጣውና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ኢኮኖሚ መገንባት እንዳማያስችለው ሰፊ ምርምርና ጥናት ያካሄዱ ምሁራን ይናገራሉ። በነዚህ አመለካከትና ትንተና መሰረት ቀድሞም ሆነ ዛሬ አምባገነኖችና ወንጀለኞች እየተባሉ የሚከሰሱ የአፍሪካ ገዢዎች በየአገሮቻቸው ለደረሰውና ለሚደርሰው ሰቆቃና የኢኮኖሚ ኋላ-ቀርነት ብቻቸውን ተጠያቂ መሆን እንደማይችሉ ነው። ነገሩን ከአንድ ወገን ብቻ ማየቱ ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገውን ትግል እንደሚያጨናግፍና የአፍሪካን ጥገኝነትና በኢኮኖሚ ኋላ-ቀርነት እንደሚያራዝመው በመተንተን አመኔታ ያለው ማረጋገጫ ይሰጣሉ። ስለዚህም ይላሉ እነዚህ ኃይሎች፣ ቀድሞም ሆነ ዛሬ በአፍሪካ ምድር ውስጥ በስልጣን ላይ የተቀመጡትና የተቆናጠጡ ገዢዎች በምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በእንግሊዝ የስለላ ድርጅት በተቀነባበረ ስትራቴጂያዊ ክንውን እንደሆነ ያመለክታሉ።
እንዲያውም ይላሉ እነዚህ ኃይሎች፣ ቀድሞም ሆነ ዛሬ ለአፍሪካ ኋላ-ቀርነትና የዲሞክራሲ አለመኖር ዋናው ተጠያቂ ኃይል የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም ናቸው። በመሆኑም ሁለቱም የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላው የምዕራቡ ዓለምና የነጭ ኦሊጋሪኪ መደብ በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ውስጥ የዕውነተኛ ዲሞክራሲ አጋዦች ሊሆኑ እንደማይችሉ ሰፋ ያለ ትንተናና ኢምፔሪካል ማስረጃ ያቀርባሉ። ስለዚህም፣ አምባገነን እየተባሉ በሚጠሩት የአፍሪካ መሪዎችና በኢምፔሪያሊስት መሀከል ያለው የተቆላለፍ ግኑኝነት ሲበጠስ ብቻ ነው ዕውነተኛ ነፃነትን መቀዳጀት የሚቻለው ብለው ይነግሩናል። አምባገነን አገዛዞች እያሉ በየጊዜው መለፍለፉና መወትወቱ አውቆም ሆነ ሳያውቁ በኢምፔሪያሊስቶች ጉያ ስር ለመውደቅና እነሱን ተገን አድርጎ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ብሎ የነሱን ፖሊሲ ተግባራዊ ከማድረግና ጥቅማቸውን ከማስጠበቅ ውጭ በፍጹም ለመታየት እንደማይችል ያመለክታሉ። በዚያውም መጠንም የጭቆናው ዘመንና ድህነቱ፣ በረቀቀ መልክ ደግሞ አምባገነንነቱ እንደሚራዘም የዕቅጩን ይነግሩናል።
ይህ ዐይነቱ ግልጽ አመለካከትና በብዙ ኢምፔሪካል ጥናት የተደገፈ ትንተናና ማስረጃ እያለ፣ እንዲሁም ደግሞ እንኳን ለተማረ ሰው ቀርቶ ላልተማረም ሰው ግልጽ የሆነ ቀጥተኛ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚካሄድ ወረራና ዲሞክራሲያዊ ያልሆኑ ኃይሎችን ስልጣን ላይ እንዲወጡ በማድረግ ዕውነተኛ ዕድገት እንዳይመጣ በሚካሄድበት ዘመን ለምንድ ነው ዝም ብሎ ቁንጽል የሆነ አስተሳሰብ በማስተጋባት አምባገነኖች ብቻ ይጠየቁ እየተባለ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦቾን ማሳሳቱ? በየጊዜው ስለአምባገነን አገዛዝ የሚጽፉ የፖለቲካ ተንታኞች የነገሩን ውስብስብነት ማየት ለምን ተሳናቸው? ወደ ኋላ በመሄድ የታሪክን ሂደትና የህብረተሰቦችን ዕድገት ውጣ ውረድ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተዘረጋውና ከተቀነባበረው ሁኔታ ጋር በማቀናጀት ሰፊ ትንተና ለመስጠት ምን የሚያግዳችው ነገር አለ? በእርግጥስ በዚህ ዐይነቱ አተናተናቸውና ውትወታቸው ለህዝባችንና ለተቀረው የአፍሪካ ህዝብ ውሸቱን ከዕውነቱ ነጥሎ በማሳየት የስልጣኔና የዕውነተኛ ነፃነት አጋዠ የሆኑ ይመስላቸዋል ወይ? የአጻጻፍ ስልታቸውና አመለካከታቸው በአንዳች ፍልስፍናና ሳይንስ ላይ የተመሰረተ ነው? ወይስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚናፈሰው ሁኔታ ጋር በማገናዘብ የሚቀርብ ሀተታ ነው ወይ? ይህ ዐይነቱ አመለካከት ከምን እንደመነጨ ጠጋ ብሎ መመልከቱ ጠቃሚ ይመስለኛል።
በየሳምንቱ ቦምባስቲክ በሆኑ ቃላቶች እየተሸፈነ የሚቀርበው ሀተታ ለምን የዕውነተኛ ነፃነትና ስልጣኔ አጋዠ መሆን እንደማይችል ጠጋ ብለን መመልከት አለብን። በተጨማሪም ከዚህ ዐይነቱ ሳይንሰ-አልባ የሆነ ትንተና እስካልተላቀቅን ድረስና፣ ይህንን ትክክለኛ ነው ብለን የምናራግብና የምናሰራጭ ከሆነ ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘውን ዕውነተኛውን ስልጣኔና ነፃነት እንዳያገኝ አስተዋፅዖ እናበርክታለን ማለት ነው፤ ሳናውቀውም እያበረክትንና፣ ራስን ችሎና ተከብሮ ለመኖር የሚያስቸለውን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ እንዲጨናገፍ ማድረጋችን የማይቀር ነው።
ትክክለኛ የሆነ የሳይንሳዊ ግንዛቤ እጦት የሚፈጥረው የአመለካከት ችግር!
ለአብዛኞቻችን ግልጽ ያልሆኑ መሰረታዊ ችግሮች አሉ። አንዳንዶቻቸን በእንግሊዘኛም ሆነ በአማርኛ አንድ ጽሁፍ አዘጋጅተን እንዲነበብለን ለድህረ-ገጾችም ሆነ ለመጽሄቶቸ እንዲወጣልን ወይም እንዲታተምልን በምንልክበት ጊዜ ከሳይንሳዊ ምርምርና ከኢምፔሪካል ጥናት ጋር የተያያዘ መሆኑና አለመሆኑ በግልጽ አይታወቅም። የፍልስፍናችንም መሰረት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ዕምነታችንም ወይም የምናስተጋባው መልዕክት የሰውን አስተሳሰብ በመቅረጽና ለአንድ ዓላማ ለመታገል ያለው ችሎታ እንዲዳብር ለማድረግ የምንፈልገውና የምንጽፈው ጽሁፍ አስተዋጽዖው የቱን ያህል መሰረት ይጣል አይጣል፣ ተቀባይነትን አግኝቶ በዚያው ላይ መስፋፋትና ክሪቲካል ትንተና ተጨምሮብት ይዳብር አይዳብር ጉዳያችን አይደለም። እንዲያው በደፈናው ካለምንም ፍልስፍናዊ ዕምነት፣ ሳይንሳዊ የአጻጻፍ ዘዴና የተወሳሰበ ኢምፔሪካል አመለካከት፣ `እኔ የማምነው በዚህ መልክ ነው፣ ከተቀበልክ ተቀበል ካለበለዚያም ተው` በሚለው አካሄድ የምንጽፈው ሀተታ አንዳችም ፍሬያማ ውጤት ላይ ሊያደርሰን አይችልም። እንዲያውም ጥራትን ከመስጠትና በፕሪንስፕልና በዓላማ ላይ ተመርኩዘን እንድንታገል ከማድረግ ይልቅ ውዝንብር ነዢ እየሆነ መጥቷል። ይህ ዐይነቱ ከሳይንስ ውጭ የሆነና፣ በግልጽ ከሚታዩ፣ ግን ደግሞ እንደተራ ወይም ኖርማል ነገር ሆኖ የሚወሰድ አጻጻፍ ባሻገር የማይታይና የማይተነተን አመለካከት ለሳይንስና ለተክኖሎጂ ዕድገት፣ እንዲያም ሲል ለዕውነተኛ የህዝቦች ነጻነት የማያመች፣ አንድ ህዝብ ዕውነትን ከውሸት ለይቶ ማየት የማይችልበት በመሆኑ የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች በፀረ-ዕድገትና በፀረ-ዲሞክራሲ አገዛዛቸው እንዲገፉበት የሚያደርግ ነው።
በጥንት የአውሮፓ የፍልስፍናና የሳይንስ ትግል ዓለም ውስጥ ነገሮችን በጥቁርና በነጭ እየፃፉ የማየትና፣ አንድን ሁኔታ እንደኖርማል አድርጎ የመውሰድ ባህል የለም።ሁሉም ነገር በዲያሌክቲክ መነጽር መታየትና ለፈተና መቅረብ አለበት። ስለዚህም ስለአንድ ነገር በሚጻፍበት ጊዜ ከቦታና ከጊዜ በሻገር፣ በአንድ ወቅት ውስጥ ተዋናይ የሆኑ ኃይሎች ምን ዐይነት ርዕይና ፍልስፍና እንደሚያራምዱና፣ ሚናቸውንም መረዳቱ ለምናደርገው የነፃነት ትግል ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። የየአንዳንዱን ግለሰብም ሆነ ድርጅት አመለካከትና ብቃት እንዲሁም ሚና ለመረዳትም የምንችለው በየኤፖኩ የተለወጡትን ውስብስብ ርዕዮተ-ዓለማዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችና፣ የበላይነትንና ተፆዕኖን (Sphere of Influence) ማስፋፋት በትንታኔያቸን ውስጥ አካተን መጻፍ የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ በየአገሮች ውስጥ በምድር ላይ የሚታዩ የተበላሹ ሁኔታዎች፣ ድህነት፣ መዝረክረክ፣ የከተማዎች አገነባብ ዕቅድ አለመኖርና ውበት ማጣት፣ የጥቂቱ በሀብት መናጠጥና መባለግ… ወዘተ. የብቃት ዕጦት ውጤቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ የሳይንሳዊ ግንዛቤ እጦትና በአንድ የተወሰነ አመለካከት መሰልጠን የሚፈጥራቸው ሁኔታዎች ናቸው።
በታሪክ ውስጥ ለዕውነተኛ ነፃነት ትግል ሲደረግ፣ በመጀመሪያ ደረጃ በአንድ ወቅት ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች የተበላሸ ወይም ደግሞ ህዝብን የሚበታትንና ወደ ድህነት የሚገፉ ፖለቲካዎች ለምን እንደሚከተሉ ዋናው የምርምር ዘዴ ነበር። ስለሆነም ትግሉ በግልጽ የሚታዩ ነገሮችን ከማይታዩ ነጥሎ በማውጣት በማይታየው ላይ ማነጻጸርና ወደ ውጭ አውጥቶ በመጻፍ ህዝብን ማሰተማርና አንድ ሀዝብ ለትክክለኛው የነፃነት ትግል እንዲነሳ ማድረግ ተቀዳሚው ተግባር ነበር። ስለሆነም በጊዜው የነበረው ትግል በስልጣን ላይ የነበሩትንና በጦርነት መንፈስ የሰከሩ ኃይሎችን አዕምሮ መመርመሪያው ዘዴ በስልጣን ላይ ያሉትን ኃይሎች የዕውቀት መሰረትና የሞራል ብቃት መመርመር ነበር። ከዚህም በመነሳት እነዚህ ኃይሎች ድርጊታቸውን በትክክል ይገነዘቡ አይገነዘቡ እንደሆን፣ ድርጊታቸው በተከታታይ ትውልድና በጠቅላላው ህብረተሰብ ስርዓት ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጠንቅ በደንብ መረዳት መቻላቸውንና አለመቻላቸውን መመርመርና፣ ይህንንም በመመርኮዝ ትግል ማካሄድ ነበር። ትግሉ በቀጥታ እነሱን ማስወገዱ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ የሚመሩበትንም ጠቅላላ ፍልስፍናና ፖሊሲ በመመርመር እሱን በመዋጋት ዕውነተኛ የጭንቅላት ተሃድሶን ሊያመጣና አንድን ህዝብ ፈጣሪ ሊያደርግ በሚችል ፍልስፍናና ላይ መረባረብ ነበር። ይህም ማለት ትግሉ በአንድ ነጠላ ነገር ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን በጠቅላላው ሁኔታ ላይ የሚያነጻጽር ሲሆን፣ መምጣት ያለበትም ለውጥ ጠቅላላውን ሁኔታ ቀስ በቀስ እንዲለወጥ የሚያደርግና በጸና መሰረት ላይ ሊቆም የሚችልና ዘላቂነት ያለው አገር መገንባት ነው። በዚያውም መጠን ሰላምና ዕኩልነትን ለማስፈን ነው።
በሌላ ወገን ግን የጥንቱ ሁኔታ እንደዛሬው የተወሳሰበና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘረጋ ፖለቲካዊ፣ ሚሊታሪያዊና ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር ስላልነበረና፣ በሺህ ድሮችም ከውስጡ ሁኔታ ጋር ያልተሳሰረ ስልነበር ትግሉ ንጹህ በንጹህ ብሄራዊ ነበር። እንደዛሬው አንድ ወይም ሁለት ኃያል መንግስታት በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን፣ በሚሊታሪና በኢኮኖሚ እንዲሁም በርዕዮተ-ዓለም አይለው በመሄድ የዓለምን ህዝብ ዕድል የሚወስኑበት ሁኔታ ስላልነበር ትግሉን ለማካሄድ በጣም ቀላል ነበር። ፍልሚያው ወደ ውስጥ ያተኮረና ግልጽም ነበር። አሁን ያለንበት የታሪክ ወቅት ግን እንደ ጥንቱ ግልጽ ስላይደለ ለነፃነት የሚደረገው ትግል እዝጅግ አስቸጋሪ ነው። ከሁለት መቶ ዐመት ጀምሮ የዓለምን ህዝቦች ዕድል ወሳኝ በመሆን አይሎ የወጣው የካፒታሊዝም ኢኮኖሚያዊ ክንውን ወይም ስልተ-ምርትና፣ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ ወደ ሞኖፖሊዝምነትና ከዚያም ወደ ኢምፔሪያሊዝምነት የተለወጠው ፓለቲካዊ፣ ሚሊታሪያዊ፣ ርዕዮተ-ዓለማዊ፣ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔዎችን የሚያካትተው በአንድ አገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የዓለምን ህዝብ ሁሉ ዕድል ወሳኝ በመሆን ለነፃነት የሚደረገው ትግል እጅግ እየተወሳሰበ መጥቷል። በተለይም እ.አ ከ1945 ወዲህ የተፈጠረው አዲስ የኃይል አሰላለፍ የብዙ አፍሪካ መንግስታትንና የላቲንና የአሽያን አገሮች የመንግስት አወቃቀር ጥንካሬና ድክመት ሊወስን ችሏል።
ስለሆነም በተለይም ባለፉት 60 ዐመታት በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የርዕዮተ-ዓለም ውዥንብር በመፈጠር ትግሉ በኮሙኒስቶችና የሊበራል ዲሞክራሲን መንፈስ በሚያስተጋቡና የህግ የበላይነት እያሉ በሚጮሁ መንግስታትና ድርጅቶች እንዲሁም ግለሰቦች አስመስሎታል። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ሁላችንም በእንደዚህ ዐይነቱ በተወናበደ ርዕዮተ-ዓለም ውስጥ ገብተን እንድንዋኝ በማድረግ፣ የዕውነተኛውን ፍልስፍናና የነፃነት መንገድ በመሳት ወደድንም ጠላንም የአንድን አገር ነባራዊ ሁኔታና የተወሳሰበውን ዓለም ሁኔታ እንዳንገነዘብ በማድረግ ወደ ግብግብ እንድናመራ አድርጎናል። እ.አ ከ1989 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ ዓለም ወደ አንድ መንደር እያመራች ነው ከተባለና የአሜሪካንን የነፃ ገበያና የነፃ ንግድ መርሆ ማራገብ ከተጀመረ ወዲህ የዓለም ህዝብ አመለካከት የባሰውኑ ተዘበራረቀ እንጂ ጥራት አግኝቶ በየአገሮችም ውስጥ ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰላምና ብልጽግና ሲሰፍኑና ሲዳብሩ አይታይም። እንደምናየው ዓለም በግሎባላይዜሽን ውስጥ ተጠቃለለች፣ ርዕዮተ-ዓለም የሚባልም ነገረ ጠፋ፣ ከእንግዲህ ወዲያ የሚኖረው ግጭት የባህል ግጭት ነው ከተባለ ወዲህ የዓለም ህዝብ ሲረጋጋና ሰላማዊ ኑሮ ሲገነባ አይታይም። ግሎባላይዜሽን አዲስ መዘዝ ይዞ በመምጣት እንደሸበርተኝነት የመሳሰሉት ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች በመሆን መንፈሳዊ መረጋጋት እንዳይኖር ተደርጓል። ከዚህም ስንነሳ ብዙ ነገሮች ስለተምታቱ ሀቁን ከውሸቱ መለየት የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። በመሆኑም እኛም ራሳችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተስፋፋው የየአገሮችን ህይወት የሚያበላሸው ኢምፔሪሲስታዊ አመለካከት ሰለባ በመሆን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንድንወድቅ ተገደናል።
ከዚህ ስንነሳ በአብዛኛው ለድህረ-ገጾችም ሆነ ለመጽሄቶችና ለጋዜጦች ጽሁፍ የሚያቀርቡ ምሁራን ዘንድ የዓለምን ፖለቲካ አወቃቀርና፣ በአፍሪካና በአሜሪካን፣ እንዲሁም በተቀረው ኢምፔሪያሊስት አገር ያለውን ትስስር በደንብ ዘርዝሮ ለማቅረብ ምንም ጥረት አይደረግም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በየአገሮች ውስጥ ያለውን ወይም የሰፈነውን ህብረተሰብአዊ አወቃቀር፣ የማቴሪያል ሁኔታና የስነልቦና ባህርይ የመረዳት ችግር አለ። ስለሆነም ብዙዎቻችን ሁኔታዎችን በተሳሳተ መልክ ስለምናነብና በተሳሳተ የአሰራር ስልት ስለምንጠቀም ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን። እንደሚታወቀው በተፈጥሮ ሳይንስም ሆነ በህብረተሰብ ሳይንስ ውስጥ ግልጽ የሆኑ ሳይንሳዊና ኢምፔሪካል የአሰራር ስልቶች አሉ። ችግሮችን ለመረዳት የሚያገለግሉና የተደራረቡ ችግሮችም እንዴት ቀስ በቀስ መፈታት እንደሚችሉ የሚያሳዩ። ስለሆነም ሳይንሳዊ የአሰራር ስልትንና አንዳች ዐይነት የሆነን ፍልስፍናዊ አመለካከት መሰረት ያላደረገ አቀራረብ የችግሩን መሰረት እንድንረዳ ከማድረግ ይልቅ እያሳሳተንና ውዥንብር እየነዛብን ነው። በተለይም ስለ አፍሪካ አምባገነኖችና ሚናቸው በየጊዜው የሚቀርበው የፖለቲካ ሀተታ ብዙ ግድፈቶች ይታይበታል። የአፍሪካን ህዝብ ዕድል ወሳኞች እነዚህ አምባገነን እየተባሉ የሚጠሩ አገዛዞች እንደሆኑ ተደርገው ነው እንጂ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደረግባቸውን የሚሊታሪ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጣልቃ-ገብነትና ጭነት ከቁጥር ውስጥ በማስገባት አይደለም ለሌላው ለማስተማር ጥረት የሚደረገው።
በተወሰነ የአስተሳሰብ መነፅር በመመልከትና በመመራት የነገሮችን ሂደትና ዕድገት ለመገንዘብ ወደ ኋላ ትንሽ ተጉዞ ከመመርመርና፣ የአፍሪካን የህብረተሰብ ዕድገት ከአውሮፓው የህብረተሰብ አካሄድ ጋር እያነፃፀሩ (Comparative Studies) የአፍሪካን አገሮች ችግር ከማጥናት ይልቅ አንድ ውሳኔ ላይ በመድረስ በየአገሮች ውስጥ ለደረሰውና ለሚደርሰው በደልና ድህነት ተጠያቂዎቹ አምባገነኖች ብቻ እንደሆኑ እንከሳቸዋለን። በዚህም ምክንያት የተነሳ ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገውን ትግል እያዛነፍን ነው። እንደ ዕውነቱ ከሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዕውነተኛ ነፃነት፣ ለዕኩልነትና በአገሮች መሀከል በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት እንዲፈጠር የሚደረገውን ትግል ጠጋ ብሎ ለተመለከተ ወይም ለተከታተለ ሰው የሚገነዘበው ነገር ለእኛ ነፃነትና ዕድገት የሚታገሉንን እኛው ሳንሆን ከራሱ ከካፒታሊዝም አብራክ ስር የፈለቁ አንዳንድ የተገለጸላቸው ምሁራን ናቸው። የሚገርመውም ነገር እዚህ ላይ ነው። እኛው ተበዳዮችና ተበዝባዦች ቁጭት ይዞን በትጋት እያጠናንና እየተባበርን፣ እንዲሁም ሃሳብ ለሃሳብ እየተለዋወጥን በጋራ ለዕውነተኛ ነፃነት ከመታገል ይልቅ አንገታችንን ደፍተንና በመሸማቀቅ ከዋናው ችግር ለመሸሽ እንሞክራለን።ይህ ዐይነቱ መሸማምቀቅና ቁንጽል አስተሳሰብ፣ እንዲሁም ኢ-ሳይንሳዊ አመለካከት እንዴት ሊስፋፋና በጽሁፍ መልክ ሊስተጋባ ቻለ?
በኛ በኢትዮጵያውያኖች ዘንድ ያለው ዋናው ችግር በየጊዜው ጥያቄ ያለመጠየቅና፣ አንድ ቦታ ላይ ቆሞ በመገረምም ሆነ በማዘን አንድ ነገር ሲከሰት ሁኔታው ለምን በዚህ መልክ ሊከሰት ቻለ? ብሎ የነገሮችን መነሻና ርስ በርስ መያያዝ በዲያሌክቲካልና በሚታፊዚካል መነጽር ለመመርመር ያለመቻል ዋናው ምክንያት ይመስለኛል። ይህንን ቁንጽል አስተሳሰብና የነገሮችን ዕድገትና ውስብስበነት ለመረዳት ያለመቻል ደግሞ በራሱ በቂ ምክንያት አለው።
ለምሳሌ የኢትዮጵያን የትምህርት ስርዓትና ካሪኩለሙን ስንመለከት ክሪቲካል በሆነ መልክ የተዘጋጀ አይደለም። ሳይንሳዊና ክሪቲካል አመለካከት እንዲዳብር የተዘጋጁ የመማሪያ መጽሀፎችና አስተማሪዎችም ስለሌሉ ተማሪዎች ጨርሰው ሲወጡ የሚያስቡና የነገሮችን ሂደት ክሪቲካል በሆነ መልክ ከመመልከት ይልቅ አንድን ነገር በጥቁርና በነጭ በመሳል የአንድን ነገር ሁኔታና ዕድገት ለመረዳት በጣም ይቸግራቸዋል። ከዚህም የተነሳ አብዛኛዎቹ አቀራረቦችና ትንተናዎች ሎጂክን ያዘሉ አይደሉም። ስለሆነም ለነፃነት እታገላለሁ የሚለውን ሰው አቋምና ፍልስፍና ለመረዳት በጣም አአስቸጋሪ ነው። እንደዚሁ ዐይነቱ አስተሳሰብና አመለካከት የሚንፀባረቀው በአገር ቤት ብቻ ሳይሆን በውጭ አገርም የመማር ዕድል ባገኘውም ላይ ይታያል። ወደ ውጭ ለመማር ዕድል ያገኘው አብዛኛው በኒዎ-ክላሲካልና በኒዎ-ሊበራል አስተሳሰብ ክልል ውስጥ ወይም ደግሞ በኢምፔሪሲስት አስተሳሰብ ክልል ውስጥ ስለሚሽከረከርና፣ በዚህ አስተሳሰብ ስለሚታነጽ የሚኖርበትንና የዓለምን የፖለቲካ አወቃቀርና አካሄድ የመረዳት ችግር አለበት ብል የምሳሳት አይመስለኝም። ለምን እንደሆን አላውቅም አብዛኛው ተማሪ ቶሎ ብሎ የኒዎ-ክላሲካል አስተሳሰብ ያላቸው ፕሮፊሰሮች ጋር ስለሚወድቅና በነሱ አስተሳሰብ ስለሚጠመድ የዓለምንም ኢኮኖሚ አወቃቀርና በተለያዩ አገሮች ያለውን የተዛባ ዕድገትና እጅግ አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ለመረዳት ያዳግተዋል።
ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ በውጭ አገር የሚኖረው አብዛኛው ተማሪም ሆነ ምሁር ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባለበት አካባቢ ስለማይውልና ከሌላውም የመማር ዕድል ስለማያገኝ በአስተሳሰቡ ውስን ይሆናል። ተገልሎም ስለሚኖር የመወያየትንና የመከራከር፣ እንዲሁም ሃሳቡን በድፍረት የመግለጽ ችግር ይታይበታል። ሌላው ደግሞ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንደ አሸን የፈለፈለው ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ውስጥ እየተመለመለ ስለሚገባና ቲክኖክራሲያዊ የአሰራር ልምድ ስለሚያካብት የዓለምንም ሆነ የየአገሩን ተጨባጭ ሁኔታ የማንበብ ችግር አለበት። በስራ ዓለም ላይ በሚቆይበትም ጊዜ ከተለያዩ የስራ ባልደረቦች ጋር ስለሚገናኛና ልዩ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀምና አነጋገር ባህርይ ስለሚለምድ ሁለንታዊና ክሪቲካል የሆነ አስተሳሰብና አመለካከት ሊያዳብር አይችልም። በዚህም የተነሳ ዕውነተኛ የሰብአዊነት ባህርይና ርዕይ ማዳበር ስለማይችል ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ በዓለም ላይ የተስፋፋውን የብዝበዛና የጭቆና ስርዓት የሚያጠናክር ይሆናል። ለስልጣኔም ጠንቅ ይሆናል። የተገለጸለት አስተሳሰብ ከማዳበር ይልቅ ፊዩዳላዊውንና የአሜሪካን ኤምፔሪያሊዝምን የአመጽ አስተሳሰብ በማጣመር ወደ ጨቋኝነትና ታዛዥነት፣ እንዲያም ሲል ህዝብን ወደ መናቅ ያመራል። በዓለም የአገዛዝ የጭቆና ሂራርኪ ውስጥም ስለሚካተትና የምዕራቡ የተሳሳተ እሴት ዋና አቀንቃኝና አራማጅ ነው ተብሎ ሰለሚታይ በዚህ እየተደሰተና ውስብስብ ስምምነት ውስጥ እየገባ ድህነትን የሚያስፋፋና ብሄራዊ ነፃነት የሚገፍና የሚያስገፍፍ ይሆናል።
በዚህም መልከ የረቀቀ የህዝብን ነፃነት የሚገፍ አምባገነናዊነት ይስፋፋል። በዚህም ምክንያት ያለበትን አገር የኑሮ ሁኔታ፣ የዕውቀት ጉዳይ፣ የኃይል አሰላለፍና የምርት ግኑኝነት፣ እንዲሁም ይህንን ለማጠናከር የሚወሰደውን ርዕዮተ-ዓለማዊ ሰበካ ለመመርመር የሚያስችለው ዕውቀት ስለማይኖረው ዕውነተኛ ሀብትን አፍሪና ስልጣኔን አምጭ አይሆንም ማለት ነው። አውቃለሁ የሚለው ደግሞ በቆንጆ ቃላቶችና `በተወሳሰበ` የአጻጻፍ ስልት በመጠቀም የነገሮችን ሂደት እንዳንረዳ በማድረግ አመለካከታችንን ያዛንፍል። ይህ አቀራረቤ ተራ ውንጀላ ሳይሆን ከብዙ ምርምርና ግንዛቤ በኋላ የደረስኩበት ድምዳሜ ነው። በኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ- በምዕራቡ ማስ ሚዲያ በተሳሳተ መልክ ፕሮፖጋንዳ ስለሚነዛና አብዛኛውም በስራ ስለሚጠመድ ይህ ዐይነቱ የተዛባ አመለካከትና ዕምነት የኛ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ ነው- ለመረዳት ታች ያለውን የተሳሳተ የታሪክን ሂደት የማንበብ ችግር መጥቀሱ አቀራረቤን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል ብዬ እገምታለሁ።
ለምሳሌ በጣም ጥቂቶች ካልሆን በስተቀር ወደ ኋላ መለስ ብለን በካፒታሊዝም ዕድገትና መስፋፋት ውስጥ የተደረጉትን ውጣ ውረድ ሁኔታዎችንና ወንጀሎችን የምንጠይቅ በጣም ጥቂቶች ብቻ ነን። ለምሳሌ የጦርነትን ታሪክ ስንመረምር አብዛኛው ጦርነት የተካሄደው በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ነው። የመቶ ዐመት፣ የሰላሳ ዐመት፣ የሰባት ዐመትና ከዚያ በኋላ ደግሞ ትናንሽ ጦርነቶች የተካሄዱት በምዕራቡ የካፒታሊስት ምድር ነው። እጅግ በአሰቃቂ መልክ ሴቶች እንደጭራቅ እየታዩ ይቃጠሉ የነበረው በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ፣ ያውም ሬናሳንስ፣ ፕሮቴስታንቲዝምና ኢንላይተንሜንት የተባሉ ጭንቅላትን የሚያድሱና ሰው ሰው መሆኑን እንዲገነዘብ የሚያደርጉ የአውሮፓ ህዝብ ከፊዩዳሉ ስርዓት እየተላቀቀ ወደ ካፒታሊዝም በሚሸጋገርበት ዘመን ነበር። ካፒታሊዝም እንደህብረተሰብ ስርዓት ተቀባይነት እያገኘ ከመጣም ወዲህ ህጻናት ሁሉ ሳይቀሩ ወደ ስራ ዓለም በመሰማራት የሚሰቃዩበት ዘመን ኮሙኒዝም ሳይሆን ካፒታሊዝም ነበር። ካፒታሊዝም ወደ ሞኖፖሊዝምነት ከተለወጠ በኋላ የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት የተቀሰቀሰውና ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ተጠያቂ የሆነው የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት የተቀሰቀሰው በካፒታሊስት አገር ነው።
የሁለተኛው ዓለም ጦርነትም እንደዚህ በካፒታሊስት አገር ሲቀሰቀስ ወደ ሃምሳ ሚሊዮን የሚጠጉ ህዝቦች ህይወታቸው እንዳጡ ይታወቃል። ታሪኮች፣ ባህሎችና ከተማዎች ወድመዋል። እንደዚሁም ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ ይሁዲዎች የተቃጠሉት፣ በአሰቃቂ ሁኔታ ቆዳቸው እንዲገፈፍ የተደረገውና በየቦታው የተገደሉት በሰለጠነው የካፒታሊስት ስርዓት ያውም በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ነው። የጦርነቱም ዋናው አራጋቢዎች የጀርመን ፋሺዝም ብቻ ሳይሆን ስርዓቱም እንደነበርና፣ ይህም ደግሞ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በእንግሊዝ ሲደገፍ ዋናው ዓላማው በጊዜው በተቀናቃኝነት የወጣችውንና ሌላ ስርዓት በመመስረት ላይ የነበረችውን ሶቭየት ህብረትን ለመደምሰስና ሀብቷን ለመቆጣጠር ነበር። ስሌቱ ግን ስላልሰራ ሂትለር ጠላቶቼ ናቸው የሚላቸውን ሁሉ በቦምብ መደብደብ ጀመረ። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ጦርነት የካፒታሊዝም አንደኛው አካል ነው። በሰላም ሊያገኛቸው የማይችላቸውን መሬትም ሆነ የጥሬ ሀብት የግዴታ በጦርነት አማካይነት አገኛለሁ ብሎ ስለሚያምን ደካማ አገሮችን ይወራል። የሚፎካከሩትን ደግሞ በተለያዩ መንገዶች ለመዳካም ይጥራል። ይህ ካላዋጣው ደግሞ ወደ ጦርነት ውስጥ የሚገቡበትን ዘዴ በመፍጠር እንዲወጠሩ ያደርጋል። በዚህ መልክ ጦርነቶችን በየቦታው በመቀስቀስ ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች መሞት ምክንያት ይሆናል። ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች እየተባሉ በሚጠሩት አገሮች ውስጥ የተካሄዱትና ዛሬም የሚካሄዱትንም ጦርነቶች ስንመለከት፣ በመጀመሪያ በቀጥታ ወረራ፣ ቀጥሎ ደግሞ የውክልና ጦርነት (Proxy War) በማስፋፋት ጦርነት ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዲይዝ ያደረገው በተለይም የአሜሪካን ኢምፔርያሊዝም እንደሆነ ራሳቸው የሲአይኤ የቀድሞ ሰራተኞች ሳይቀሩ ያረጋግጣሉ። ብዙ አሜሪካዊያን የሊትሬቸርና የፖለቲካ ተንታኞች በሰፊው ዘግበዋል።
ሀቁ ይህ ከሆነ ታዲያ በኛ ምሁራን በምንባል ኢትዮጵያኖች ዘንድ ለምን የአስተሳሰብ ግድፈት ይታያል? ነገሩ ቀላል ነው። ላይ እንዳልኩት ታሪክን ወደ ኋላ መለስ ብለን የምንመረምርበት መሳሪያ ዲያሌክቲክና ሜታፊዚክሳዊ አመለካከት አይደሉም። ይህም ማለት የነገሮችን ሂደት ወይም ሁኔታ በተወሰነ የክስተት (Empiricism) መነጽር ብቻ ነው የምንመለከተው። ስለሆነም የአንድን ነገር ሁኔታ ወደ ውስጥ ገብቶና ውስብስብ ሁኔታዎችን መርምሮ አንዳች ውጤት ላይ ከመድረስ ይልቅ ቶሎ ብለን አንድ መደምደሚያ ላይ በመድረስ ለስልጣኔም ሆነ ለዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የማያመች የወገናዊ ስሜት እንወስዳለን። በቂ ኢንፎርሜሽን ሳይኖረንና ሁኔታዎችን ከብዙ አቅጣጫ ሳንመረምር እጅግ የሚያሳስትና ጭንቅላትን የሚያደነዝዝ ሀተታ ነገር በመሰጠት ለዕውነተኛ ነጻነት የሚደረገው ትግል ተልከስክሶ እንዲቀር እናደርጋለን፤ እያደረግንም ነው። በዚህም ምክንያት የአንድን ችግር ዋና ምንጭ ለመረዳት ባለመቻላችን ትግላችንን ውስብስብ እያደረግነውና የአገራችንንም ዕድል እያበላሸነው ነው።
ከዚህ ዐይነቱ ኤምፔሪሲስታዊ አመለካከት እስካለተላቀቅን ድረስና፣ ተራ የጋዜጣ ዐይነት ሪፖርት በማቅረብ ውንጀላን በአንድ ግለሰብ ወይም አገዛዝ ላይ ብቻ የምንለጥፍ ከሆነ የምንፈልገውን ነፃነት ማግኘት አንችልም። ይህ ማለት ግን አንድ ግለሰብም ሆነ አገዛዝ የችግር ምንጭ ሊሆኑ አይችሉም ማለት አይደለም። ጥያቄው ለምን የተስተካከለ ዕድገትና ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ሊያመጡና ሊያሰፍኑ አልቻሉም? ብሎ በምሁራዊ መነፅር መመርመር የምሁራን ኃላፊነት ነው። የለም አምባገነኖች ስለሆኑ ነው የተስተካከለ ዕድገት እንዳይኖር የሚያደርጉትና ጭቆናንም የሚያሰፍኑት የሚለው በምንም ዐይነት እንደዋና ምክንያት ሆኖ ሊተነተን አይችልም። ለምንድነው አምባገነን ለመሆን የቻሉት የሚለውንም መመርመሩ የግዴታ ችግሩን የመረዳት አንድ አካል መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር ማንም ሰው በአፈጣጠሩ አምባገነናዊ ሆኖ ስለማይፈጠር የዕውነተኛ ምሁራን የምርምር ዘዴ አምባገነን እየተባሉ የሚወነጀሉትን ግለሰቦችና አገዛዞች የተወለዱበትን የህብረተሰብ ሁኔታ፣ የአደጉበትንና የተማሩትን ትምህርት፣ ከዚያም በኋላ በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ሲገቡ ከተለያዩ ኃይሎች ጋር የሚፈጥሩትን ትስስርና የሚያስተጋቡትንና የሚጽፉትን ጽሁፍ ጠጋ ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። ይህ ዐይነቱ የምርምር ዘዴ የተጠጋጋ መልስ ሊሰጠን ይችላል።
ሌላው በእኛ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ በተለይም በድህረ-ገጾችና ለመጽሔቶች ወይም ለጋዜጦች አርቲክሎች ጽፈን እንዲወጣልን የምንልክ ምን ዐይነት ርዕይ ወይም ርዕዮተ-ዓለም እንዳለንና እንደምናስተጋባ በፍጹም ግልጽ አይደለም። እንደሚባለው ዕሴተ-አልባ ሳይንስ (Value free science) ወይም ዕሴተ-አልባ የስነ-ጽሁፍ አጻጻፍ ስልት የለም። ጋዜጠኞች እንኳ በዚህ በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ በርዕዮተ-ዓለም በመከፋፈል ነው የዚህን ወይም የዚያኛውን መደብ ጥቅም ለማስጠበቅ ደፋ ቀና የሚሉት። በተቻለ መጠን ያለው ስርዓት አማራጭ እንደሌለው ለማሳመን በሚሞክሩና ስርዓቱ በዚህ ሊቀጥል አይችልም፣ የግዴታ እዚህና እዚያ ቦታ የጥገና ለውጥ ያስፈልገዋል ብለው የሚታገሉ፣ ወይም ደግሞ ሌሎች ጥቂቶች ስርዓቱ እንዳለ መለወጥ አለበት እያሉ አስተያየት የሚሰጡም አሉ። የካፒታሊዝምን ጠቅላላ ዕድገት ከፍልስፍናና ከንጹህ የተፈጥሮ ሳይንስ አንጻር የሚመረምሩና በዚህ ዐይነት ካፒታሊስታዊ የጥሬ-ሀብት ጨራሽ የምርት አደረጃጀት ስልት የሰው ልጅና ተፈጥሮ ወደፊት ተቻችለው ሊኖሩ እንደማይችሉ ነገሩ የግዴታ መታረም እንዳለበት ግሩም ግሩም የሆነ የምርምር ጥናት የሚያቀርቡም አሉ።
አንዳንዶቹ እንዲያውም አልፈው በመሄድ ለዚህ ዐይነቱ በማያቋርጥ የምርት ሂደተና የፍጆታ አጠቃቀም ዋናው ተጠያቂው በተወሰኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች በኒውተንና በዴካ ተፈጥሮን እንደበድን ተደርጎ የተወሰደው የሳይንስ አመለካከት በመስፋፋቱና ስር እየሰደደ በመምጣቱም ነው የሚሉም አሉ። በሬነ ዲካ ዕምነት በመንፈስና በሰውነት መሀከል ልዩነት ሲኖር፣ መንፈስ ህይወት ሲኖረው ሰውነት ግን በድን ነው። ተፈጥሮም እንደዚሁ በድን ነች የሚል ነው። በተጨማሪም ወደ አንድ ነገር ለመድረስና ሳይንሳዊ መልክ ለመስጠት ነገሮችን እየሰበጣጠሩና በሚጠቅመው ነጠላ ነገር ላይ ማተኮሩ የምንፈልገውን ውጤት ይሰጠናል ይላል። ስለሆነም ይላሉ ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው ፈላስፋዎች፣ ይህ ዐይነቱ ፍልስፍና በመስፋፋቱና በነጠላ ነገሮች ላይ ማትኮር፣ እንዲሁም ደግሞ በነገሮች መሀከል ያለውን የተወሳሰበ ቅንጅትና መደጋገፍ አለመረዳትና ይህንን ሳይንሳዊ መሰረት አለማድረግ፣ ካፒታሊዝም ሳይንስንና ቴክኖሎጂን የችግር መፍቺያና የኑሮ ማቃለያ ከማድረግ ይልቅ ወደ ንጹህ ትርፍ ማትረፊያ መሳሪያና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ-ሃሳብ ውስጥ እንዲያተኩር ስላደረገው ሰውና ተፈጥሮ ወደ ተራ ተበዝባዥነት ተለውጠዋል ይላሉ።
በካፒታሊዝም የቴክኖሎጂ ምጥቀት የተነሳ ቴክኖሎጂ የችግር መፍቻ መሆኑ ቀርቶ በኢኮኖሚ ቁጥጥር ውስጥ በመውደቁ የሰው ልጅ የቲክኖሎጂ ተገዢ እንዲሆንና እንዲሰቃይ ተደርጓል። ይህንን በሚመለከት ጎተ ፋውስት ሁለት (Faust II) በሚለው ልበ-ወለድ የቲያትር ድርሰቱ ውስጥ በሚገባ አስቀምጦታል። የሰው ልጅም ፍላጎት ከማምረትና ፍጆታን ከመጠቀም ባሻገር መታየት የለበትም። ይህም ማለት በዚህ መንፈስ የሰለጠነው የሰው ልጅ ሌሎች የሰውን ልጅ ባህርዮች፣ ማለትም አርቆ አሳቢነት፣ ርህሩህነት፣ ሰብአዊነት፣ ሰነምግባራዊነትና ማህበራዊነት እንዲያጣና ወደ ንጹህ ኢኮኖሚያዊ መሳሪያነት በመለወጥ እየተፈራራ እንዲኖር ተገዷል። ገንዘብም የግኑኝነት መለኪያ እንደመሆኑ መጠን፣ ባለው ውስጣዊ `የሳይኮሎጂካል ኃይል` የሰውን መንፈስ በመቆጣጠር የሰው ልጅ ራሱን እንዲሸጥና ለሌላው ደንታ እንዳይኖረው ወደ ማድረግ ተቃርቧል። ይህ ወረቀት የሚመሰለውና ውስጥዊ ዋጋ (Intrinsic Value) የሌለው ወይም በምንም ነገር ያልተደገፈው የሰውን መንፈስ በመቆጣጠር አጭበርባሪዎችን፣ ጦረኞችንና አገር ሻጮችን በማፍራት እያንዳንዱ ዜጋ በራሱ አገር እየሰራ እንዳይኖር አግዷል።
በተለይም የአሜሪካን ዶላር ዓለም አቀፋዊ የመገበያያና የሀብት ማከማቺያ መሳሪያ ከሆነ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ የፈጠረው መንፈሳዊ ኃይል የሰውን ልጅ የርስ በርስ ግኑኝነትና የየአገሮችን የስልጣኔ መሰረትና ራስ እያመረቱ ራስን መመገብ የሚለው መሰረታዊ መመሪያ እንዲወድም በማድረግ በብዙ ሚሊያርድ የሚቆጠር ህዝብ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ተገዷል። የአመራረትን ስልት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የፖለቲካ ስርዓቱ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እያጣ እንደመጣና በገዚዎችና በተገዚዎች መሀከል ያለው ግኑኝነት ከምንጊዜውም በላይ እየራቀ እንደመጣ እየተነተኑ ያስተምራሉ። በቴሌቪዠንም እየወጡ ይከራከራሉ። ራሳቸው ወግ-አጥባቂ ነን የሚሉ ሳይቀሩ የድሮ እሴት ያለው የአኗኗር ስልት መምጣት አለበት እያሉ የራሳቸውን የድሮ አቋም በጥያቄ ውስጥ እያስቀመጡት ነው። ከዚህ ስንነሳ የኛ የኢትዮጵያውያን ምሁራኖች አቋም ግራ የሚያገባ ነው የሚመስለኝ። እንደሚባለው እያንዳንዱ ነገር ስም አለው። ስርዓትም እንደዚሁ። ስለሆነም ለምን እንደምንታገል ግልጽ የሆነ አቋም ቢኖረንና ለሱ እንደጠበቃ ብንቆም የትግሉ መስመር መጥራት ብቻ ሳይሆን፣ ውስብስብ የሆነው ትግላችንም መልክ በመያዝ ኃይል ከመጨረስ ተቆጥበን ቶሎ ወደ ድል ማምራት እንችላለን።
ያም ሆነ ይህ በየሳምንቱ አምባገነን እያሉ የሚወተውቱት ምሁራን በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው የችግሩን ምንጭ ያለመረዳት ችግር ውስጥ እየከተቱን ነው። በየሳምንቱ ከየአቅጣጫው በዚህ መልክ የሚቀርበው ትንተና ልክ እንደ ድረግ ጭንቅላታችን ውስጥ በመተከል አምባገነን ካለወረደ እያለን በመወትወት ለሌላና ለሳይንሳዊ ትንተና በር በመዝጋት ያለንን የተመሰቃቀለና የተወሳሰበ ችግር ለሌላ መቶ ዐመት እንዲተላለፍ እያደረግን ነው። ህዝባችንም ዘለዓለሙን ድህነትና ስቃይ ከእግዚአብሄር የተላከበት መጥፎ ዕድሉ አድርጎ በመውሰድ እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ በማድረግ የውጭ ኃይል በተለያየ መልክ አገሩን ሲወርና ባህሉንና ታሪኩን ሲያበላሽ እንዲመለከት በማድረግ የታሪክ ወንጀል በመስራት ላይ ነን ብል የምሳሳት አይመስለኝም።
የፅንሰ-ሃሳብን አመጣጥና ትርጉም የመረዳት አስፈላጊነት!
በታሪክ ውስጥ ብቅ ብቅ ያሉና አንድን ነገር ወይም ስርዓትን መግለጫ ፅንሰ-ሃሳቦች ዝም ብለው በጥራዝ ነጠቅ ወይም በአክራሪዎች የሚወረወሩ ሳይሆኑ፣ ከፍተኛ ዕውቀት በነበራቸውና በአላቸው የሰውን ልጅ ስልጣኔ በትክከለኛ መነፅር በሚመለከቱ ምሁራን ነበር። የፅንሰ-ሃሳቦችም አፈላለቅ በየታሪክ ኤፖኩ የነበሩትን አደገኛ፣ ለሰላምና ተቻችሎ ለመኖር የማያመቹ አገዛዞችን መግለጫዎች ነበሩ። ለምሳሌ ኢምፔሪያል ወይም ኢምፔሪያሊስት የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሙት ፕላቶና ቱካይዳይደስ (Thucydides) ሲሆኑ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት በአምስተኛውና በአራተኛው ክፍለ-ዘመን የነበረውን ከጦርነትና ከህዝቦች ዕልቂት ጋር የተያያዘ የጥቂት ገዢዎችን ብልግናና ቅጥ ያጣ ስረዓት መግለጫ ነበር።በሁለቱም ፈላስፋዎችና የታሪክ አዋቂዎች ዕምነት የዚያን ጊዜው የአቴኑ የመስፋፋትና ሌሎች ነፃ አገሮችን በራስ ተፅዕኖ ስር ማድረግ ዋናው ምንጩና ምክንያቱ ስግብግብነትና (Greed= pleonexia) ሶፊስታዊ የተሳሳተ ዕውቀት መሆኑን ያብራራሉ።
በላቲን ቋንቋ ደግሞ ኢምፔሪያሊዝም ማለት መስፋፋትና ተፅዕኖን በሌሎች ህዝቦች ላይ ማሳደርና የመጨረሻ ላይም በቁጥጥር ስር ማዋል ማለት ነው። በተለይም በአራተኛው ክፍለ-ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት አቴን በእነፕሬክሊን አገዛዝ ወቅት ኃያል በነበረችበት ዘመን በስፓርታና በሌሎች ደካማ በነበሩ ግዛቶች ላይ ታደርስ የነበረውን ወረራና አሰቃቂ ድርጊት እነ ፕላቶን ይገልጹ የነበረው አገዛዙ ስነ-ምግባር የጎደለውና፣ በእኩልነት መርሆችና የሌሎችን ግዛቶች በማክበር ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ስላልነበር ይህ ዐይነቱ ወረራ ኢምፔሪያሊስት ነው እያሉ ነበር። በፕላቶንና በተከታዮቹ ዕምነት ይህ ዐይነቱ የሌሎችን መብት በእኩልነት መኖር አለማክበር ከውስጡ በእኩልነትና በዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ላይ ካልተገነባ አገዛዝ ጋር በማያያዝ ነው።
በሌላ ወገን ደግሞ እነ ፕሬክሊን በጊዜው የነበረውን ኃያልነታቸውንና ወራሪነታቸውን ይገልጹ የነበረው አቴን ከሌሎች የበለጠችና ለዚህም የተባረከች ስለነበረች በሌሎች ላይ የበላይነቷን የማስፈንና የእነሱን ዕድል የመወሰን መብት አላት ብለው ነበር የሚከራከሩት። ዛሬም በሞራል ውድቀት የበሰበሰው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ስንትና ስንት ሺህ ህዝቦችን እየገደለና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦችንም ለመጨረስ የሚያስችለው መሳሪያ እየሰራ ከሌሎች አገሮች በሞራል የምበልጥና የሰውን ልጅም ዕድል እኔ በምፈልገው መልክና ርዕይ ነው መቀረጽና መከተል አለበት እያለ የሚሰብከውና መንፈሳችንን የሚያጠበው ከእነ ፕሬክሊን በመማርና፣ እንዲሁም ደግሞ የዓለምን ታሪክና የተለያዩ ህዝቦችን የባህል ዕድገትና ልዩነት መኖር አስፈላጊነት ባለመረዳት ነው። የራሱን ቤት ሳያጸዳና ወደ 40 ሚሊዮን የሚጠጋ አሜሪካዊ አንድ ሰው በቀን መኖር ካለበት የኑሮ ደረጃ እየኖረና የህክምናም ዕድል እንዳያገኝ በተደረገበት አገር እኔ ነኝ የሞራልና የስልጣኔ መመዘኛ ነኝ ማለት የስልጣኔንና የሞራልን ትርጉም በአፍጢሙ ደፍቶ የሰውን ልጅ ዕድገት ከዚህ አንፃር እንደማየትና ተግባራዊ ለማድረገም እንደመሞከር ይቆጠራል።
ወደ ግሪኩ ስልጣኔም ስንመጣ፣ ይህ ዐይነቱ ኢምፔሪያሊስታዊ ፖለቲካና አመለካከት በእነ ፕሬክሊን ስልጣን ዘመን ተቀባይነት ያገኘውና የውጭ ፖሊሲ መመሪያም ሊሆን የበቃው በስልጣን አካባቢ የነበሩ ሰዎች ሶፊስታዊ አመለካከት በነበራቸው፣ እኩልነትን በሚቃወሙና ኦሊጋርኪያዊ አገዛዝን በሚሰብኩና በሚያስተጋቡ ፖለቲከኞች ስለተከበበ ነበር። በሶፊስቶች አመለካከት ማንኛውም ከአንድ አገዛዝ የፈለቀ ህግ ወይም መመሪያ እንደደንብ መወሰድና ማንኛውም ሰው ተግባራዊ ማድረግ ያለበት ነው። ፍልስፍናም ለሰው ልጅ አያስፈልገውም። አንድ አገዛዝ የሚለው ሁሉ ትክክል ስለሚሆን ማንኛውም ዜጋ እሱን መቀበል አለበት። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላም አዲሱ የአሜሪካን ኦሊጋርኪ መደብ የእነ ፕሬክሊንን የተዛባ አመለካከት እንዳለ በመውሰድ ከአገሩ አልፎ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እንዲያገኝ አደረገ።
ይህንን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ግሎባላይዜሽንና የነፃ ንግድን የዕድገት መሰረቶችና አጋዦች አድርጎ በመስበክ የዓለምን ህዝብ ማሳመን ቻለ። ዕውቀት፣ ንቃተ-ህሊና፣ በልዩ ልዩ ነገሮች የሚገለጽ የባህል ዕድገት፣ ሳይንስና ቲክኖሎጂ ሳይሆኑ ለአንድ ህዝብ ወይም አገር የሚያስፈልጉት፣ ንግድና ትርፍ ናቸው በማለት የሰው ልጅ የኑሮ ፍልስፍናና አመለካከቱ በእነዚህ ዙሪያ ብቻ እንዲሽከረከሩ ማድረግ ቻለ። ከዚህ ስንነሳ እነ ፕላቶንም ሆነ ሌሎች በኢምፔሪያሊዝም ዙርያ ምርምር ያደረጉ ምሁራን፣ ኢምፔሪያሊዝም የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ የተጠቀሙትና የሚጠቀሙት አንድን ተስፋፊ አገር ለመስደብ ሳይሆን ተስፋፊነቱንና ወራሪ ባህርይውን ለመግለጽ ነው። ስለሆንም ጽንሰ-ሃሳቡ ሳይንሳዊና ከአንድ ሁኔታ ጋር የሚገናኝ ነው።
ይህ ዐይነቱ ሌሎችን አገሮች መውረርና ስልጣኔያቸውን ማፍረስ በሮማውያን አገዛዝ ዘመንም የተስፋፋና፣ ለግሪክና ለግብጽ ስልጣኔ መፈራረስ፣ እንዲሁም ደግሞ በኋላ ላይ የጨለማው ዘመን ለተባለውና ፊዩዳሊዝም ለሚባለው እጅግ ወደ ኋላ የቀረ አገዛዝ በሩን እንደከፈተና ሁኔታውን እንዳመቻቸ የታሪክ ጸሀፊዎች በመረቃ መልክ ያስረዳሉ። የሮማውያንን አምፔሪያሊስታዊ መስፋፋት ልዩ የሚያደርገው በያዙበት ቦታ ሁሉ የአስተዳደር መዋቅራቸውን አንድ ወጥ ማድረግ ነበር። ይሁንና ግን ፖሊሲያቸው ሌላውን ከማስገበርና ለነሱ ተገዥ ከማደረግ የራቀ ፖሊሲ አልነበረም። ይህም ዐይነቱ በስልጣን መባልግና በተወሰነ ርዕዮተ-ዓለም ታውሮ ይህንን ብቻ ተቀበል፣ ይህንን ካልተቀበልክ ድምጥማጥህን አጠፋሃለው የሚለው አባባልና ተግባር በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተስፋፋና ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ተጠያቂ እንደሆነ የታሪክ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ።
እንዲያውም ብዙ የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ የሰው ልጅ የኑሮ ሁኔታ ሳይንስና ታሪክን በትክክል በተረጎሙና በተረዱ ምሁራን ቢመራ ኖሮ የሰው ልጅ ስቃይ በቀነሰ ነበር እያሉ ነው በደንብ የሚያብራሩት። ይህም ባለመሆኑ በአውሮፓ ምድር ውስጥ አሰቃቂ አገዛዝ መስፈን የቻለው ሃይማኖትን ወደ ሞራል ኮድነት ሳይሆን ወደ ንጹህ ርዕዮተ-ዓለምነት በመቀየርና የስልጣን መሳሪያ በማድረግ የሰውን ልጅ የስቃይ ኑሮ ለማራዘም በተነሱ ጥቂት ኃይሎች አማካይነት ነው። በካቶሊኮችና በፕሮፕቴስታንቶች ለሰላሳ ዐመት ያህል የተካሄደው የርስበርስ ጦርነት ዋናው መነሻው ሃይማኖት ሳይሆን የስልጣን ሽኩቻና ስልጣኔን ከመቀናቀን ጋር የተያያዘ እንደሆነ የታሪክ ዘጋቢዎች በደንብ ያስረዳሉ።
በዚህ ዘመን ኢምፔሪያሊዝም የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ በደንብ ባይስፋፋም፣ የኋላ ኋላ በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የነፃ ንግድ የሚለው መርህ ሲስፋፋ ዋና ዓላማው ኢምፔሪያሊስታዊ እንደነበር ግልጽ ነው። ከነፃ ንግድ ጋር የተያያዘው የኢምፔሪያሊዝም አገላለጽ ግን ከነፕላቶኑ የሚለይበት በቀጥታ የሌሎችን አገሮች ዕድገት ከመቀናቀንና፣ ደካማ አገሮችን ወደ ተራ ተበዝባዥነትና ጥሬ አምራችነት ጋር ከመቀየሩና ተገዢዎች እንዲሆኑ ከማድረግ ጋር የተያዘ በመሆኑ ነው።
ለካፒታሊዝም ማደግና መስፋፋት ከ17ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በአውሮፓው ምድር ውስጥ ተቀባይነት ያገኘው የህብረ-ብሄር ምስረታ ነው። ከ30ኛው ዐመት ጦርነት በኋላ ተቀባይነት ያገኘው የህብረ-ብሄር ምስረታ በጊዜው ብቅ ያሉትን የፍጹም ሞናርኪዎች ወደ ውስጥ የውስጥ ገበያን ማዳበር አስገደዳቸው። የአንድ አገር ጥንካሬ የሚመዘነው በጦርነት ብቻ ሳይሆን የግዴታ ጠንካራና ርስ በርሱ የተሳሰረ ኢኮኖሚ ሲገነባ ብቻ ነው የሚለው አስተሳሰብ በምዕራብ አውሮፓ የፍጹም ሞናርኪዎች የአገዛዝ ዘመን ተቀባይነትን አገኘ። ስለሆነም ወደ ውስጥ ሰፋ ያለና ጠንካራ ኢኮኖሚ ገንብቶ ወደ ውጭ ደግሞ መወዳደር መሰረታዊ የፍጹም ሞናርኪዎች ፖለቲካ ነበር። ይህ ዐይነቱ ወደ ውስጥ ያተኮረ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ግንባታ ለከበርቴው መደብ ማየል ሁኔታውን ሲያመቻች፣ የፍጹም ሞናርኪዎች ደግሞ የውጭ ፖሊሲያቸውን የበለጠ በአመጽ ላይ እንዲመሰረትና ደካማ አገሮችንም ለመውረርና ተገዢያቸው የሚያደርግ ሆነ። ከአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻና ከአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ አፍሪካን ለመቃረም በአውሮፓ ኃያላን መንግስታት መሀከል የሚደረግ ፍጥጫና ሽቅድምድሞሽ ዋናው የዓለም አቀፍ የፖሊታክ ቅየሳ ሆነ።
ይህ ዐይነቱ አካሄድ አጠቃላይ ለሆነ ኢምፔሪያሊስታዊ ወረራና ብዝበዛ በሩን ከፈተ። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ የሆነ ሚሊታራዊ መልክ በመያዝ በብዙ አገሮች መሳሪያዎችም መሰራጨት ጀመሩ። በዚህ ዐይነቱ የወረራ ፖለቲካና ቅኝ ገዢዎችን በቁጥጥር ስር ማድረግ የተነሳ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ዋናው መሳሪያ በማድረግ ቀደም ብለው የማይታወቁ ዛሬ አፍጠው አግጠው የወጡና ብዙ የአፍሪካ አገሮችን የሚያተራምሱ የጎሳ ቦድኖች እንደአሸን ፈለቁ። ድሮ ርስ በርሱ ይጋባና በንግድ አማካይነት ይገናኝና ራሱን የሌላው አካል አድርጎ ይቆጥር የነበረ፣ የባሪያ አጋዛዝ፣ የቅኝ አገዛዝ፣ ቀጥሎ ደግሞ በአዲሱ ዓለም አቀፋዊ የስራ ክፍፍልና በተቀነባበረ ድህነትን ፈልፋይ በሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጎሰኝነት በማቆጥቆጥና ሁሉም በጎሳው መስክ በመመሸግና ከሌላው የተለየሁ ነኝ ብሎ በማመን ወደ ማያልቅ ጦርነት አመራ። አዲሱ ኢምፔሪያሊዝም ከላይ የሱን ጥቅም አስጠባቂና ተጎታች (Vasal) አገዛዝ በማስቀመጥና ህዝቡን በመከፋፈልና በጦርነት በመጥመድ ሀብትን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሊዘርፍ የሚችልበትን መንገድ ዘረጋ። እዚህ ላይ መያዝ ያለበት ዘረኝነትና ፋሺዝም በካፒታሊስት ስርዓት ውስጥ የተፈጠሩና የስርዓቱ አንድ አካል የሆኑ ናቸው። ይህም የሚያሳየው ካፒታሊዝም እንደስርዓት በቅራኔዎች የተወጠረ መሆኑንና እንደሚባለው ሙሉ በሙሉ የሊበራል ዲሞክራሲ መሰረተ-ሃሳቦች የሰፈነበት ስርዓአት አይደለም ማለት ነው።
ለአብዛኛዎቻችን በሊበራል ዲሞክራሲ ለምናምንና፣ የሰውን ልጅ ዕድገት በዚህ ክልል ውስጥ ብቻ በማገናዘብ ለምንተነትንና ለማሳመን ለምንሞክር፣ በመሰረቱ ሊበራል ዲሞክራሲ እየተባለ የሚወደሰው የምዕራቡ ዲሞክራሲ መሰረቱ ካፒታሊዝም እንደሆነ ግንዛቤ ውስጥ የገባ አይመስልም። በአብዛኛዎቻችን ዕምነት ሊበራል ዲሞክራሲ እንጂ ካፒታሊዝም የሚባል ስርዓት የለም። ከዚህ ስንነሳ በብዞዎቻችን ዘንድ ያለው አመለካከት የሊበራል ዲሞክራሲን በሚያራምዱ አገሮች ውስጥ እኩልነት የሰፈነ ስለሆነ ማንኛውም ዜጋ በማንኛውም መስክ በመሳተፍ የኑሮውም ሆነ የፖለቲካና የማህበራዊ ደረጃውን ሊያሳድግ ይችላል የሚል ዕምነት አለ። በሌላ ወገን ግን ሊበራል ዲሞክራሲን እንደስርዓት መውሰድና ሌላውን ለማሳመን መሞከር ሳይንሳዊ አቀራረብ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛ አመለካከት እንደሆነ ብዙ ጥናቶች ያመለክታሉ። እነዚህ ክሪቲካል አመለካከት አላቸው በሚባሉ ምሁራን ትንተና መሰረት የሊበራል ዲሞክራሲን እንደ ስርዓት መውሰድና እኩልነት የሰፈነበት ነው ብሎ ሌላውን ለማሳመን መሞከር የካፒታሊዝምን ውስጣዊ ህጎች አለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ በገሀድ የሚታየውን የሀብት ቁጥጥርና ክፍፍል መዛባት፣ የፖለቲካና የመንግስትን በጥቂት ቡድኖች ስር መውደቅን መካድና ለተሻለ የዲሞክራሲ ሪፎርሞች የሚደረገውን ትግል ለማዘናጋት እንደመሞከር ነው ብለው ይናገራሉ።
ነገሩን ይበልጥ ለመረዳት ኢምፔሪያሊዝም በሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ላይ ትንሽ እንቆይ። ቢያንስ በቅኝ ግዛት ዘመን የነበረውንና በብዙ የአፍሪካ አገሮች ተግባራዊ የሆነውን የብዝበዛና የፀረ-ዕድገት የኢምፔርያሊስት ፓሊሲና ፕሮጀክት የሚክድ የለም ብዬ አምናለሁ። ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የባሪያ ንግድን ማስፋፋት፣ ቀጥሎ ደግሞ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ፖርቱጋል፣ ስፔይን ፈረንሳይና እንግሊዝ ተራ በተራ አፍሪካን ሲወሩና የግዛታቸው ተቀጥያ ሲያደርጉ ዋና ዓላማቸው ጥሬ-ሀብትን መበዝበዝና ወደ ምዕራብ አውሮፓ እንዳለ እያጋዙ ማምጣት ሲሆን፣ በዚያው መጠን ደግሞ በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ምንም ዐይነት ህዝቦችን የሚጠቅም ዕድገት እንዳይመጣ ማገድ ነበር። ስለሆነም የአፍሪካ ገበሬና ነጋዴ ከለመደው ሰራና የስራ ክፍፍል እየተፈናቀለ ለምዕራብ አውሮፓ የጥሬ-ሀብት አምራች እንዲሆን ተገደደ። በዚህም ምክንያትና በተመሰረቱት የጭቆና አገዛዞች ምክንያት ወደ ውስጥ የስራ ክፍፍል እንዳይዳብርና ከተማዎችም እንዳያድጉ ሆኑ። ይኸኛው የስራ ክፍፍል ፕሮጀክትና የአፍሪካ አገሮችን ወደ ጥሬ-ሀብት አምራችነት መለወጥና ተበዝባዥ ማድረግ በተለይም የእንግሊዝ ካፒታሊዝም እያደገ ከመጣና ሌሎችን አገሮች ተበዝባዥ ማድረግ ያስፈልጋል የሚለው መሰበክ ከጀመረ ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ወዲህ ነው። እነ አዳም ስሚዝና እነ ሪካርዶ በቲዎሪ ደረጃ ያስቀመጡት ዓለም አቀፋዊ የስራ-ክፍፍል በመጀመሪያ ደረጃ የግዴታ በአመጽ በመደገፍ ተግባራዊ እንዲሆን መደረግ ተጀመረ።
እንምደሚታወቀው ከአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የሊበራል ዲሞክራሲ ስርዓት ሳይሆን በካፒታሊዝም ሎጂክ ላይ የተመሰረተ፣ ግን ደግሞ ለይስሙላ ያህል የተለያየ አመለካከት ያላቸውን ኃይሎች ሊያሳትፍ የሚችል የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ መቋቋም አስፈላጊ ሆነ። የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲ መስፋፋት በጊዜው የነበረውን የኃይል አሰላለፍ ለውጥ የሚያመለክት ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ የካፒታሊዝምን አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ፕሮጀክት የሚያረጋግጥ አማራጭ የሌለው አንድ ወጥ ኢኮኖሚዊ የአመራረት ሆኖ የተወሰደበት ነው። የካፒታሊዝምንም ከተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርት አንስቶ ወደ ተወሳሰበ የምርት ሂደትና፣ ከዚያም በኋላ ቀስ በቀስ ትናንሽ አምራች ኃይሎችን እያፈራረሰና ወይንም ደግሞ በራሱ ቁጥጥር ስር እያደረገ መምጣትና ወደ ኦሊጎፖሊስቲና ወደ ሞኖፖሊዝምነት መለወጥና ከባንኮች ጋር መዋሃድ ለተመለከተ መገንዘብ የሚችለው፣ እንደዚህ ዐይነቱ ኢኮኖሚያዊ የአመራረት ዘዴ በአንድ ክልል ብቻ ተወስኖ መቅረት እንደማይችል ነው። ይህም ማለት ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ካፒታሊዝም ውስጣዊ-ኃይል እያገኛና እየተስፋፋ በመምጣት ከአገር አቀፍ ደረጃ በማለፍ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ እንደጀመረ ነው። ስለዚህም ገበያን ብቻ ሳይሆን ለዕድገትና ለመስፋፋት የሚያስፈልገውን የጥሬ-ሀብት ለማግኘት የግዴታ ሌሎች አገሮችን አይ በጦርነት፣ ከተቻለ ደግሞ አዳዲስ መስበኪያ ዘዴዎችን እየፈጠረ በቁጥጥሩ ስር ማዋል አለበት። ከዚህ ስንነሳ ማርክስ እንደሚነግረን ሳይሆን፣ ካፒታሊዝም ሁሉንም አገሮች በሱ አምሳል በመቅረጽ በየአገሮች ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት ማምጣት እንደማይችል ነው። ካፒታሊዝም በአገርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባልተስተካከለ መልክ ብቻ ነው መስፋፋት የሚችለው።
ስለሆነም በቅኝ ግዛት የተገነቡትን ወደቦችና ከተማዎች በደንብ ለተመለከተ፣ በጊዜው የኢምፔሪያሊስት ፕሮጀክት እነዚህን አገሮች ለማበልጸግና ዲሞክራሲን ለማስፈን ሳይሆን ብዝበዛን ለማጠናከርና፣ በከፈፍለህ ግዛ ፖሊሲ አማካይነት ጥቂቱን እየጠቀሙ አብዛኛው ደሃና ተራ ሰራተኛ ተበዝባዠ እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ በእነሮዛ ሉክሰምበርግ በበቂው የተተነተነና ኋላም ላይ በሌሎች ክሪቲካል አመለካከት ባላቸው ምሁራን ተቀባይነት ያገኘ ሳይንሳዊ አመለካከት ነው። ይህም ማለት ኢምፔሪያሊዝም በየጊዜው ገፅታውን የሚለዋውጥና እንደየሁኔታው፣ ሳያመቸው በወረራ፣ ሲያመቸው ደግሞ አዳዲስ ዘዴዎችን በመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያልተስተካከለ ዕድገት (Uneven Development) እንዲስፋፋ የሚያደርግ መሆኑን ነው። ለምሳሌ በአብዛኛው የምዕራብ አውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ከሞላ ጎደል የተሰተካከለ ወይም ተመሳሳይ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያ ሲኖር፣ በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ ተመሳሳይ ዕድገት ሊኖር ያልቻለው ዋናው ምክንያት ኢምፔሪያሊዝም እነዚህን አገሮች ዕንቅፋት ስለሆነባቸው ነው። ዕድገታቸውን የሚያጨናግፍ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን በየጊዜው ስለሚፈጥር ነው።
በዚህ መልክ ካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እየወሰደ ሲመጣ የጥሬ-ሀብት ዘረፋን በልዩ መልኩ በቁጥጥር ስር ለማዋል ዓለም አቀፋዊ የስራ ክፍፍል የሚለው ከተግባር ጀምሮ በቲዎሪ ደረጃም በየትምህርት ቤቱ ወይም በየዩኒቨርሲቲዎች የሚሰበክበት መሳሪያ ሆነ። እያንዳንዱ አገር በመጀመሪያ የራሱን የውስጥ ገበያ በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባት አለበት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማዳበር ያስፈልገዋል በሚለው ፈንታ፣ በዓለም አቀፍ የስራ ክፍፍል ውስጥ ቢሳተፍና በሩንም ለዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎች ቢከፍት ዕድገትን ሊጎናጸፍ ይችላል የሚለው ትጥቅ አስፈቺ ቲዎሪ በመስፋፋቱ ለኢምፔሪያሊዝም ቀዳዳ መግቢያ አመቺ ሁኔታ ፈጠረለት። እያንዳንዱ አገር በዚህ ዐይነቱ የስራ ክፍፍል ውስጥም በመካተቱ እንደ ተፈጥሮ ሀብት ዐይነቱና አቅራቢነቱ በዚያው ተወስኖ በመቅረት የየአገሮች ዕድል በእንደዚህ ዐይነቱ ኢምፔሪያሊስታዊ ፕሮጀክት ውስጥ በመካተቱ ዕድገቱ የተኮላሸ ሆነ። ምርታዊ ክንውንና የፍጆታ አጠቃቀም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ በመውሰድ የስራ መስክ ዕድል ማግኘትና ገቢ አግኝቶ ፍጆታን ገዝቶ መጠቀም የማይችለው ሁሉ በእንደዚህ ዐይነቱ የስራ ክፍፍል ውስጥ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችል መሰለው።
ይህ ዐይነቱ ዓለም አቀፋዊ የኢምፔሪያሊስት ፕሮጀክት ከላይ በተዘረዘረው ጥንታዊ ወይም ክላሲካል መንገድ ብቻ የሚሰራ ሳይሆን የየአገሮችን ዕድል ለመወሰንና በዚያው ባሉበት ብቻ ረግተው እንዲቀሩ ሰፊና የተወሳሰብ ኔት-ወርክ ዘርግቷል። በዙሪክ/ስዊዘርላንድ መቀመጫውን ያደረገው የሂሳብና የፊዚክስ ተመራማሪዎች ቡድን ከረዠም ጊዜ ጥናትና ምርምር በኋላ ያገኘው ውጤት በአሁኑ ጊዜ የዓለምን ኢኮኖሚ የሚቆጣጠሩ 147 የሚሆኑ ትላልቅ የኢንዱስትሪ፣ የባንኮችና የኢንሹራን ኩባንያዎች እንዳሉ ነው። በኒዚህ ስር የሚተዳደሩ ሌላ ከ40,000 በላይ የሚሆኑ ኩባንያዎች እንዳሉና፣ 147ቱ ትላልቅ ኩባንያዎች ከ40% በላይ የሚሆነውን ኔት-ወርክ ይቆጣጠራሉ። ከዚህም በላይ እነዚህ 147 ትላልቅ ኩባንያዎች ሜዲያዎችን፣ ፖለቲካን፣ ቲንክ-ታንክ ግሩፖችን፣ መንግስት-ነክ ያልሆኑ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶችንና ልዩ ልዩ መንግስታዊ ኢንስቲቱሽኖችን በመቆጣጠር የሶስተኛውን ዓለም ዕድገት ብቻ ሳይሆን በካፒታሊስት አግሮች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የሀብት ክፍፍል በምን መልክ መዳረስ እንዳለበት ይወስናሉ። በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታትን፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን፣ የዓለም ባንክንና የዓለም የንግድ ድርጅትን በመቆጣጠር በሶስተኛው ዓለም አገሮች ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን እንዳለበትና ዕድገቱም ምን መምሰል እንዳለበት ይወስናሉ። እንደምናየው የኢኮኖሚው ፖሊሲ በየአገሮች ውስጥ ለነሱ የሚያጎበድድ አዲስ ቡችላ መፍጠርና በአንድ በኩል ሀብት ወደ ካፒታሊስት አገሮች እንዲፈስ ማድረግ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ድህነቱ ስር እንዲሰድ ማድረግና ዘለዓለማዊ ተመፅዋች ማድረግ ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን ትላልቅ የአሜሪካንና የእንግሊዝ ባንኮች የክሬዲት ካርዶችን፣ ማስተር ካርድ፣ ቪዛ ካርድና ይህንን የመሳሰሉትን በመቆጣጠር በቀጥታ ሀብት ከልዩ ልዩ አገሮች ወደ ካፒታሊስት አገሮች እንዲፈስ ያደርጋሉ። የወደፊቱ ትልቁ ፕሮጀክት ደግሞ የወረቀት ገንዘብን እንዳለ አጥፍቶ በኤሌክትሮንኪስ ገንዘብ (RFID=Radio Frequency Identification) መተካትና የዓለምን ሀብት ብቻ ሳይሆን የዓለምንም ህዝብና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን በመቆጣጠር አደገኛ ናቸው የሚላቸውና የሚጠረጥራቸውን ማስወገድ ነው ። ይህ ቺፕ ገንዘብ የየሰውን መለያ ቁጥር፣ የስራ ህይወት ታሪክ፣ ትምህርት፣ ሃይማኖት፣ ጎሳና ሌሎችም የወንጀለኛ ሪኮርዶችን የሚይዝ ነው። ከዚህም ባሻገር የሶስተኛው ዓለም አገሮችን እየደለሉና እየመከሩ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንዲሆኑ ማድረግና በነፃ ንግድ ስም ገበያቸውን ልቅ እንዲያደርጉ ማስገደድ የየአገሩ ገበያዎች ሙሉ በሙሉ በትላልቅ የአሜሪካንና የአውሮፓ የዘር ፋብሪካዎችና የእርሻ ኩባንያዎች ቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ የማምረት ኃይላቸውን ማዳከም ነው። በዚያውም መጠንም በላቦራቶሪ ውስጥ የተዳቀለ የእህል ዘር (Genetically Modified Seed) በማስገባት ለብዙ ሺህ ዐመታት ያካበቷቸውን የእርሻና የእህል ዘር እንዲያጡ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ ዓለምን አንድ ወጥ የማድረጉ አካሄድ የተፈጥሮን ህግ የሚፃረርና ለሰው ልጅ ጤንነት ጠንቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሰላም የሚያናጋውና ረሃብንም ሊያስከትል የሚችል ነው። በዚህ መልክ በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም አምባገነናዊ አገዛዝ በመስፈን የዓለም ህዝብ መብት በሙሉ ይገፈፋል ማለት ነው።
ይህም የሚያመለክተው የካፒታሊስት አገር መንግስታት የእነዚህ ትላልቅ ኩባንያዎች ተጠሪዎችና ስራ-አስፈጻሚዎች እንጂ የህዝቦቻቸው ወኪሎች እንዳልሆኑ ነው። የተለያየ ስም እየያዙ በየአራት ዐመቱ የሚመረጡ፣ ዲሞክራቶች፣ ሊበራሎች፣ የክርስቲያን ዴሞክራቶችና ሶሻል ዴሞክራቶች ወይም ሶሻሊስቶች ሙሉ በሙሉ የሚያገለግሉትና የሚያስጠብቁት በየአገራቸው የሰፈነውን የሚሊታሪ ኢንደስትሪያል ኮምፕሌክስና የፋይናንስ ድርጅቶችን ጥቅም ነው። ሰለሆነም የተለያየ ስም ይዘው ስልጣን ላይ የሚወጡ ፓርቲዎች በውጭ ፖሊሲያቸው ተመሳሳይ ናቸው። ያላቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚን የሚሊታሪ ኃይል ተገን በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን የሚያስፋፍ እንጂ የሰላምና የዕኩልነት አፍቃሪዎችና አስከባሪዎች አይደሉም። በየአገሩ ውስጥ አዳዲስ ሰፊውን ህዝብ ይጠቅማሉ የሚባሉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ከመጀመሪያዎኑ ተቃውሞ የሚገጥማቸው-ለምሳሌ በአሜሪካን ኦባማኬር የሚባለው ጥገናዊ ለውጥ- የትላልቅ ኩባንያዎችን ትርፍ ይጋራሉ ተብለው ስለሚገመቱ ብቻ ሳይሆን፣ የዝቅተኛው ህብረተሰብ ክፍል የኢኮኖሚ ስታተስ በዚያው መቅረት አለበት ከሚለው ኋላ-ቀር አስተሳሰብም በመነሳት ነው። እዚህ ላይ ግን የኦባ አስተደዳር ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልገው ፖሊሲ በሙሉ ከኒዎ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ የጸዳ ነው ማለት አይደለም። የኦባማ አስተዳደርና የፖሊሲ አማካሪዎችን ለተመለከተ ከዎል-ስትሪት ጋር የጠበቀ ግኑኝነት የነበራቸውና ያላቸው ሲሆን፣ ቀውሱን ለመግታት በሚል በዝቅተኛ ወለድ አማካይነት ለዎል-ስትሪት ሰዎች ነበር ገንዘቡን የሚያስተላልፉት።
በዚህም ምክንያት የተነሳ የስቶክ ገበያውና ክፍያው (Share) እያደገ ሲመጣና ሀብታሙ የበለጠ ሀብታም ሲሆን፣ ኢንዱስትሪዎች ግን ወደ 15 ሚሊዮን ለሚጠጋ የስራ አጥ የስራ መስክ ሊከፍቱ በፍጹም አልቻሉም። ለዚህም ነው እስከዛሬ ድረስ ቀውሱ በመጠኑም ቢሆን ሊፈታ ያልቻለው። ይህ ብቻ ሳይሆን አሜሪካንን በተጨባጭ የሚገዛው የሚሊታሪ ኢንዱስትሪው ኮምፕሌክስና ከሱ ጋር የተሳሰሩ ወደ አስራስምንት የሚጠጉ የስለላ ድርጅቶች ናቸው። ይህ ዐይነቱ የአገዛዝ አወቃቀር ከአሜሪካን አልፎ ዓለምን ለመቆጣጠርና ዓለም አቀፋዊ አገዛዝ ለማስፈን የሚያስችል ኔት-ወርክ ዘርግቷል። የኤንሴአ(NSA) ሁኔታን ስንመለከት ይህንን ነው የሚያረጋግጠው። በአሁኑ ወቅት ኳንተም ኮምፒዩተር የሚባል በመስራት ዓለምን እንዳለ ለመቆጣጠር በመዘጋጀት ላይ ነው። ይህንን ስንመለከት እኛ ለባራክ ኦባማ የምንጽፈው የልመና ደብዳቤና ጩኸት ተደማጭነት ማግኘት ያልቻለውና የማይችለው፣ በጠቅላላው የአሜሪካን አገዛዝ ነፃ ንግድን የሚያራምድና፣ ይህም ነፃ ንግድ የአሜሪካንን ኮርፖሬሽኖች የሚጠቅም በመሆኑ በኛ አገር ዲሞክራሲያዊ ለውጥና ዕድገት መምጣት ከዚህ ዐይነቱ የነፃ ንግድ መንፈስ ጋር ስለማይጣጣሙ ነው። ዓለምን በሱ ቁጥጥር ስር ከማምጣት ህልምና ስትራቴጂ ጋር በፍጹም የሚሄዱ አይደለም። ባለፉት 60 ዐመታት እንደተረጋገጠው አሜሪካን በአገሮች ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ያስፈልጋል ሲል የሱን ጥቅም የሚጻረሩ አገዛዞችን ለማስወገድና በሱ የጥቅም ክልል ውስጥ ለማምጣት እንጂ በአንድ አገር ውስጥ ዕውነተኛና ህዝባዊ ዲሞክራሲ ተግባራዊ እንዲሆን ስለሚፈልግ አይደለም።
ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወዲህ የተፈጠረው አዲስ ሁኔታ!
እንደሚታወቀው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በአሸናፊነት የወጣበት ወቅት ነው። ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን የወርቅ ክምችትና የውስጥ ሰፊ ገበያና የኢንዱስትሪ መሰረት ተገን በማድረግ ለሱ በሚስማማው መልክ የዓለምን ገበያ ያዋቀረበት ሁኔታ ነበር። በዚህም መሰረት እንደ እነ የዓለም አቀፍ የገንዝብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክና የዓለም የንግድ ድርጅት ይህንን አዲሱን የአሜሪካን ዓለም አቀፋዊ የኢምፔሪያሊስት ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግና ተቀጥያ መንግስታትን ለማፍራት የተቋቋሙ ድርጅቶች ናቸው። በዚያው መጠንም እነዚህ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ያላቸው የሚመስሉ ድርጅቶች በዕድገት ስም እያሳበቡ በምሁር ደረጃ ያልበለጸጉ አገሮችን እንዲያሳስቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፍ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ከውስጥ ዕድገት እንዳይመጣ እገዳ የሚያደርጉ ድርጅቶች ሆነው የወጡበት ወቅት ነው። በተጨማሪም፣ በተዘዋዋሪና ግልጽ ባልሆነ መልክ የዕድገትን ፖሊሲ ለማጨናገፍ በማይቻልበት አገሮች ውስጥ የግዴታ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ በማድረግ ፋሺሽታዊ መንግስታትን በማቋቋም ጠቅላላውን የዕድገት ፕሮጀክት ማክሸፍ ሌላው የአሜሪካን ኢምፔርያሊዝም ፕሮጀክት ነበር። ከኢራን እስከ ቺሌ የተደረጉትን የመንግስት ግልበጣዎች ለተመለከተና በህዝብ የተመረጡ ፕሬዚደንቶችን ማስገደል ዋና ዓላማው በሶሻሊዝም ስም በማሳበብ በየአገሮች ውስጥ ህዝቡን የሚጠቅም የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ ማገድ ነበር።
በዚያው መጠንም የኢንዱስትሪ ከበርቴ መደብ ብቅ እንዳይልና ተወዳዳሪ እንዳይሆን ማደናቀፍ ነበር። ከብራዚል እስከቺሌና አርጀንቲና ድረስ በ60ኛው መጨረሻና በ70ኛው ዓ.ም ያለቁትንና የተገደሉትን ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ስንመለከት አብዛኛዎች የዕውነተኛ ዲሞክራሲ ናፋቂና ለሚድል ክላስ ማበብ የሚያመቹ ነበሩ። በሌላ አነጋገር ሶሾሊዝምን የሰው ልጅ ነፃነት ዋናው ጠላት አድርጎ በማቅረብ በመንግስታት የተደገፉና የሚደገፉ የኢንዱስትሪ ፖለቲካ እንዳይካሄድ ማደናቀፍ ዋና ዓላማው ሶሻሊዝምን መዋጋት ሳይሆን በሶስተኛው ዓለም አገሮች ካፒታሊስታዊ ዕድገት እንዳይመጣና ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ነፃነትን እንዳይቀዳጁ ማድረግ ነበር። ለምሳሌ የምዕራብ አውሮፓንንም ሆነ የአሜሪካንን የካፒታሊዝምን ዕድገት ታሪክና ሂደት ስንመለከት የኢኮኖሚ ፖሊሲያችው ዋናው መሰረት መርካንትሊዝም ወይም በመንግስት የተደገፈ ሁለንታዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነበር።
ይህ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው? የካፒታሊዝምን የዕድገት ታሪክ በደንብ ላጠና የእነ አዳም ስሚዙ የረቀቀው እጅ (Invisible Hand) ተግባራዊ ሊሆን የቻለው በመጀመሪያውኑ ቀደም ብለው ለዚህ የሚያመቹ የባህልና የህብረተሰብአዊ ለውጥና አመለካከት ስለተካሄዱ ነው። በአውሮፓ ምድር ውስጥ የግለሰብ ተሳትፎና ሚና ቀስ እያለ እያደገ የመጣው በመጀመሪያ በሬናሳንስ አማካይነት ሲሆን፣ ይህ ስላልበቃ የግዴታ የሃይማኖት ክፍፍል እንዲደረግ በማድረግ ፕሮቴስታንቲዝም ለአስተሳሰብ መዳበር አመቺ ሁኔታን ፈጠረ። ለምሳሌ የማክስ ዌበርን የካፒታሊዝም መንፈስና የፕሮቴስታንቲዝምን ስነ-ምግባር የሚለውን ግሩም ስራ ስናነብ የምንረዳው ፕሮቲስታንቲዝም በበኩሉ የቱን ያህል ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን እንደፈጠረ እንገነዘባለን። ከዚህም ባሻገር የፕሮቴስታንት ስነ-ምግባር ቀስ በቀስ ተግባራዊ መሆን ለካፒታሊዝም ሙሉ በሙሉ በአሸናፊነት መውጣት በቂ ስላልነበር በ17ኛው ክፍለ-ዘመን የግዴታ የኢንላይተንሜንት አብዮት ማካሄድ አስፈለገ። የሞናርኪስቶች የዲስፖቲዝም አገዛዝ ዘመን ፈተና ውስጥ የወደቀበትና የሪፑብሊክ ምስረታ መንገዱ የተቀደደበት ዘመን ነው።
ከዚህም ጊዜ ጀምሮ ማለት ይችላል የዲስፖቲዝም አገዛዝ እየተዳከመ ሲመጣና የከበርቴው አገዛዝ ቦታውን ሲወስድ ግለሰብአዊ አስተሳሰብና ድርጊት ህብረተሰብአዊ ተቀባይነት እያገኙ መምጣት ቻሉ። ይህም ማለት ግለሰብአዊነት ከሰው ልጅ ጋር አብሮ የተወለደና ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ያለ ሳይሆን፣ በአንድ የታሪክ ወቅት በተከሰተ ሁለንታዊ የአስተሳሰብና የባህል፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ አወቃቀር ለውጥ የተነሳ የተፈጠረ ድርጊት ነው ማለት ይቻላል። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ በተለይም የተፈጥሮ ሳይንስ የበለጠ የመፈናፈኛ ዕድል እያገኘ በመምጣቱ ለካፒታሊዝም ዕድገት መሰረት ጣለ። ይህም ሆኖ የግዴታ የመንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ ገብቶ የማኑፋክቱር አብዮት እንዲካሄድ ማድረግና የውስጥ ገበያ እንዲስፋፋ መንገዱን ማዘጋጀት የየመንግስታቱ ዋና ፖሊሲ ነበር። ይህም የሚያመለክተው ግለሰብአዊነትና ግለሰብአዊ ነፃነት ወደ ተግባር ሊለወጡ የሚችሉት የግዴታ የባህል ለውጥ ሲካሄድ ብቻና ግለሰቦች ራሴ ጥሬ ግሬ ሀብትም ማግኘት እችላለሁ የሚለውን ሲረዱ ብቻ እንድሆነ የአውሮፓው የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ያረጋግጣል። ከባህልና ከህብረተሰብአዊ ለውጥ በፊት የግለሰብ ድርጊቶች በታሪክ ውስጥ አልታዩም። ወይም ደግሞ በተራ አዋጅ የሚሆኑ አይደሉም። በአንፃሩ ግን ወደ ሶስተኛው ዓለም ወደሚባሉት አገሮች ስንመጣ በመንግስት የሚደገፉ ወይንም የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ሁሉ ከሶሻሊዝም ጋር አየተገናኙ ዘመቻ ይካሄድባቸዋል፤ መንግስታቱ በዚያው ሲገፉበት ደግሞ የመንግስት ግልበጣ ሙከራ ይደረግባቸዋል። በአንዳንድ አገሮችም ፕሪዚደንቶች ይገደላሉ። ለዚህም ዋናው ምክንያት ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ሶሻሊዝምንም ለመዋጋት ሳይሆን የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም ላቲን አሜሪካና አፍሪካ አውሮፓውያን የሄዱበትን የዕድገት ፈለግ ወይንም የመሰላል መወጣጫ ዘዴ መከተል የለባቸውም፤ ባሉበት ቀጭጨው መቅረት አለባቸው ከሚለው አደገኛ አመለካከትና የሰውን ልጅ እኩልነት ከሚፃረር አስተሳሰብ በመነሳት ነው።
ወደ አፍሪካ ስንመጣ ከቅኝ አገዛዝ ተላቀው የፖለቲካ ነፃነት የተቀዳጁ አገሮች በሙሉ ከባድ ፈተና ውስጥ ወድቀው ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ የወረሱት ኢንስቲቱሽንና የመንግስታት አወቃቀር የቅኝ ግዛት አስተዳዳሪዎች ያዋቀሯቸውና ለብዝበዛ የሚያመቹ ነበሩ። በሌላ አነጋገር ለውስጥ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት የሚያመቹ አልነበሩም። በሁለተኛ ደረጃ፣ ብዙ አገሮች ከፍተኛ የሆነ የምሁር ክፍተት ነበራቸው። አሁንም በሌላ አነጋገር ከውጭ የሚመጣውን ማንኛውንም የኢኮኖሚ ፖሊሲና ርዕዮተ-ዓለም ለመመርመርና ለየአገሩ ተስማሚ ሊሆን የሚችል የኢኮኖሚና የሶሻል ፖሊሲ የሚነድፍ ሰፋ ያለ የምሁር ኃይል አልነበራቸውም። በሶስተኛ ደረጃ፣ አብዛኛዎቹ አገሮች ወደ ውስጥ የተሰፋፋ የስራ ክፍፍልና የውስጥ ገበያ አልነበራቸውም። በዚህም ምክንያት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋሙት ዓለም አቀፋዊ ኢንስቲቱሽኖችና የዓለም ገበያ የአፍሪካን ዕድገት ወሳኞች ነበሩ። አሁንም ናቸው። ስለሆኑም ሁሉም አገሮች ተመሳሳይ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲከተሉ ተገደዱ። የህዝቦቻቸውን መሰረታዊ ፍላጎት እያሟሉ ቀስ እያሉ ከማደግ ይልቅ በተወሰኑ የፍጆታ ምርቶች ላይ ያተኮረ የምትክ ኢንዱስትሪ ተከላ (Import-Substitution Industrialization) ኢምፔርያሊስታዊ ፕሮጀክት በመከተል ዕድገታቸው እንዲሰናከል ወይም እንዲጨናገፍ ሆነ። የባህልና የትምህርት ለውጥም ስላልተካሄደ ሰፋ ያለ ዕድገት ማምጣት አልተቻለም።
ከዚህ በሻገር በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አገሮች እስካሁን ድረስ ነፃ የሆነ የራሳቸው የገንዘብ ፖሊሲ እንዳይኖራቸው ተደረገ። የውጭ ከረንሲያቸው በመጀመሪያ ደረጃ ከፍራንክ ጋር፣ አሁን ደግሞ ከኦይሮ ጋር በመያያዙ የገንዘብ ፖሊሲያቸውን እንደያስፈላጊነቱ ሊለዋውጡ እንዳይችሉ ተደረጉ። ይህ ብቻ ሳይሆን በፈረንሳይ ቁጥጥር ስር የነበሩ ወደ አስራአራት የሚጠጉ አገሮች ነፃነታቸውን ተቀዳጁ ከተባለ በኋላ ከውጭ ንግድ የሚያገኙትን የውጭ ገንዘብ 60% የሚሆነውን የፈረንሳይ ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ ነው ማስቀመጥ ያለባቸው። በውጭ የተከማቸውን የወርቅና የውጭ ምንዛሪ መጠንም የማወቅ መብት የላቸውም። እነዚህ አገሮች አሁንም በቅኝ ግዛት ቁጥጥር ውስጥ እንዳሉ ሆነው ነው የሚታዩት። በዚህ መልክ ዕድገታቸው እንዲጨናገፍና ዕውነተኛ ነፃነት እንዳያገኙ ሆኑ። ይህም የሚያመለክተው የአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች አምባገነንነት ከውጭ ከመጣውና በአገዛዞች ላይ ከተጫነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በዚህ ዐይነቱ ጭቆናዊ አገዛዝ ፈረንሳይና ሌሎችም ኢምፔሪያሊስት አገሮች በቀጥታ እንዳሉበት ነው። የአምባገነንነትና የጭቆናው አገዛዝ፣ እንዲሁም የፀረ-ዕድገት ፖሊሲው አንድ አካል ናቸው ማለት ነው።
ወደ የመንግስታቱ የመኪና አወቃቀር ስንመጣ፣ ከሲቪል ቢሮክራሲው አንስቶ እስከ ጸጥታ ኃይሉ፣ ፖሊስና ወታደር ድረስ አንዳንዶች በአሜሪካን ርዕዮተ-ዓለም ሲሰለጥኑ፣ የተቀሩት ደግሞ በእንግሊዝና በፈረንሳይ የሚሊታሪ ኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ቁጥጥር ስር ያሉ እንጂ በነፃ በየአገሮች መሪዎች የየአገሩን ሁኔታ በሚመለከት ረገድ የተደራጁ አይደሉም። በዚህም ምክንያት በስድሳኛውና በሰባኛው፣ አልፎ አልፎም በሰማኒያኛው ዐመተ ምህረቶች የተካሄዱት ወደ ስድሳ የሚጠጉ የመንግስት ግልበጣዎች በሙሉ በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝና በአሜሪካን የተካሄዱ ናቸው። የየመንስታቱም አምባገነናዊ ባህርይ ላይ ከገለጽኩትና ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ከተቀናጀው የዓለም ኢኮኖሚ፣ የፓለቲካና የሚሊታሪ ሁኔታ ጋር የሚያያዝ እንጂ የአፍሪካ መሪዎች በአፈጣጠራቸው አምባገነን ስለሆኑ አይደለም። በሌላ አነጋገር ከውስጥ ህብረተሰብአዊ ለውጥ ባለመካሄዱና ኢንስቱቲሽናዊም ግንባታ ስለሌለ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያሉ መሪዎች ቀድሞ የተገነባውን የሚሊታሪና የፀጥታ መሰረት በመጠቀም ስልጣናቸውን ለማጠናከር ይገደዳሉ። ከውስጥ ለውጥ ለማምጣት የሚያስቡ ከሆነ ደግሞ የግልበጣ መኩራ ይደርግባቸዋል፤ ወይም ይገደላሉ። ለምሳሌ ሳንካራ ለውጥ አመጣለሁ፣ የአገሩንም ሀብት እቆጣጠራለሁ ስላለ ነው ለፈረንሳይ ታማኝ በሆነው በአገሩ ሰው እንዲገደል የተደረገው። እነ ፕሬዚደንት ንክሩማ፣ ፓትሪስ ሉቡምባና ፕሬዚደንት ኦቦቴ ከስልጣን እንዲወገዱና እንዲገደሉ የተደረገው በሲአይኤ፣ በእንግሊዙ የስለላ ድርጅትና በሞሳድ አማካይነት ነው።
ዛሬም ያለው ሁኔታ የሚያረጋግጠው አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግስታት በምዕራቡ የስለላ ድርጅት የተተበተቡና የሚሰለጥኑትም በምዕራቡ፣ በተለይም በአሜሪካኑ የሚሊታሪ አሰለጣጠን ዘዴ ነው። በተለይም አሁን ከቻይና ጋር ባለው የጥሬ ሀብት እሽቅድምድሞሽ የተነሳ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አፍሪኮም የሚባል የወራሪ ጦር በማደራጀት ከ 53 የአፍሪካ መንግስታት ጋር የጦር ግኑኝነት ተፈራርሟል። ብዙ የአፍሪካ መኮንኖችም አሜሪካን ድረስ እየሄዱ ይሰለጥናሉ። ከዚህ ባሻገር ኮለኔል ጋዳፊ ከሞቱ በኋላ መንገዱ ክፍት ስለሆነ በማሊ የተነሳውን የቱዋሬግ ኖማዶችንና የእስላሞችን ጥምር ግፊት ለመግታትና አልቃይዳን ለመዋጋት በሚል የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ኒጄር ውስጥ የጦር ካምፕ በማቋቋም ከዚያ በመነሳት ጠቅላላውን አፍሪካን በራሱ ቁጥጥር ስር ለማድረግ እየጣረ ነው። ከአንዳንድ የድሮ የኢትዮጵያ ኦፊሰሮች ለእነኦባማ `ምክር` ከመለገሱ በፊት፣ ሲአይኤና ሌሎች ወደ 17 የሚጠጉ የስለላ ድርጅቶች ለአሜሪካን አጠቃላይ ኢምፔሪያሊስታዊ ፕሮጀክት አስፈላጊውን የቤት ስራ ሰርተውለታል። ስለዚህም ፕሬዚደንት ኦባማ ከኢትዮጵያውን `የዲሞክራሲ ጠበቃ ባዮች ነን` ምክር የሚያስፈልገው አይመስለኝም። በየአገሮችም ውስጥ ባስፈለገው ጊዜ ብጥብጥ ለማንሳት ይችል ዘንድ የስለላና የስልጠና መረቦችን ዘርግቷል።
በዚህ መልክ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በጥንታዊው የኢምፔርያሊዝም የወረራ ስልት ብቻ ሳይመካ በየአገሮች ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ይችል ዘንድ ሁለንታዊና የረቀቀ እንዲሁም የተወሳሰበ ኔት-ወርክ ለመዘርጋት በቅቷል። አፍሪካ በምንም ዐይነት የማደግና ራሷን የመቻል ዕድል እንዳይኖራት ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ አዘጋጅቷል። ከዚህ ዐይነቱ የስግብግብነት ባህርይው በመነሳት ነው ከረዠም ጊዜ አንስቶ ሲአይኤ አንዳንድ ሊቢያዎችን በማሰልጠን ጊዜውን ጠብቆ በሊቢያው ኮለኔል ሙአመር ጋዳፊ ላይ ህዝቡ እንዲነሳ ያደረገውና፣ ፕሬዚደንቱም እልክ የተጋቡት። እንደሚታወቀው ፕሬዚደንት ጋዳፊ የአፍሪካን አንድነት ለማጠናከር በፖለቲካም ሆነ በኢኮኖሚ ድጋፍ ይሰጡ እንደነበር ይታወቃል። የራሳቸውን አንዳንድ ምኞትና ስህተት ወደ ጎን ትተን- ከባህል የመጣ ችግር- አፍሪካ ራሷን እንድትችል በወርቅ የሚደገፍ፣ ዲናር-ወርቅ የሚባል የውጭ ገንዝብ ወይም ከረንሲ ተግባራዊ ለማድረግ ሽር ጉድ ይሉ እንደነበር ይታወቃል። የሚሸጡትንም ዘይት በአሜሪካን ዶላር ሳይሆን በኢሮ እንዲከፈል ዕቅድ ነበራቸው። ከዚህ በላይ ኮለኔል ጋዳፊ የመጀመሪያውን የአፍሪካ የሳቴላይት ግኑኝነት እንዲቋቋም ከፍተኛውን ወጭ በብድር መልክ የለገሱ ነበሩ። እ.አ በ1992 ዓ.ም 45 የአፍሪካ አገሮች ከአውሮፓ ጥገኝነት ለመላቀቅ ሲሉ የሳቴላይት ኩባንያ ያቋቁማሉ። ፋይናንስ ለማድረግ እ.አ እስከ 2005 ዓ.ም ድረስ ከአውሮፓው አንድነት ጋር ይደራደራሉ። የአውሮፓው አንድነት እምቢ ይላል። በዚህን ጊዜ ፕሬዚደንት ጋዳፊ $ 300 ሚሊዮን ብድር ይሰጣሉ። የአፍሪካ የዕድገት ባንክና የምዕራብ አፍሪካ ባንክ $50ና $27 ሚሊዮን ያክሉበታል። በተጨማሪም ራሺያና ቻይና ርዳታ ይለጉሷቸዋል። በዚህም ርዳታ አማካይነት አፍሪካ በታሪኳ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሷን ነፃ የግኑኝነት ሳተላይት ማቋቋም ትችላለች። ከዚህ በተረፈ ሙአመር ጋዳፊ ሰፋ ያለ የባቡር ሀዲድ ለመዘርጋትና የአፍሪካ የውስጥ ገበያ እንዲቋቋም ምኞትና ዕቅድ ነበራቸው።ይህ ጉዳይና የአፍሪካን ከረንሲ ተግባራዊ ለማድረግ ማቀድ በአሜሪካንና በአውሮፓ እንደክፉ ነገር ይታይ ስለነበር የግዴታ ኮለኔሉ መወገድ ነበረባቸው። ስለሆነም ይህንን የኮለኔል ጋዳፊን ህልምና ዕቅድ ለማጨናገፍ ጊዜ ይጠብቁ ነበር፤ መንገድም ያመቻቹ ነበር።
ወደ ውስጥ ፖለቲካቸው ስንመጣ እንደሚባለውና እንደሚነፍሰው የሊቢያ ህዝብ በችግር ውስጥ የሚኖር አልነበረም። በእርግጥ አንድ አገዛዝ ነበር። የምዕራቡ ዐይነት ዲሞክራሲም አልነበረም። ይሁንና ሰፊው የሊቢያ ህዝብ የዘይት ውጤቱ ተጠቃሚ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ ኮለኔል ጋዳፊ ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ማንበብና መጻፍ የሚችለው ህዝብ 25% ብቻ ነበር። በአሁኑ ጊዜ 83% ነው። 2ኛ) መብራት በነጻ ነው፤ 3ኝ) ማንኛውም ዜጋ ብድር ካለወለድ የማግኘት መብት አለው። 4ኛ)እያንዳንዱ ሊቢያዊ በነጻ ቤት ይሰጠዋል። 5ኛ) አዲስ ለሚጋቡና ቤተሰብ ለመመስረት ለሚፈልጉ በነጻ $ 50 ሺህ ይሰጣቸዋል። 6ኛ) ማንኛውም ሊቢያዊ ትምህርት በነጻ ነው የሚማረው። ውጭ የሚማር፣ በተለይም የህክምና ትምህርት ለመማር የሚፈልግ በየወሩ $2, 500 ይሰጠዋል።7ኛ) ለማረስ የሚፈልግ መሬት፣ የገበሬ ቤት፣ የእርሻ መሳሪያና ዘር በነጻ ይሰጠዋል። 8ኛ) አንድ ሊቢያዊ አዲስ መኪና ለመግዛት ሲፈልግ መንግስት 50% በነጻ ይሸፍንለታል። 9ኛ)አንድ ሌትር ቤንዚን 0.14$ ነው የሚያወጣው። 10ኛ) አንድ ሰው ትምህርቱን ጨርሶ በሙያው ቶሎ ስራ ካላገኘ፣ እስኪያገኝ ድረስ የአገሪቱ አማካይ የወር ደሞዝ ይከፈለዋል። ጋዳፊ እስከሞቱ ድረስ ሊቢያ ምንም የውጭ ዕዳ አልነበረባትም። እንዲያውም በምዕራብ ባንክ ውስጥ ከ$150 ቢሊዮን በላይ በህዝቡ ስም ተቀምጧል። ሀቁ ይህ ከሆነ ለምንድነው በሰውየው ላይ እንደዚህ ዐይነቱ ዘመቻ የተካሄደው?
ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩትና በብዙ ማስረጃዎችም እንደተረጋገጠው የአፍሪካን ዕድገት ለማኮላሸት እንደዚህ ዐይነቱ መሪ መወገድ ነበረባቸው። አገሪቱ ውስጥ ዛሬ እንደምናየው ኬኦስ መፈጠር አለበት። ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ፣ በዚህ ዐይነት ሁኔታ የሰሜን አትላንቲክ የሚባለው የወራሪዎች ጦር የመዝረፍ ዕድል ያገኛል። በዚህ ብቻ ሳያበቃ ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ ከተገደሉና አዲስ መንግስት ከተቋቋመ ወዲህ፣ አዲሱ መንግስት ውጭ የተቀመጠውን ገንዘብ እንዳያገኝ ታግዶበታል። በዚህም ምክንያት የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ተንጠልጥለው እንዳሉ ናቸው። ከዚህም በላይ በተለይም ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች ወደ ሊቢያ እንዳይገቡ የሰሜን አትላንቲክ ጦር መርከቦች እንዳይተላለፉ የባህር ዕገዳ አድርጓል። ውጭ አገር ከዚህ ቀደም ከጋዳፊ መንግስት ስኮላር ሺፕ እየተከፈለው እንዲማር የተደረገው አሁን በችግር ላይ እንደሚገኝ አዲሱ የሊቢያ መንግስት አስታውቋል። ዲሞክራሲና ነፃነት ማለት እንደዚህ ነው። ይህንን ዐይነቱን ዐይን ያወጣ ጣልቃ-ገብነት የኛዎቹም ጋዜጠኞችና ታጋዮች አምባገነኑ ተወገዱ፣ ተገደሉ በማለት ተደስተዋል። በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ከማለት በስተቀር ሌላ የምለው ነገር የለም። አብዛኛዎቻችን ሰፋና ጠለቅ ያለ ኢንፎርሜሽን ሳይኖረን ከፍተኛ ስህተትና ወንጀል እንሰራለን፤ እየሰራንም ነው። ይህም የሚያመለክተውና የሚያረጋግጠው የምዕራቡ ማስ ሚዲያ በሚሰጠው የተሳሳተ ኢንፎርሜሽን ብቻ ስለምንመካና ከዚህ በመነሳት የዓለምን ሁኔታ በተሳሳተ መልክ ስለምናነብ ሚዛን ያለው ፍርድ ለመስጠት ተስኖናል። የራሳችንን ፍርድ ለመስጠት ከሁሉም አቅጣጫ ኢንፎርሜሽኖችና መሰረታዊ ሃሳቦችን ለመሰብሰብና ለማወዳደር ፍላጎት ያለን አይመስለኝም። እንደዚህ ዐይነት ኢትዮጵያኖች ስልጣን ቢይዙ ምን ዐይነት ኢትዮጵያን እንደምናይ ዕድሜውን ይስጠን ከማለት በስተቀር ሌላ የምለው ነገር የለኝም።
ወደ አገራችንም ስንመጣ የአፄ ኃይለስላሴ የመንግስት የሲቪልና የሚሊታሪ ቢሮክራሲ በእንግሊዝና በአሜሪካን እስከተወሰነ ደረጃም በእስራኤሎች የሰለጠነ ስለነበር በአጠቃላይ ሲታይ አገዛዙ ህዝባዊና ብሄራዊ ባህርይ አልነበረውም። በመሆኑም ለዕድገት የሚያመች አልነበረም። እንዲያውም ዕድገትን የሚያጨናግፍ ከመሆኑ የተነሳ ለዲሞክራሲ መብቶች የሚታገሉ ኃይሎችን ማፈኛና መግደያ መሳሪያ ነበር። አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው አንደኛውና ዋናው ምክንያት ይህ በውጭ ኃይል የሰለጠነ ቢሮክራሲ ከውስጥ ሆኖ ለውጥን አፋኝና የኢምፔሪያሊዝምን ፕሮጀክት ተግባራዊ ስለሚያደርግ ነበር። በጠቅላላው ወታደሩ በአሜሪካን ርዕዮተ-ዓለም የሰለጠነ ስለነበር የሶሻሊዝምን ርዕዮተ-ዓለም ለጊዜው የተቀበለ ቢያስመስለውም ወደ ጭፍጨፋና ወደ ጦርነት ያመራው ፊዩዳላዊና በጭንቅላቱ ውስጥ የተቀረጸው የአሜሪካን የሚሊታሪ የጭፍጨፋ ርዕዮተ-ዓለም ስላየለበት ነው።
ይህንን በርዕዮተ-ዓለም መጨፈንና ወደ መጥፎ ተግባር መሰማራት በሳይኮሎጂ ቲዎሪ መነጽርና በፍልስፍና መመርመር ይቻላል። ለምን የቀድሞው ርዕዮተ-ዓለም እንደሚያይልና ኢሰብአዊነት ዋናው ተግባሩ እንደሆነ ማረጋገጥ ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ ማርክሲዝምና ሶሻሊዝም ናቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ለደረሰው የርስ በርስ ጦርነትና ለብዙ ወጣቶች መሞት ተጠያቂው ነው የሚለው ቦታ ሊኖረው በፍጹም አይችልም። እንደዚህ የምንል ከሆነ በክርስትና ሃማኖት ስም በማዕከለኛውና ከዚያ በኋላ ዘመን በብዙ መቶ ሺሆች የሚጠጉ ህዝቦች አልቅዋል። በቁርአንም ስም በቡዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ተገድሏል፤ እየተገደለም ነው። ስለዚህ መጽሀፍ ቅዱስና ቁርአን ወይም ክርስቶስና ነቢዩ መሀመድ ናቸው ለዚህ ሁሉ ህዝብ ተጠያቂዎቹ ብለን ልንደመድም ነው ማለት ነው።
ያም ሆነ፣ ይህ ትላንትም ሆነ ዛሬ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮችም ሆነ በአገራችንም ምድር የተፈጠረውን አምባገነናዊና ፀረ-ዕድገት ሁኔታ በምንመረምርበት ጊዜ ሁኔታውን ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አገሮችን በሱ ቁጥጥር ስር አምጥቶ ከማሸትና ዕድገታቸውን ከማጨናገፍ ስትራቴጂ ውጭ ነጥሎ ማየት እጅግ አደገኛ አመለካከት ነው። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተስፋፋውንም ዓለም አቀፋዊ የትምህርት ሁኔታ፣ በተለይም የሶሻል ሳይንስንና የኢኮኖሚክስን ትምህርት ሁኔታ ስንመረምር ዕውነቱን ከውሸት መለየት እንዳይቻልና ክሪቲካል አስተሳሰብ አዳብሮ ዕውነተኛ ህብረተሰብአዊና አንድን አገር እንደ አገር እንዳትገነባ የተደረገበት ዋናው ምክንያት የውስጡ ከውጭው ኃይል ጋር በመያያዙና በመቆላለፉ ነው። ለምሳሌ ከሁለት መቶ ዐመት በፊት የነበሩትን የትምህርት ዐይነቶች ስንመለከት አብዛኛው በቋንቋ፣ በፊሎሶፊ፣ በሊትሬቸርና በተፈጥሮ ሳይንስ ላይ የተመሰረተ ስለነበር ለዕድገት የሚያመች ነበር። በዚህም ምክንያት በብዙ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ቀደም ብሎ ከተካሄደው ለውጥ ጋር ተያይዞ አዲስ ኢኮኖሚያዊና ህብረተሰብአዊ ዕድገት ለመቀየስ ከባድ አልነበረም።
ወደ አገራችን ስንመጣ ግን በኢምፔሪያሊዝም ስር የተቀናጀው ዕድገትን አጨናጋፊ የሆነው የሶሻል ሳይንስ ትምህርት ጭንቅላታችንን እንድንከፍትና ራሳችንን ተገንዝበን ህብረተሰብአዊ ለውጥ ለማምጣት አላስቻለንም። ይህ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አገሮችን የማደንቆር ፕሮጀክት፣ ውስጥ ካለው የፊዩዳል ባህልና የኢኮኖሚ አወቃቀር ጋር በመጣመር የሰብአዊነት ባህል ከማዳበርና ዕድገት አጋዠ ከመሆን ይልቅ በተለይም በሚሊታሪውና በሲቪል የመንግስት አወቃቀር ውስጥ ለፋሽሽታዊ ድርጊት የሚያመቹ ሁኔታዎችን ፈጠረ። ወደ ተማረውም ስንመጣ ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኛው የተማረው የለውጥ አጋዠ መሆን ያልቻለውና ሰፋ ላለ በሁሉም መልክ ሊገለጽ የሚችል እንስቃሴ ውስጥ ሊሳተፍም ሆነ ራሱም ጀማሪ መሆን ያልቻለው የነበረውና የተዘጋጀው፣ እንዲሁም የተማረው ትምህርት ውስጠ-ኃይሉን ውስን ስላደረጉበት ነው። ምኞቱና ድርጊቱም በአሜሪካን ናፍቆትነትና የበላይነት የሚገለጽ እንጂ ብሄራዊ ባህርይ ሊወስድና ሊያዳብር የቻለ አልነበረም። የብሄረተኝነት ወይም የአገርወዳድነት ስሜት አልነበረውም።
ይህ ማለት ግን አውቆ አገሩን በመጥላት ያደረገው ነገር ሳይሆን ከንቃተ-ህሊና ማነስ የጎደለ ስለሆነ ብቻ ነው። ሳይንቲስቱ ተመራማሪና ፈላስፋው ላይብኒዝ እንዳለው „እየተማርኩና እያወቁ በሂድኩ ቁጥር አገሬንና ህዝቤን እወዳለሁ“ እንዳለው፣ የኛው የስድሳዎቹ ዘመን የተወሰነው አዲስ ትውልድ የላይብኒዝን አንድ ሶስተኛ የሆነ ዕድል እንኳ ማግኘት ስላልቻለ ታሪክን ሊሰራ አልቻለም። ስለዚህም የየካቲቱ አበዮት ሲፈነዳ ብዙ ግልጽነት ያለው ነገር መስራትና ሁኔታዎችን ማቃናት ያልተቻለው እነዚህ ሁሉ ነገሮች በመደራረባቸው ነው። በአጭሩ የአሜሪካን ዓለም አቀፋዊ አገሮችን የማደኽየት ፕሮጀክት ሁኔታውን ስላጨለመብን በቀላሉም ወደትርምስና ወደ ብጥብጥ ገባን። ራሱም ያሰለጠናቸውን ሰዎች ወደ ትግሉ ውስጥ በመክተት ለዕልቂቱ ተጠያቂ ሆነ። በግድያ ውስጥ እንዲሰማሩ በማድረግ ብዙ ምሁርና ወጣት ህይወቱ እንዲቀነጠስ ተደረገ። ዛሬም ያለብን ችግር አገር ወዳድ ስሜትን ከሳይንስና ከፍልስፍና ጋር ለማዋሃድ ወይም እነሱን መሰረት አድርገን ለመታገል ስላልቻልን ብዙ ነገሮች ተምታተው ይገኛሉ። ሁሉም በኢትዮጵያዊነት ስም የሚምልበት ጊዜ ስለሆነ ዕውነቱን ከውሸት በመለየትና በዕውቀት መነፅር በመመልከት መልክ ለማሲያዝ አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ከዚህ ስንነሳ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አገሮችን በማዳከምና ወደ ርስ በርስ ጦርነት እንዲመሩ ማድረግ እስካሁን ድረስ ሊቆይ የቻለው በብዙ ምክንያቶች የተነሳ ነው። እንደሚታወቀው በዓለም ታሪክ ውስጥ የተነሱና የተስፋፉ፣ እንዲሁም ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች ዕልቂት ምክንያት የሆኑ ኢምፓየሮች በራሳቸው ብልግናና ኩራት የመጨረሻ መጨረሻ ሊወድሙ ችለዋል። የቀድሞዎች ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች፣ ፐርሺያ፣ አቴን፣ ሮማውያንና የብሪትሽ ኢምፓየሮች እንደዛሬው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የታደሉ አልነበሩም። ከብሪትሹ በስተቀር የተቀሩት በውስጥ ኢኮኖሚያቸው ደካማና ወደ ውጭ ደግሞ እንደዛሬው የሰውን ጭንቅላት የሚሸፍን የተወሳሰበ ርዕዮተ-ዓለም ስላልነበራቸው ሊቆዩ አልቻሉም። አሜሪካንን ልዩ የሚያደርገው በተለይም፣ ከ1973/74 ዓ.ም የኢኮኖሚ ቀውስ በኋላ ዶላር ከወርቅ ጋር መላቀቁ ትልቅ መፈናፈኛ ሰጥቶታል። ከዘይት ሺያጭ የሚተርፈውና ሪሳይክልድ የሚሆነው የአሜሪካን ዶላር የግዴታ የጦር መሳሪያውን በየጊዜው እንዲያሻሽል አግዞታል። በዚህ ላይ ደግሞ የቻይና በዶላር መትረፍረፍና የአሜሪካንን ስቴት ቦንድ መግዛት ተጨማሪ መፈናፈኛ ሊሰጠው ችሏል። የአሚሪካን ዶላር የዓለም ንግድ መገበያያ መሆን ሌላው ምክንያት ሲሆን፣ አሜሪካን አንድን አገር ለመደብደብ ወይም ለመውረር በሚነሳበት ጊዜ ሊያሰልፋቸው የሚችሉ ኃይሎች አሉ። በተለያዩ አገሮች ያሉት ቫሳል የሚመስሉ አገዛዞች ለአሜሪካን እንደ ኢምፓየር መቆየትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ነፃነትን እንዲያፍን አስችሎታል። ይህ ሁኔታ ግን ዘላቂነት አይኖረውም። የመጨረሻ መጨረሻ የመከስከሱ ጉዳይ የማይቀር የታሪክ ግዴታ ነው።
የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አምባገነንነትን የማጠናከር ኃይል!
በእኛ ታጋይ ነን በምንለው ኢትዮጵያኖች ዘንድ ያለው ችግር የአንድን ፅንሰ-ሃሳብ አመጣጥ ሁኔታና በየትኛው የህብረተሰብ ግኑኝነት ውስጥ መፍለቁና መዳበር እንዲሁም ዓለም አቀፋዊነት ባህርይ መያዝ እንደቻለ አለመረዳት ነው። ከዚህ ስንነሳ አንድን ፅንሰ-ሃሳብ ከራስ አመለካከት ጋር የማይስማማ ከሆነ አለመቀበል ስልታችን ሆኗል። ስለሆነም ለትምህርት የተዘጋጀውን መማሪያና ከውጭ የመጣውን አስተሳሰብ ከአገር ሁኔታ ጋር ይስማማ አይስማማ፣ ዕድገት ያምጣ አያምጣ፣ ህብረተሰብአዊ ስምምነት ይፍጠር አይፍጠር፣ በጠቅላላው ለህብረተሰብአዊ ለውጥ ያለውን ብቃትና ኃይል ሳንመረምር ዝም ብሎ መቀበልና በወጣቱ ጭንቅላት ውስጥ እንደ አንዳች ቫይረስ በማስፋፋት ተለክፎ እንዲቀር ማድረግ ሌላው ችግራችን ነው። የማይስማማንን አመለካከት ደግሞ የአንድን ህብረተሰብ ችግር በደንብ ለመረዳትና መፍትሄም ለመፈለግ ቢያስችልም እሱን ማንቋሸሽ ወይም ደግሞ ላለመቀበል ያለን ፍላጎት ከፍ ያለ ነው።
የኒዎ-ሊበራሊዝም ተቀዳሚና መሰረት የሆነውን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ኒዎ-ክላሲካል፣ በብዙዎቻችን ዘንድ ሚክሮና ማክሮ ኢኮኖሚክስ በመባል የሚታወቀውን ለተመለከተ፣ ቲዎሪው በ1880 ዓ.ም ሲፈልቅ ዋና ዓላማውም በጊዜው የነበረውን የማርክሲዝምን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ለመዋጋት ነበር። መሰረተ-ሃሳቡም የአንድ ህብረተሰብ ችግር ዕውነተኛ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ምርትን ማሳደግ ሳይሆን የሰውን ልጅ አርቆ-አሳቢነት (Rationality) ዋናው የምርምሩ ስትራቴጂ በማድረግ ተጠቃሚነትና አትራፊነትን ከፍ ለማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ መፈለግ ነበር። ማለትም የሰው ልጅ አስተሳሰብ ወደ ንጹህ ተጠቃሚነትና አትራፊነት በመቀነስ በማቲማቲካል ሞዴል መጠናቀርና መቀየስ አለበት። በዚህም መሰረት እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱ ዕድል ወሳኝና የራሱን ገቢ እንደፈለገው የሚወሰንና የሚያወጣ ነው በማለት ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም አስተሳሰብ ማስፋፋት የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስቶች ዋናው የቅስቀሳ ፖሊሲ መሰረት ሆነ።
በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ዕምነት በኢኮኖሚ ውስጥ የሚታዩ ቀውሶችም ከውጭ በሚመጣ ግፊት እንጂ ከስርዓቱ የሚወለዱ አይደለም። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የውጭ ግፊት ሲነሳ ወይም ሲቀንስ ኢኮኖሚው ወደ ሚዛናዊነት ያመራል። በጠያቂና በአቅራቢዎች መሀከል ያለው ግኑኝነት ይስተካከል ይላል። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚክስ ትምህርት የፈለቀው የፊዚክስን የመካኒካልና ስታቲስት ቲዎሪ በወሰዱና እንደመመሪያቸው ባደረጉ ምሁሮች ነው። በነሱ ዕምነትም ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ ምርትና ግኑኝነት የመጨረሻ መጨረሻ ወደ ተስተካከለ ሁኔታ ይመጣል። በኢኮኖሚ ውስጥ የመፈራረስ፣ ራስን የማደስና ከዚያም በመነሳት ለውጥና መተሳሰር የለም። የሹምፔተር ኢኮኖሚና የዳርዊን ኢቮሉሺነሪ ቲዎሪ ግን ይህንን የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ስታቲክ ወይም ቋሚ ቲዎሪ አይቀበሉም። በድርጊትም እንደታየውና እንደምናየው የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ-ኃይሉ ከፍ ያለና በቅራኔዎችም የተጠመደ ስለሆነ የአረጁ ቴክኖሎጂዎችን በመጋፋት ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ፈጠራዎች በሩን ይከፍታል። እርስ በርሱም የተቆላለፈ ስለሆነ ኢኮኖሚያዊ ክንውኑ እንደ ደም ዝውውር ነው ማለት ነው። ይህ ማለት ግን ከቀውስ ነፃ ነው ማለት አይደለም።
የኔዎ-ሊበራል ርዕዮተ-ዓለም ከዚህ ለየት የሚያደርገው ወደ መንግስታት ፖሊሲም መለወጡ ነው። በዚህም መሰረት በአንድ አገር ውስጥ የሚከሰቱ መዛባቶች፣ በውጭ ንግድ፣ በስራ-አጥ፣ በዋጋ ግሽበትና በከረንሲ ከፍና ዝቅ ማለት፣ እነዚህ መዛባቶች ከክስተት ጋር የተያያዙ እንጂ የስርዓቱ ውስጣዊ ባህርዮች አይደሉም የሚል ነው። በዚህ ዐይነት የመዛባት ሁኔታ መንግስታት በኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ ጣልቃ መግባት የለባቸውም። ማድረግ ያለባቸው የተቅዋም መዛባት የሚሏቸውን፣ የሰራተኛውን ደሞዝ ህጋዊ መሰረቱን አላቆ የግዴታ ንጹህ በንጹህ በገበያ ህግ እንዲተዳደር ማድረግ፣ በዚያውም መጠን የካፒታሊስቶችን ኃይል ማጠናከር፣ ገንዘብ ወደነሱ የሚፈስበትን መንገድ ማመቻቸት፣ ለትምህርት፣ ለጤናና ለሌሎች የሶሻል መስኮች የሚወጡትን መቀነስና ምርታማ ወደ ሆኑ መስኮች ማሸጋሸግ፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ የህዝብ ሀብቶችን እንዳለ መሸጥ፣… ወዘተ. ወዘተ. የሚሉ ናቸው።
ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በ1930ዎቹ ውስጥ በቲዎሪ ድረጃ ሲስፋፋ፣ ከ1973/74 የኢኮኖሚ ቀውስ በኋላ ነፍስ እንዲዘራ በማድረግ፣ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ግን ከ1979 ዓ.ም በእንግሊዝ አገርና ቀጥሎም በአሜሪካን ነው። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ካፒታልና ካፒታሊዝም ሙሉ በሙሉ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዲወስዱና የዓለም ማህበረሰብም በሙሉ የኒዎ-ሊበራል የገበያን ኢኮኖሚ ተግባራዊ ማድረግ አለበት የሚባለው ይደመደማል። ለአፍሪካ አገሮች ደግሞ በዋሽንግተን ስምምነት (The Washington Consensus) መሰረት ለነሱ የሚስማማ የተቋም ፖሊሲ (Structural Adjustment Progarm) በቀኝ ወይም አክራሪ ኢኮኖሚስቶች እንደ ዊሊያምሰንና ሚልተን ፍሪድማን በመሳሰሉት የኖቭል ዋጋ ተሸላሚዎች ይረቃል። ይህ ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ መሆን እንዳለበት ይደመደማል። የአፍሪካ መንግስታት እንደፕሮጀክት መወሰድ እንዳለባቸው ይረጋገጣል።
ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ይህ የተቅዋም ፖሊሲ በጋና፣ በናይጄሪያና በሌሎች ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ውስጥ ተራ በተራ ተግባራዊ ይሆናል። እነዚህ የኒዎ-ሊበራሊዝምን አጀንዳ ወይም የተቅዋም ፖሊሲ የሚባለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረጉ አገሮች በሙሉ ገበያቸውን ወደ ውስጥ ከማሳደግና ከማስፋፋት ይልቅ ወደ ውጭ እንዲያተኩሩ ይገደዳሉ። የገበያን ፖሊሲ ተግባራዊ ያደርጋሉ። የተቅዋም ቀውስንም (Structural Crises) ይቀርፋል የተባለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በብዙ ጥናቶች እንደተረጋገጠውና ራሱም የተባበሩት መንግስታት የንግድና የዕድገት ኮሚሽን (UNCTAD) በጥናቱ እንዳረጋገጠው፣ የኒዎ-ሊበራል የተቅዋም ፖሊሲን በአፍሪካ ምድር ውስጥ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወዲህ ብዙ ኢንዱስትሪዎች እንደፈራረሱና ልዩ ዐይነት ቀውስም መከሰት እንደቻለ ነው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በቁጥር እየጨመረ የመጣውን የስራ ፈላጊ ህዝብ የስራ ዕድል መስጠት ያልተቻለበት ሁኔታና ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊና ማህበረሰብአዊ ቀውስ እንደተፈጠረ ይህ ጥናትና ሌሎች ጥናቶችም በሰፊው ዘግበዋል።
በአንጻሩ ግን ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ፕሮጀክት አዲስ አምራች ሳይሆን ተጠቃሚ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል እንዲፈጠር በማድረግ ለከበርቴ መደብ ማደግ መንገዱ እንዲዘጋ አድርጓል። በዚያው መጠንም ይህ አዲስ የምዕራቡን የፍጆታ ዕቃ እየገዛ የሚጠቀም የህብረተሰብ ክፍል ሀብት አካባች ከመሆን አልፎ ከመንግስት መኪና ጋር በመቆላለፍ ልዩ ዐይነት ህብረተሰብአዊ ጭቆና እንዲዘረጋ ማድረግ ችሏል። ኮሙኒዝም የሚባለው አስፈሪው ስርዓት ከተገረሰሰና ግሎባልይዜሽን ብዙ ደሀ አገሮችን በቁጥጥሩ ስር እያዋለ መምጣት ከጀመረ ወዲህ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ወደ ዲሞክራሲና ወደ ነፃነት ሲያመሩ በፍጹም አልታዩም። ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አብዛኛዎችን አገዛዞች የመንግስቱን መኪና የበለጠ ጨቋኝ በማድረግና ሀብታቸውን በጦር መሳሪያ ላይ በማፍሰስ የህዝቡን ነፃነት እየገፈፉ በመምጣት ላይ እንደሆኑ ሁኔታዎች ያረጋግጣሉ።
ይህም ማለት ብዙ የአፍሪካ መንግስታት ኢኮኖሚውና ህብረተሰቡ ከሚችለው በላይ ለመንግስቱ መኪና ሀብት በማፍሰስ የተዛባ ሁኔታን እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል። አሁን ደግሞ አፍሪካ ውስጥ እየተስፋፋ ነው የሚባለው የአልቃይዳ ሴል ብዙዎችን ስላሳሰባቸው አትኩሮአቸው ይበልጥ አሸባሪዎችን ለመዋጋት በሚል እዚያ ላይ ማትኮር እንጂ የተስተካከለና ጤናማ ኢኮኖሚ መገንባት አይደለም። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ራሱ የፈለፈለውንና ያደራጀውን አልቃይዳ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስፋፋትና መንግስታትን በማስፈራራት ቀስ በቀስ አትክሮአቸው እንዲለወጥና ድርጊታቸውም ወደ ጦርነት እንዲያመራ ሊገደዱ በቅተዋል።
ቀደም ብሎም ሆነ ዛሬ ቀንደኛ የአልቃይዳ መሪዎች ከአሜሪካኑና ከሌሎች የስለላ ድርጅቶች ጋር የሚሰሩ ሲሆን፣ ሲሪያ፣ ኢራክና ሊቢያ የሚካሄዱት ጦርነቶች ሆን ተብለው የተቀሰቀሱና መንግስታቱን በውጥረት በመያዝ እንደ አገር እንዲወድሙ ማድረግ ነው። በዚህ ዐይነቱ እርኩስ ስራ ሳውዲዎች ሲኖሩበት፣ የየአገሩ መንግስታት በሶሻልና በኢኮኖሚ መሳሪያዎች ሊፈቷቸው ያልቻሏቸውን ሰፊ ማህበራዊ ችግሮች በመጠቀም በየቦታው አክራሪዎችን በመመልመል በየአገሮች ውስጥ የሃይማኖት ጦርነት እንዲመጣ እየቀሰቀሱ ነው። ይህ ጉዳይ ወደኛም አገር ሊመጣ የሚችልና ለዚህ የተዘጋጁ ወጣት አክራሪዎችም እንዳሉ ይታወቃል። ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ ከዚህ ቀደም የፖለቲካ አክቲቪስት የነበሩ ከመቅጽበት ተገልበጠው አክራሪነትን ማራመድ ጀምረዋል። የተሌቪዥን ጣብያቸውንና እንቅስቃሴያቸውን፣ እንዲሁም በየጊዜው የሚሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ ስንመለከት ከበስተጀርባቸው በሃሳብም ሆነ በገንዘብ የሚደግፏቸው ኃይሎች እንዳሉ መጠራጠር ይቻላል።
የእነዚህ ወጣት አክራሪዎች ዋና ዓላማ በግልጽ ባይታወቅም አንድ ነገር ማለት የሚቻለው በዚህ ድርጊታቸውና ቅስቀሳቸው ከገፉበት በአገራችን ውስጥ በቀላሉ ሊገታ የማይችል ህብረተሰብአዊ ውዝግብ ሊፈጥሩ ይችላሉ። እንደዚህ ባለ ሁኔታ ውስጥ በቂ ዝግጅትና ጥንቃቄ የማያደርግ አገርና አገዛዝ፣ እንዲሁም ደግሞ የታሪክ ኃላፊነትን ሳይሆን የስልጣን ስግብግብነትን የሚያስቀድምና ሁሉንም ነገር በራሱ ቁጥጥር ስር አድርጎ ህብረተሰቡን የሚያሽና የሚያዋካብ፣ ባላሰበው መልክ አገሩን የዚህ ዐይነቱ ዕርኩስ ድርጊት ሰለባ በማድረግ አገራችን በዘለዓለም ትርምስ ውስጥ እንድትኖር ያስገድዳታል። ይህ ሁኔታ በአንድ በኩል የባሰውኑ ለአክራሪዎች አመቺ ሁኔታዎችን ሲፈጥርላቸው፣ በሌላ ወገን ደግሞ አክራሪዎችን ለመዋጋት በሚል የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የስለላ ድርጅቱን ያጠናክራል። በዚህ መልክ በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች የሚሊታሪና የስለላ ተቋም ውስጥ ሰርጎ በመግባት የባሰውኑ አምባገነናዊ ስርዓትና ጭቆና እንዲሰፍን ለማድረግ ይችላል ማለት ነው።
ስለሆነም በብዙ የአፍሪካ አገሮች በተለያየ መልክ የሚገለጽ የሰውን መብት መርገጥና መግፈፍ ተግባራዊ ሲሆን፣ ህዝቦቹም በአገራችው ውስጥ ሁለተኛ ዜጋ ይሆናሉ። ባህላቸውን፣ እሴታቸውን፣ ታሪካቸውን፣ የመንፈስ ነፃነታቸውን፣ እንደ ሰው ሰርቶ መኖርና ቤተሰብ መመስረትና የማስተዳደር አቅማቸውን፣ ባጭሩ ማንነታቸው ተገፎ ታሪክ እንዳይሰሩ ይታገዳሉ። ዛሬ በግልጽ እንደምናየው አብዛኛው የአፍሪካ ህዝብ መሬቱን መነጠቁና የጥሬ ሀብቱ መዘረፉ የዚህ ዐይነቱ በረቀቀ መንገድ በሚካሄድ የአገዛዞች በዓለም አቀፍ የሂራርኪ አገዛዝ ውስጥ መውደቅና የአገርነት ነፃነታቸውን የማጣት ውጤት ነው ። የክርስቲያን ዲሞክራሲ እሴት አለኝ፣ የህግ የበላይነትን አከብራለሁ፣ ለዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊበራል ዲሞክራሲን የማስፋፋ ነኝ የሚለው የምዕራቡ ካፒታሊዝም፣ በተለይም የአሜሪካን ካፒታሊዝም በዚህ መልክ አገሮችን በልዩ ዐይነት የህብረተሰብ፣ የማህበረሰብና የባህል፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የሚሊታሪ ቀውስ ውስጥ በመክተት በተለይም ወጣቶችና ታዳጊው ትውልድ አዲስ ህይወት እንዳይቀምሱና ፈጣሪ እንዳይሆኑ ለማገድ በቅቷል። ኑሮአቸው የጨለመና፣ በየአገሮቻቸውም ዕድል ማግኘት ስለማይችሉ ባህርን እያቋረጡ ወደ ውጭ አገር እንዲሰደዱ ተደርገዋል፤ አየተደረጉም ነው። በመርከብ ላይ እያሉ ህይወታቸን የሚያጡ ደግሞ ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ እንደመጣ ነው የምናየውና ዜናውን የምንሰማው።
ከዚህ ስንነሳ በብዙዎቻችን አምባገነን እየተባሉ በአንዳንድ መሪዎች ላይ የሚለጠፈው ቅጽል ታሪካዊ ሂደቶችን ያላከተተ፣ የዓለም አቀፋዊውን ሁኔታ ያለገናዘበና በጥናቱ ውስጥ ያልጨመረ፣ ነፃነትን የሚያጎናጽፍ ሳይሆን ብዙ ነገሮችን በግልጽ እንዳናይ ከማድረግ አልፎ የዝንተ-ዓለማችንን በውጭ ኃይል እየተሽመደመድን እንድንቀር የሚያደርግ ነው። ይህ ዐይነቱ ሀተታና የተቆነጸለ ግንዛቤ ደግሞ ዕውነተኛውን የክርስትና ሃይማኖትን የፍልስፍና መሰረተ ሃሳብ የሚቃወም ነው። በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የሰው ልጅ በእግዜአብሄር አምሳል እንደተፈጠረና የራሱንም ዕድል ወሳኝ እንደሆነ ያብራራል። አንዱ ለሌላው ጠላት ሳይሆን ወዳጁ፣ አደጋ ሲደርስበት የሚደርስለትና ችግሩን የሚጋራው መሆን አለበት ነው የሚለው። ፍልስፍናም ከዚህ የተለየ መልዕክት የለውም። የሰው ልጅ ፈጣሪና አድራጊ ነው። በማሰብ ኃይሉ ቆንጆ ቆንጆ ነገሮችን በመፍጠር ኑሮውን ያሻሽላል፤ በዚያውም የተረጋጋ ህብረተሰብ ይፈጥራል ይላል። በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው ግሎባል ካፒታሊዝም ግን ይህንን በመጻረር የእያንዳንዱን ዕድል እኔው ነኝ ወሳኝ ይላል። ከዚህም በመነሳት ጥቅሜን ያስጠብቃሉ ከሚላቸው የሰይጣን ኃይሎች ጋር በመሰለፍና በመተባበር፣ እንዲሁም እነሱን በማስታጠቅና በመምከር የድህነቱንና የጭቆናውን ዘመን ያራዝምብናል። እያንዳንዱ ዜጋ ርስ በርሱ በመፈራራት እንዲኖር በማድረግ በዘለዓለማዊ ጦርነት ውስጥ እንዲኖር አድርጓል። የዛሬው በአፍሪካ ውስጥ ጎልብቶ የሚታየው አምባገነናዊ ስርዓት የሚባለው፣ የባሪያ ንግድ፣ የቅኝ-ግዛት፣ የእጅ አዙር ቅኝ-ግዛት አስተዳደርና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዋቀረው ድህነትን ፈልፋይ የሆነው የግሎባል ካፒታሊዝም ውጤት ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ ፀረ-ታሪክና ፀረ-ሳይንሳዊ አቀራረብ ነው።
የወያኔ አገዛዝና የአምባገነንነት ሂደት!
ስለወያኔ አመሰራረት፣ አነሳሰና ማደግ ሙሉ በሙሉ የተሟላ ኢንፎርሜሽን የለንም። ማለት የሚቻለው በኋላ መለሰ ዜናዊ ብሎ ስሙን የለወጠውና ለፕሬዚደትነት፣ ቀጥሎም ለጠቅላይ ሚኒስተርነት የበቃው ዊንጌት ትምህርት ቤት በነበረበት ጊዜ በእንግሊዞች ይመከርና ይሰበክ እንደነበር፣ የብሄረሰብን ጥያቄ ዋናው አጀንዳው እንዲያደርግ ምክር ይሰጠው እንደነበር ሁኔታውን በቅርብ የተከታተሉ ይናገራሉ። ራሱ ውስጥ ከነበረው የዝቅተኛና የአማራ ጥላቻ ስሜት ጋር ተደምሮ ይህንን የተደበቀ ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ከሰይጣን ሁሉ ጋር መተባበር ነበረበት። ከመጀመሪያውኑ ግን በዚህ ዐይነቱ ፕሮጀክት ወደ እንቅስቃሴው ውስጥ ከመግባቱ በፊት የማርክሲዝምን ሌኒንዝምን ካባ አጥልቆ ቀስ በቀስ ስልጣን ላይ በሚወጣበት ጊዜ የኢምፔሪያሊስት ፕሮጀክቱን፣ ወይም ኢትዮጵያን የማዳከሙን ስትራቴጂውን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ግልጽ ነበር።
በግልጽ እንደሚታወቀው መለስ ዜናዊ ጦር ሜዳ ውስጥ በነበረበት ወቅት ፓውል ሂንዘ ከሚባለው በስድሳኛውና በሰባኛው ዓ.ም በቱርክና በአንዳንድ የደቡብ አውሮፓ አገሮች ኮሙኒስቶችንና የግራ አዝማሚያ ያላቸውን ኃይሎች ወይም አአገዛዞች ለማዳከም የሲአይኤን የህቡዕ ጦር ከሚገነቡትና የውስጥ ለውስጥ ከሚያደራጁት ጋር የጠበቀ ግኑኝነት እንደነበረው ነው። እንደሚታወቀው ፓውል ሂንዘ ፖፕ ጆን ፓውልን ለማስገደል ሁኔታውን ያቀነባበረው እሱ እንደነበር መረጃዎች ያረጋግጣሉ። በተለይም ዳንኤለ ጋንሰር ግላዲዮ ወይም የሰሜን አትላንቲክ የህቡ የጎሬላ ጦር በሚለው መጽሀፉ ውስጥ በዝርዝር ጽፏል። መለሰ ዜናዊ ከፓውል ሂንዘ ጋር ብቻ ሳይሆን ጋይሊ ስሚዝ ከምትባለው የሲአይኤ የአፍሪካ ተወካይ ጋር የጠበቀ ግኑኝነት እንደነበረው ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ጋይሊ ስሚዝ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ የሲአይኤ ተወካይና የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን ጥቅም ለማስጠበቅ በምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ጋ የምትንቀሳቀስና ይህንን ርኩስ ስራዋን ተግባራዊ የሚያደርጉ የነፃ አውጭ ድርጅቶችን የምትረዳና፣ በተለይም መሪዎቻቸውን በህቡዕ የምትመለምልና የምታሰለጥን፣ አሜሪካንም ድረስ ሄደው ልዩ ስልጠና እንዲሰጣቸው የምታደርግ የነበረች ሴት ነች።
በኋላም በፕሬዚደንት ክሊንተን የስልጣን ዘመን ልዩ ቦታ ተሰጥቷት ጠዋት ጠዋት ለፕሬዚደንቱ ኋይት ሀውስ እየገባች በምስራቅ አፍሪካ ስለሚካሄደው እንቅስቃሴ አጫጭር መግለጫዎች የምትሰጥ ነበረች። ይህንን ርኩስ ተግባሯን ዕውን ለማድረግ ከመለሰ ዜናዊ ጋር የጠበቀ ግኑኝነት በመፍጠር ወደ ስልጣን እንዲመጣ ካበቁት ሰዎች አንዷ ነበረች። እንደሚታወቀው መለስ ዜናዊ ጦር ሜዳ በነበረበት ጊዜ ለተወሰኑ ጊዜያት ተሰውሮ እንደነበር ይታወቃል። ምናልባትም በዚህ ወቅት ልዩ ስልጠና ለማግኘት በድብቅ አሜሪካን የሲአይኤ ካምፕ ጋ ሄዶ ይሆናል። ለዚህም ነው ካጋሜ፣ ሙሰቬኒና መለሰ ዜናዊ አዲሶች ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣት ዲሞክራቶች ተብለው በዚያን ጊዜ የአሜሪካን ፕሬዚደንት በነበሩት ቢል ክሊንተን ይወደሱ የነበረውና ቀደም ብለውም በተወሳሰበ መንገድ ወደ ስልጣን ላይ እንዲወጡ የተደረገው።
አንዳንዶች የሱ የትግል ጓዶች መለሰ ዜናዊን ማርክሲትና፣ ማርክሲዝምን ሌኒንዝምን እንዳነበበ ይናገራሉ። ከዚህም የተነሳ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ የምዕራቡም ሜዲያ፣ ኮትኳቶቹ ሁሉ ሳይቀሩ በአንድ ወቅት ማርክሲስት እንደነበር ይነግሩናል። ጥያቄው ግን እሱ ማርክሲዝምን ማንበቡና አለማንበቡ ሳይሆን፣ በመጀመሪያ ደረጃ የቱን ያህል ተረድቶታል? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ትርጉሞችን ነው ወይም ኦሪጂናል መጽሀፎችን ነው ያነበበው? በሶስተኛ ደረጃ፣ የኢትዮጵያን የህብረተሰብ ታሪክና የዕድገት ደረጃዎች ገብቶታል ወይ? መመርመር ያለበት ጉዳይ ነው። በአራተኛ ደረጃ፣ መነሳት ያለበት ጥያቄ፣ የወጣለት ማርክሲስት-ሌኒሲስት ከሆነ ለምን የሰውን ልጅ ዕድገትና ዕኩልነት ከሚጠላው ከሲአይኤ ጉያ ስር መወደቅ ተገደደ? በአምስተኛ ደረጃ፣ ማርክሲዝምን ሌኒንዝምን አምኖት ነው የተቀበለው ወይስ ለስልጣን መወጣጫ? እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች በዝርዝር መመመለስና መተንተን ያለባቸው ሲሆኑ፣ ማርክሲዝምን ያነበበ ሁሉ ማርክሲስት ይሆናል ማለት አይደለም። እዚህ በከበርቴው ህብረተሰብ ውስጥ ካፒታሊስቶች ሳይቀሩ እስከ የተለያዩ የፓርቲዎች አመራሮች ድረስና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች በተለይም ዳስ ካፒታልን አብጠርጥረው ያውቃሉ።
በማርክስም ትክክለኛ ትንታኔ ጥርጣሬ የላቸውም። ይሁንና ግን ክርስት ዲሞክራቶች እንደ ክርስት ዲሞክራትነታቸው፣ ካፒታሊስቶችም እንደካፒታሊስትነታቸው ይሰራሉ፤ በዕምነታቸውም ይቀጥላሉ። በውሸት ግን ያልሆኑትን ሆኛለህ እያሉ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ 180 ዲግሪ ተለውጠው ሌላ አቋም ሲወስዱ አይታይም። ስለዚህም ስለ መለስ ማርክሲስትነት ስናወራ ብዙ መመርመርና መጠየቅ ያለብን ጉዳዮች አሉ። በተለይም ደግሞ ከአንድ እጅግ ወደ ኋላ-ከቀረ ህብረተሰብ የወጣ ታጋይ ነኝ ባይ ማርክሲዝምንም ቢያነብ ብዙም ልንጠብቅ የምንችለው ነገር የለም። እንደሚባለው አንድ ሰው መጽሀፍ ብቻ ስላነበበ ሳይሆን ጭንቅላቱ በመጥፎም ሆነ በጥሩ ነገር መቀረጽ የሚችለው፣ በተለይም ለአስተሳሰቡና ለአመለካከቱ ያደገበት ህብረተሰብአዊ አወቃቀርና የማቴሪያል ሁኔታዎች ወሳኝ ናቸው። ማርክስ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢወለድና ቢያድግ ኖሮ ዳስ ካፒታልን መጻፍ ባልቻለ ነበር። ይህም ማለት የአንድን ሰው አስተሳሰብ በመቅረጽ፣ በረቀቀ መልክ ለማሰብና ንቃተ-ህሊናው አድጎ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት ይሰማው ዘንድ በዚያው ህብረተሰብ ውስጥ የተዘረጉት የማቴሪያል ሁኔታዎች ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። ይህ ሁኔታ በሌለበት ደግሞ የሰዎች አስተሳሰብ በጣም ውስን ይሆናሉ ማለት ነው። አሁንም ማክስ ዌበር ስለሰው ልጅ የአስተሳሰብ መቀረጽ (Rationalization Process) ሲያትት ከላይ የተቀመጠውን ቁም ነገር በማስመር ነው። ኖርበርት ኤሊያስም የስልጣኔ ክንውን (The Civilization Process) በሚለው ግሩም መጽሀፉ ውስጥ የማክስ ዌበርን አመለካከትና የአተናተን ዘዴ ይጋራል።
ከዚህ ባሻገር የአንድን ግለሰብ የፖለቲካ አስተሳሰብ ብቻ ሳይሆን የድርጅቱንም አወቃቀርና ርዕዮተ-ዓለም ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል። አንዳንዶች ድርጅቱ ጥብቅ በሆነ የማርክሲስት ሌኒንስት የአደረጃጀት ህግ የተደራጀና፣ ከላይ ወደ ታች ትዕዛዝን ተቀብሎ የሚያስፈጽም ነው ይላሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በማርክሲዝም ሌኒንዝም ስም ይንቀሳቀሱ የነበሩ ድርጅቶች ከሞላ ጎደል ሴንትራላይዝድ የሆነ ተቋም ቢኖራቸውም ይህ ማለት ግን ይህ ዐይነቱ አደረጃጀት ተፈጥሮአዊ ወይም ማርክስ ቲዎሪውን ሲያዳብር ማንኛውም ድርጅት አንድ ወጥ በሆነ መልክ መዋቀር አለበት ያለበት ቦታ የለም። በነገራችን ላይ በብዙ ቢሮክራሲያዊ አደረጃጀቶች፣ የሚሊታሪንም ጨምሮ ሊኖር የሚችለው ሂራርኪያዊ አደረጃጀት ነው። ስለዚህ አንድ ድርጅት በማርክሲዝም ሌኒንዝም ስለሚመራ ነው ሴንትራላይዝድ የሆነ የአደረጃጀት ስልት የሚከተለው ብሎ መደምደም አይቻልም፤ ትክክልም አይደለም። ከላይ እንዳልኩት ለአንድ ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መኖርና አለመኖር፣ ወይም ማዳበርና አለማዳበር ሊወሰን የሚችለው በተወለደበት፣ ባደገበት ሁኔታና በቀሰመው የትምህርት ዐይነት ሁኔታ ነው። በተጨማሪም በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ሰፋ ያለ ህብረተሰብአዊና ምሁራዊ እንቅስቃሴዎች መዳበር ለአንድ ሰው የማሰብ ኃይልና ዲሞክራት መሆን ይረዱታል። ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ክርክር በሌለበት ህብረተሰብ ውስጥ ደግሞ ትንሽ ተማርኩ የሚለው አወቅሁኝ በማለት ወደ አምባገነንነት ማዘንበሉና ዕድገትን የመቀናቀን ኃይሉ ከፍ ሊል ይችላል።
ስለሆነም የወያኔ ወይም የህወአት አደረጃጀትና አስተሳሰብ ከዚህ ውጭ ሊወጣ አይችልም። ይህ ሁኔታና፣ በተለይም ደግሞ ራሱ ትግሬ በኢንዱስትሪ ዕድገት፣ በባህልና በምሁራዊ እንቅስቃሴ እጅግ ወደ ኋላ ቀሩ ከሚባሉት ክፍለ-ሀገሮች ውስጥ አንዱ በመሆኑ ካለምንም ጥርጥር የድርጅቱን ካድሬዎችና አመራሩን ሙሉ በሙሉ በጥላቻና በንቀት ላይ እንዲደራጁና በዚህም እንዲገፉበት ሆነዋል። ከዚህም በላይ በድርጅት ውስጥ ምንም ዐይነት የሃሳብ መንሸራሸርና ምሁራዊ ውይይት ስላልነበር-ብዙ ነፃ አውጭ ነኝ የሚሉ ድርጅቶች ያለባቸው ችግር- የግዴታ አንድ ወጥ አመለካከትና ወደ ፊት የመግፋት ባህርይ ይዘው መውጣት ችለዋል። ስለዚህም ነው ስልጣን ከያዙ በኋላ አመራሩ በተለይም በኢኮኖሚ ፖሊሲ ላይ የተከተለውን መስመር አንስተው መወያየት ያልቻሉት። ምናልባት ኒዎ-ሊበራሊዝምና የማርክሲዝም የኢኮኖሚ አስተሳሰብ አንድ መስሏቸው ይሆናል። ከዚህ ስነሳ ድርጅቱ የኋላ ኋላ አምባገነን እየሆነ ቢመጣምና ሙሉ በሙሉ በኢምፔሪያሊዝም ጉያ ስር ቢወድቅ የሚገርም አይደለም።
ያም ሆነ ይህ የወያኔና የእነ መለስ ዜናዊ ስልጣን አወጣጥ በደንብ የተቀነባበረና የተጠና፣ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ብዙ ኃይሎች የተሳተፉበት ነገር ነው።
1ኛ) አገር ቤት ተራማጅ በሚለው መሀከል የተፈጠረው ሽኩቻና መገዳደል ለነሱ የመደራጀት መፈናፈኛ ሊሰጣቸው ችሏል።
2ኛ) ራሳቸው በአንዳንድ ብሄራዊ ባህርይ አለን በሚሉ ድርጅቶች ውስጥ የታቀፉ ስለነበር ድርጅቶችን ከውስጥ ማዳከም ችለዋል። ከዚህም በመነሳት በነጭ-ሽብር ቀይ ሽብር ትርምስ ውስጥ በመካፈል ለብዙ ታጋዮች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆነዋል።
3ኛ) ራሳቸው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ አካል ስለሆኑ ጠላትን ከወዳጅ መለየት የሚያስቸግርበት ወቅት ነበር። በተለይም በሚሊታሪውና በሲቪል ቢሮክራሲው ውስጥ ይሰሩ ስለነበር ኢንፎርሜሽን በማቀበል ይተባበሩና የደርግን ውስጣዊ ኃይል ያዳክሙ ነበር።
4ኛ) በተለይም ሲአይኤ በሚሊታሪውና በጸጥታው ውስጥ የዘረጋው መስመርና የኢትዮጵያ ወታደር እንዲዳከም ማድረግና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ተራው ወታደርና ኦፊሰሮች ካለምንም አመራር መቅረትና መበታተትን በቀላሉ ስልጣን ላይ እንዲወጡ አድርጓቸዋል።
5ኛ) በአካባቢው አገሮች ያለው አመቺ የመግቢያና የመውጫ መንገድ፣ የኤርትራ ነጻ አውጭ ድርጅት ነኝ ከሚለው ያገኙት የነበረው ዕርዳታና፣ በተጨማሪም ኢትዮጵያን ከሚጠላው ከአረብ አገሮች የሚፈስላቸው ዕርዳታና፣ ወደ ውጭም በነፃ አውጭ ድርጅት ስም የዘረጉት የዲፕሎማሲ ግኑኝነት፣
እነዚህ ሁሉ በአንድነት ተደምረው ስልጣን ላይ ለመውጣትና ፀረ-ብሄራዊና ፀረ-ኢትዮጵያ ድርጊታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲችሉ አግዞአቸዋል። ትግላቸው በሙሉ ፀረ-ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው የጥቁርን የነፃነት ፍላጎት የሚጻረርና፣ ኢትዮጵያም ብዙ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ ያደረገችውን አስተዋጽዖና መንፈስ ሙሉ በሙሉ የሚቀናቀን፣ ፀረ-ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ፀረ-ጥቁር ትግልና የስልጣን አወጣጥ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። ከዚህ በላይ ደግሞ ትግላቸውን የጀመሩት በኢትዮጵያ ምድር አብዮት ፈንድቶ ሞቅ ሞቅ በሚልበት ወቅትና፣ ህዝባችን ከሁሉም አቅጣጫ ትብብር በሚፈልግበት ወቅት ነበር። ከዚህም ስንነሳ ትግላቸው ፀረ-አብዮትና ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-ዕድገት ነበር ማለት ይቻላል። በጠቅላላው በጥቁር ህዝብ ላይ የተሰነዘረ የነጭ ኦሊጋርኪን ኢምፔሪያሊስታዊ ዓላማና ህልም ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ነው።
ስለሆነም መለሰ ዜናዊና ቡድኑ ስልጣን ሲጨብጡ መከተል ያለባቸው ፖሊሲ ከመጀመሪያውኑ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የተደነገገ ነበር።
1ኛ) የአገሪቱን የተቀረውን ጦር እንዳለ መበታተን፣
2ኛ) በደርግ ጊዜ የተቋቋመውንና ብዙ የተወሳሰቡ የጦር መሳሪያዎችን የሚሰራውንና የሚያመርተውን፣እንዲሁም ለወደፊቱም የአገሪቱ ዕድገት ሊያገለግል ይችላል የተባለውን የጦር መሳሪያ ፋብሪካ ማውደም፣- መለሰ ዜናዊ ለምን አፈራረሳችሁት ተብሎ ሲጠየቅ ማንኪያ፣ ሹካና ድስት ይሰራበታል፣ ኢትዮጵያ እንደዚህ ዐይነት ነገር አያስፈልጋትም እያለ ነው ያሾፍ የነበረው-
3ኛ) የአገሪቱን የዘር ባንክ ለአሜሪካ አሳልፎ መስጠትና አገራችን ከአሜሪካን በሚመጣ የእህል ዘር ጥገኛ እንድትሆን ማድረግ፣
4ኛ) አገሪቱን በክልል ደረጃ በማደራጀት የብሄረሰብ ስሜት ዳብሮ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲወድም ማድረግ፣ ባጭሩ የኢትዮጵያን ናሺናሊዝም ስሜት መጥፋት አለበት፣
5ኛ) የአማርኛን ቋንቋ እንዲዳከም ማድረግና ብዙ ቋንቋዎች ፊደል ተቀርጾላቸው ህዝቡ በአንድ ቋንቋ እንዳይግባባ ማድረግና፣
6ኛ) በኒዎ-ሊበራሊዝም ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት ንጹህ የገበያን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ናቸው።
በዚህም መሰረት የአገሪቱ ገበያ ለውጭ ንግድ ክፍት መሆን አለበት። በዚህ መልክ የአገራችን ገበያ በውጭ ሸቀጣ ሸቀጥ ሲወረር፣ በዚያው መጠንም የማምረት ኃይሉ ይዳከማል። ጥገኝነት ይጠናከራል፤ ድህነት በመስፋፋትም ህዝቡ አቅመ-ቢስ ይሆናል።
የመለሰ ዜናዊ ቡድን ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የተከተለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ደግሞ እንመልከት። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲና በተለይም ደግሞ የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም (Structural Adjustment Program SAPs) በነፃ ገበያና በነፃ ንግድ አሳቦ ለካፒታሊስት አገሮች መግቢያ ቀዳዳ መክፈትና የማምረት ኃይልን ማዳከም ሲሆን፣ ከዚህ ባሻገር ወደ ውስጥ ያልተስተካከለ ሀብት በመፍጠርና የተወሰነን የህብረተሰብ ክፍል በማደለብ ከውጭው ዓለም ጋር ተቆላልፎ ድህነትን ማጠናከርና ማስፋፋት ነው።
ዝርዝር የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሳሪዎችን ከመመልከታችን በፊት የተቅዋም ማስተካከያ ፕሮግራም (Structural Adjustment Program) የሚለውን ጽንሰ-ሃስብ ትርጉም እንመርምር። ጽንሰ-ሃሳቡ የአንድን ህብረተሰብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ህሊናዊ አወቃቀሮች የመረዳት ችሎታ አለው ? ወይስ ዝም ብሎ የተወረወረ ነው? በእንግሊዘኛው ስትራክቸር የሚለውን ስንተረጉም የአንድን ነገር ህይወት ያለውንም ሆነ የሌለን ውስጣዊ አቀራረጽና ውስጣዊ አገነባብ መግለጫ ነው። የአንድን ነገር ውስጣዊም ሆነ የውጭውን ሎጂካዊና ስነ-ስርዓት ባለው መልክ መገንባቱን ወይም መዋቀሩን የሚገልጽ ነው። ይሁንና ግን ይኸኛው አተረጓጎም የማይለወጥ(Static) ሲሆን ወደ ህብረተሰብ ስንመጣ ግን የስትራክቸር አጠቃቀም ውስጠ-ኃይልን (Dynamism) መኖር ያመለክታል። ስለሆነም ስለስትራክቸር በምናወራበት ጊዜ በቀጥታ በሚታየው ላይ ብቻ ሳይሆን ወደ ማይታየውም ወደ ውስጥ ገባ ብሎ መመርመር ያስፈልጋል። ይህንን በኢኮኖሚ ላይ ለመመርመሪያ ስንጠቀምበት የአንድ አገር ኢኮኖሚ አወቃቀር ምን ይመስላል? በምን ዐይነት ህጎችስ ይተዳደራል? አንድ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር በግልጽ ከምናየው ሌላ ኢኮኖሚው የሚገዛበት ውስጣዊ ህጎች አሉት ወይ? የሚለውንም መመርመር ያስፈልጋል።
በዚህም መሰረት በአጠቃላይም ሆነ በተናጠል የኢኮኖሚ መስኮችን በመመርመር በአዲስ መልክ የሚዋቀሩበትን ሁኔታ ማጥናትና ማቀድ፣ እንዲሁም ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ ተቋም እንዲዘረጋና የህዝቡ የማምረት ኃይል በማደግ ፍላጎቱን በማሟላት የተሳሰረ ኢኮኖሚ ለመገንባት ነው። የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክን የተቅዋም ፖሊስ ጥናትና ምክር ስንመረምር ግን ጥናቱ ዓለም ሁሉ አንድ ዐይነት መልክ አላት ብሎ ስለሚነሳ የሚሰጠውም ምክር ተራ የፖሊሲ መሳሪያዎችን ተግባራዊ እንድናደርግ እንጂ የአንድን ህብረተሰብ ችግር ከሁሉም አቅጣጫ በመመርመር መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ አይደለም። ማስተካከል ወይም አድጀስትሜንት የሚለውንም ፅንሰ-ሃሳብ ስንመለከትም ምኑ ከምን ጋር ነው የሚስተካከለው? የሚለውን ጥያቄ በምናቀርብበት ጊዜ በፍጹም መልስ አናገኝም። የውስጡ ከውስቱ ሁኔታ ጋ? ወይስ የውስጡ ከውጭው ጋ? ነገሩን ጠጋ ብለን ስንመረመር መስተካከል ወይም አድጀስትሜንት የሚለው የአንድ አገር ኢኮኖሚ ለውጭው ዓለም በሚስማማ መልክ መቀናጅት አለበት የሚል እንጂ ወደ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ይምጣ ማለቱ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል።
በዚህ ዐይነቱ የፅንሰ-ሃሳብ ጨዋታ ዝም ብለን በጭፍናችን እንድንነዳና ገደል ውስጥ እንድንወረወር ተደርገናል። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ ወይም ምክር የዓለም አቀፍ የገንዘብ ችግር ብቻ ሳይሆን እኛው ራሳችን ነገሩ ያገባናል የምንል ሰዎች ጥያቄ ስለማንጠይቅ ብቻ ሳይሆን፣ ስለማናወጣና ስለማናወርድ ከውጭ የሚመጣውን ሃሳብ ዝም ብለን የእግዚአብሄር ቃል ይመስል ተግባራዊ እንድናደርግ ተገደናል። በብዙዎቻችንም ዕምነት ፈረንጅ የሚያመጣው ነገር ሁሉ ትክክል ነው የሚል ዕምነት ስላለን ወይም ከበስተጀርባው በርዕዮተ-ዓለም የተሸፈነና ተንኮልን ያዘለ ነው ብለን ስለማንገምት ዝም ብለን በመቀበልና ተግባራዊ በማድረግ አጠቃላይ የሆነ ህብረተሰብአዊ ቀውስ እንዲፈጠር ለማድረግ በቅተናል። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ህብረተሰብአችን በቀላሉ ሊወጣው የማይችለው በብዙ ነገሮች የሚገለጽ ቀውስ ውስጥ እንዲወድቅ አድርገናል። በአገራችን ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲና ግሎባላይዜሽን ሰተት ብሎ ገብቶ ህብረተሰብአችን በቀላሉ ሊወጣው የማይችለው ቀውስ ውስጥ መክተት በወያኔ ብቻ የሚሳበብ አይደለም። ራሱ ተቃዋሚ ነኝ የሚለውና ምሁሩ ዝም ብለው ማየታቸውና እንደዚህ ዐይነት ፖሊሲ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ ለመመርመርና ለመዋጋት ያለመቻልም ጭምር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
የኢኮኖሚውን ፖሊሲ መሳሪያ ደግሞ አንድ በአንድ እየተነተነ ለተመለከተ በምንም ዐይነት ወደ ውስጥ ሰፋ ላለ ገበያ መዳበር፣ ለቴክኖሎጂና ለሳይንስ መበልጸግ፣ ለህብረ-ብሄር ምስረታና ማጠናከሪያ፣ እንዲሁም ለማህበራዊና ለምሁራዊ እንቅስቃሴ መዳበርና መጠንከር የሚያግዝ አይደለም። የኢኮኖሚው ፖሊሲ ከሌሎች ነገሮች ተነጥሎ መወሰዱ ራሱ ፀረ-ሳይንስና ፀረ-ፍልስፍና ነው። በተለይም ገና በእግሩ ለመቆም በሚንደፋደፍ አገር ላይ እንደዚህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚያመጣው አሉታዊ ውጤት ዛሬ እንደምናየው ዐይነት ነው። መዝረክረክን፣ ድህነትን፣ ብሄራዊ ውርደትን፣ ልዩ ልዩ ዐይነት የብልግና ስራዎች መስፋፋትን፣ በሽታን፣ የኢንዱስትሪ ዕድገት መዳከምንና ሀብት ለመፍጠር አለመቻል፣ ከተማዎች መፈራረስና፣ ጠቅላላው ህዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ አድርጎ የተወሰነው እንዲሰደድ ማድረግ፣ የመጨረሻ መጨረሻም የውጭ ኃይሎች ተገዢ መሆንና ህብረተሰብአዊ ውርደትን መቀበል ነው።
ኢኮኖሚ ለሚገባው በተለይም የኢኮኖሚ መሳሪያዎችን ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈጋል። እንደሚታወቀው ኢኮኖሚ ራሱ እንደባዮሎጂካል ክንዋኔና ነው። ከታች ወደ ላይ እየተኮተኮተ የሚያድግ እንጂ በአወቅሁኝ ባይነት ከላይ ወደታች የተወሰኑ የፖሊሲ መሳሪያዎችን በመጫን ሊስተካከል የሚችል ነገር አይደለም። ይህንን በደንብ ለመረዳት የገንዘብን ወይም ከረንሲን ዝቅ አድርጎ መተመን (Devaluation) ሎጂካዊና ሳይንሳዊ ያልሆነ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን የኢኮኖሚ ስሌት እንመልከት። በዓለም አቀፍ የገንዘብና በጠቅላላው የኒዎ-ክላሲካል ወይም ኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ዕምነት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከረንሲዎች ኢኮኖሚው ከሚፈቅደው በላይ ከፍ ብለው የተተመኑ ስለሆነ እነዚህ አገሮች ወደ ውጭ የሚሸጡትን ምርት እንደልብ ለመሽጥ አይችሉም። ስለዚህም ያላቸው አማራጭ ከረንሲያቸውን ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዝቅ (Devalue) ማድረግ አለባቸው። በዚህ መልክ ምርታቸውን በብዛት መሸጥ ይችላሉ ይሉናል። ይህ ዐይነቱ ስሌት ግን በተለይም የእርሻንም ሆነ ሌሎች የጥሬ-ሀብት ውጤቶችን ለዓለም ገበያ ለሚያቀርቡ አገሮች በፍጹም ሊሰራ አይችልም።
በመጀመሪያ ደረጃ፣ የዓለም ገበያ ሊገዛ የሚችለው በሚፈልገው መጠን ብቻ ነው። ይህ ማለት አንድ አገር ገንዘቧን ዝቅ ስለ አደረገች የፈለገችውን ያህል ትሸጣለች ማለት አይደለም። የዚህ ዐይነቱ የውጭ ከረንሲ ዝቅ ማለት በቴክኖሎጂ መጥቀው ለሚገኙ አገሮችና ዕቃዎቻቸውም በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተፈላጊነት ያለውን አገሮች ብቻ ነው ሊጠቅም የሚችለው። ሁለተኛ፣ የቡናም ሆነ የሌሎች ጥሬ-ሀብቶች ዋጋ በአገር ውስጥ የምርት ሂደት በዋጋና በሺያጭ ስሌት ተተምኖ የሚመረትና የሚሸጥ ሳይሆን የዓለም ገበያ፣ በተለይም የቡናን ገበያ በሚቆጣጠሩ ጥቂት ካርቴሎች የሚወሰን ነው። ሶስተኛ፣ የቡና ገበያ አስተማማኝ ስላልሆነ ዋጋው በየጊዜው ከፍና ዝቅ ይላል። በዚህም ምክንያት ከረንሲያዋን ዝቅ ያደረገች አገር ለማካካስ ስትል ብዙ ቡና በዝቅተኛ ዋጋ ወደ ውጭ መሸጥ አለባት ማለት ነው። የኢትዮጵያ ብር ዝቅ እንዲደረግ ከተደረገ ወዲህ በተለይም ቡናን አልፎ አልፎ በብዛት መላክ ቢቻልም የውጭ ንግድ ሚዛኑ ግን በከፍተኛ ደረጃ እንደተናጋ እንመለከታለን። ወደ ውስጥ ደግሞ በተለይም ከውጭ የመለዋወጫ ዕቃና ሌሎች ምርቶችን አምጥቶ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ለሚሸጠው ነጋዴ አንድ ዶላር ለመግዛት ብዙ የኢትዮጵያ ብር ማምጣት ስላለበት፣ ይህ ሁኔታ በግሽበት ላይና በምርት ክንዋኔ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል። በሌላ አነጋገር የማምረቻ ዋጋን በማስወደድ በተጠቃሚው ላይ ጉዳት ያደርሳል። ብዙ የውጭ መለዋወጫ ዕቃዎች ወይም ማሺኖች መግዛት የማይችለው የምርት እንቅስቃሴውን እንዲያዳክም ይደረጋል። የምርት እንቅስቃሴም ሲዳከም የተወሰነው ሰራተኛ መባረሩ ብቻ ሳይሆን በተወሰነ ካፓሲቲ እንዲያመርት የሚገደደው አምራች ምርቱን በውድ ዋጋ እንዲሸጥ ይገደዳል። ምክንያቱም በዚህ ዐይነቱ የከረንሲ ፖሊሲ የተወሰነው ካፓሲቲ እንደማያመርት ስለሚደረግ ቋሚ ዋጋው (Fixed Cost) እንዳለ ስለሚቀር በእየአንዳንዱ ምርት ላይ ይህ ዋጋ በሚካፈልበት ጊዜ የግዴታ የሚሸጠውን ምርት እንዲወደድ ያደርገዋል።
ከኢኮኖሚክ ሳይንስ ወይም ከካፒታሊስት የኢኮኖሚ ዕድገት አንጻር ስንመለከተው በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የገንዘብ ኢኮኖሚ በደንብ ያልተስፋፋባቸውና የምርትም እንቅስቃሴ በጣም ደካማ ስለሆነ እንዲያውም የገበያን ኢኮኖሚ ዕድገት ከማገዝ ይልቅ የተቃራኒውን ነው የሚያደርገው። ስለገንዘብ ዕድገትና ተግባራዊነት፣ እንዲሁም ዛሬ ስላለበት ደረጃ ሚልተን ፍሪድማን ሳይሆን ማርክስ ነው በዳስ ከፒታል የመጀመሪያው ቅጹ ውስጥ በሰፊውና ሎጂካል በሆነ መልክ ያቀረበው። ስለዚህም የገንዘብን ዕድገትና ውስጣዊ ወይም ህብረተሰብአዊ ኃይል ሁለንታዊ ከሆነ ከካፒታሊስት ስልተ-ምርትና ዕድገት ተነጥሎ ሊታይ በፍጹም አይችልም። የገንዘብን ዕድገትና ምንነት መረዳት የሚቻለው በኒዎ-ሊበራል ወይም ኒዎ-ክላሲካል መነጽር ወይም ቲዎሪ ሳይሆን ካፒታሊዝምን እንደ ስልተምርትና እንደ ሸቀጥ አምራች ኃይል ወስደን ስንመለከትና መተንተን ስንችል ብቻ ነው። ከዚህ ስንነሳ ለምሳሌ በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ ገንዘብን ከፍና ዝቅ ማድረግ አያስፈልግም። አውቶማቲክ ዲቫሊዬሺን የሚባል ነገር አለ። ወደ ውስጥ ኢኮኖሚው መጠናከርና መዳከም፣ ወደ ውጭ በሚላከው የዕቃ ዐይነትና ብዛት፣ በካፒታል እንቅስቃሴና እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ አልፎ አልፎ በሚታይ ፖለቲካዊ ቀውስ እንደዶላር፣ ኦይሮና ዬንስ የመሳሰሉት ከፍና ዝቅ ይላሉ። በሌላ አነጋገር በገበያ ህግ መሰረት በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል የነዚህ አገር ከረንሲዎች ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል። በመንግስት ጣልቃ-ገብነት ወይም በማዕከላዊ ባንክ የከራንሲን ዋጋ ከፍና ዝቅ ማድረግ አያስፈልግም። በሌላ ወገን ግን ለምሳሌ ብዙ ዶላር በገበያው ውስጥ ካለና በሁለት ወይም በሶስት ከረንሲዎች መሀከል መዛባት ከተፈጠረ፣ ዶላር ወይም ሌላ ከረንሲ ዋጋው የባሰውኑ ዝቅ እንዳይል ማዕከላዊ ባንኮች የተትረፈረፈውን ገንዘብ በመግዛት እንዲረጋጋ ያደርጋሉ።
ያም ሆነ ይህ እንደኛ ባለው አገር የውጭውን ገንዘብ መቀነስና ከሌሎች ፖሊሲዎች ጋር አጣምሮ ተግባራዊ ማድረግ፣ በዚህም አማካይነት የገበያ ኢኮኖሚ ሊዳብር ይችላል የሚለው አስተሳሰብ ከካፒታሊስት የኢኮኖሚ ዕድገትና ሎጂክ አንፃር ስንመረምረው ሊሰራ የሚችል አይደለም። ህብረተሰብን ከማዘበራረቅና ችግሮችን በመደራረብ የህበረተሰቡ መሰረታዊ ጥያቄዎች እንዳይፈቱ ከማድረግ በስተቀር ኢትዮጵያ ለነበረችበትና ዛሬም ላለችበት የተወሳሰበ ቀውስ እንደ ፍቱን መሳሪያ ሆኖ ሊሰራ አይችልም። ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የፖሊሲ መሳሪያዎችን፣ ማለትም የመንግስት ሀብቶችን መሸጥና ወደ ግል-ሀብትነት እንዲዛወሩ ማድረግ፣ እንዲሁም የውጭውን ንግድ ነፃ ማድረግ ወይም ሊበራላይዜሽን ስንመለከት በፍጹም የገበያን ወይም የካፒታሊስት ኢኮኖሚን እንድንገነባ የሚረዱን አይደሉም። በታሪክም አልታየም። እንደዚህ ዐይነት ፖሊሲዎች ከላይ እንዳልኩትና በኛም ሆነ በሌሎች አገሮች እንደተረጋገጠው ጥቂት ግለሰቦችን ወይንም የመንግስትን መኪና የሚቆጣጠሩትን በተለያየ ዘዴ ሀብት እንዲያካብቱና እንዲደልቡ በማድረግ ዕድገት እንዳይመጣ የሚያግዱ ናችው።
የወያኔ ካድሬዎችና ደጋፊዎቹ ምንም ሳይሰሩ ሀብታም መሆን እንደቻሉ እንመለከታለን። ስልጣን ላይ ያለው ቡድን ኃይሉን ተገን በማድረግና ባንኮችን በማስገደድ ለካድሬዎቹ ብድር እንዲሰጡ በማድረግ፣ ጥቂት ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የናጠጡ ሀብታሞች ሊሆኑ በቅተዋል። እነዚህ በካፒታሊስት ሎጂክ ያልተኮተኮቱ ግለሰቦችና ቡድኖች ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ሳይሆኑ ከውጭ የሚመጣ ፍጆታ ተጠቃሚዎች በመሆንና በአገልግሎት መስኩ በመሰማራት ወደ ውስጥ የምርት እንቅስቃሴ እንዳይዳብርና ስራ ለሚፈልገው የስራ መስክ እንዳይፈጠር አድርገዋል። ይህ ዐይነቱ ልዩ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀምና ሀብታም መሆን በህዝቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ አምባገነንነት እንዲጫንበትና ተፈጥሮአዊ መብቱን እንዲያጣ ሊያደርገው በቅቷል። በዚህም መልክም አገሪቱ የቆሻሻ መጣያ በመሆንና ኢኮሎጂያዊ መዛባት በመፈጠር ህብረተሰቡ፣ በፖለቲካና የሚሊታሪ አምባገነንነት፣ኢኮኖሚያዊ አምባገንነትና የባህል ድቀት ተጨምሮበት ከብዙ አቅጣጫዎች እንዲወጠር በመደረጉ ለበሽታ እንዲዳረግ ሆኗል።
ከብዙ የአፍሪካ አገሮች ልምድና በአገራችንም ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመለከት፣ የፖሊሲው ዋና ዓላማም የውስጥ ገበያን ማዳከም፣ ዕውነተኛ በካፒታሊዝም ሎጂክ ላይ የተመሰረተ የገበያ ውድድር እንዳይኖር ማገድ፣ አጠቃላይ የሆነ የምርት እንቅስቃሴ እንዲዳከም ማድረግ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዳይዳብር መንገዱን መዝጋት፣ በአንድ አገር ውስጥ ለገበያ ኢኮኖሚ የሚያገለግሉ ከተማዎችና መንደሮች በስነስርዓትና ውበት ባለው መልክ እንዳይገነቡ ማድረግ፣ ባጭሩ የተስተካከለ ዕድገት እንዳይመጣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው። ከማዕከለኛና ከረዢም ጊዜ አንፃር ደግሞ ህዝባዊ መተሳሰር እንዳይኖር ማድረግ፣ ህበረተሰብአዊ እሴቶች ተበጣጥሰው አንዱ ሌላውን እየፈራ እንዲኖር ማድረግ፣ አንድ አገር ታሪክ የሚሰራበት መሆኑ ቀርቶ በተወሳሰበ ሰንሰለት ከውጭው ኃይል ጋር የተሳሰሩ ማፊያዊ ቡድኖች የሚፈልቁበትና ህብረተሰቡን የሚያከረባብቱበት ሁኔታ መፍጠር ነው። የሰውም የርስ በርስ ግኑኝነት በገንዘብ አማካይነት ስለሚሰላ፣ በተለይም ምሁራዊ የሆነ ክርክር በሌለበት አገርና የገንዘብን ሚና ባልተገነዘበ ማህበረሰብ ውስጥ ገንዘብ ራሱ ህብረተሰቡን የሚያጠፋ ኃይል ይሆናል።
ዛሬ በኢትዮጵያ ምድርና በውጭውም አገር ባለው ኢትዮጵያዊ ዘንድ በገንዘብ መካካድ የተነሳ የተፈጠረውን አደገኛ ሁኔታ ስንመለከት የአገራችን ዕድገት የተወሰነ ታሪካዊና ህብረተሰብአዊ ሎጂክን ተከትሎ እንዳልተጓዘ እንመለከታለን። በተለይም እዚህ ውጭ አገር ሆነው ለፍተው ጥረው ገንዝብ አጠራቅመው ቤት እንዲሰራላቸው ለዘመዶቻቸው፣ በተለይም ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ሲልኩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ አገራቸው ሲመለሱና ቤት እንዳልተሰራላቸው ሲመለከቱ ተደናግጠው የሚመለሱ ጥቂት አይደሉም። ገንዘብ የሚላክለትና አደራም የሚጣልበት ሰርቶ ያላገኘው ገንዝብ እጁ ላይ ሲወድቅለት የቱን ያህል ተለፍቶ እንደተገኘ ስለማይረዳው ገንዘቡን ለምግብና ለሌሎች ቁሳቁስ ነገሮች ይጠቀምበታል እንጂ እስቲ ለመዋዕለ-ነዋይ ላውለውና እኔም ተጠቅሜ ገንዘብ የላከልኝን ልጥቀመው ብሎ አያስብም። በዚህ ረገድ በነፃ ገበያ ስም የተካሄደው የፖሊሲ ለውጥና ተግባሩ ኢኮኖሚውን ከማድቀቁ አልፎ የህዝቡን ሞራልና ስነ-ምግባር እንዲሁም ርስ በርስ አለመተማመን በከፍተኛ ደረጃ እንዳበላሸውና እንዳናጋው የአገራችንን ተጨበጫ ሁኔታ በቅርቡ የተከታተለ ሊገነዘበው ይችላል።
በዚህ ዐይነቱ የተቅዋም መስተካከያ ፖሊሲ አማካይነት ጥገኝነትና፣ በተዘዋዋሪ ደግሞ በቀጥታ ጥምር አምባገነንነት ሊሰፍን ችሏል። የኢኮኖሚው ፖሊሲ ዕውነተኛ ሀብትን ለመፍጠር ስለማያስችልና የአንድን አገር ጥገኝነት ስለማይቀንስ በገንዘብ ቅነሳው አማካይነትና በጠቅላላው ፖሊሲ ግድፈት የተነሳ አንድ አገር በዕዳ መተብተቧ ብቻ ሳይሆን የውጭ ንግዷ ስለሚዛባ በየጊዜው ልዩ ልዩ ግን ደግሞ ተመሳሳይ የሆኑ አንጀት አጥብቅ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ እንድታደርግ ትገደዳለች። ምክንያቱም የዓለም የገንዘብ ድርጅት በየጊዜው ብድር ሊሰጥ የሚፈልገው አንድ አገር የድርጅቱንና የዓለም ኮሙኒቲ የሚባለውን ትዕዛዝ የተቀበለች እንደሆን ብቻ ስለሆነ ነው። በዚህ መልክ የአንድ አገር ህዝብ ዕድል ወደድንም ጠላንም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀነባበረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ የረቀቀ ዓለም አቀፋዊ የአምባገነን ስርዓት እንዲሰፍንበት ይሆናል። አገዛዙ ብቻ ሳይሆን ሌላውም ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል ከዚህ ሌላ አማራጭ የሌለው ስለሚመስለው አንድ ጊዜ የተዋቀረውንና ስር የሰደደውን አስከፊ ስርዓት ሊያስተካከል አይችልም። ሳይወድ በግድ በድሮ መልኩ በመቀጠል ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል። ድህነትና መጎሳቆል የአንድ ህዝብ ዕጣው ይሆናሉ ማለት ነው። ስለዚህም ነው የአገራችን ኢኮኖሚ አድጓል ቢባልም ከዐመት ወደ ዐመት የህዝቡ ኑሮ እየተበላሸና፣ ድህነትና መጎሳቆል፣ እንዲሁም ደግሞ አገር እየጣሉ መሄድ እንደባህል ሊወሰዱ የተቻለበት።
እንደሚታወቀው ቀደም ብለው በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ሆነ በእኛ አገር ተግባራዊ የሆነው የተቅዋም ማስተካከያ ፖሊሲ (Structural Adjustment Program) በጥገናዊ ለውጥ ስም ተሳቦ ወይም ሪፎርም ያመጣል ተብሎ ነው። ለመሆኑ በአንድ አገር ጥገናዊ ለውጥ ለምንድን ነው የሚያስፈልገው? ጥገናዊ ለውጥስ ሲባል ምን ማለት ነው? በመሰረቱ በአንድ አገር ውስጥ የኢኮኖሚ ወይም የፖለቲካና የሶሻል ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ ሲባል ቀደም ብሎ የነበረው ስርዓት በደንብ ስለማይሰራና ለሰፊው ህዝብ አስፈላጊውን መሰረታዊም ሆነ ለኢኮኖሚ ግንባታ የሚያስፈልጉ ቅድመ-ሁኔታዎችን ማሟላት ስለማይችልና ለድህነትና ለኢኮኖሚ ዕድገት አንቅፋት ሆኗል ተብሎ ስልሚገመት ወይም ስለሚታመን ነው። ስለሆነም ከሱ በተሻለና ውስጠ-ኃይሉ (Dyanamism) ከፍ ባለና፣ ከማዕከለኛም ሆነ ከረዢም ጊዜ አንፃር የሰፊውን ህዝብ ፍላጎት በማሟላት ኢኮኖሚው አድጎ አንድ አገር በአስተማማኛ መሰረት ላይ ልትቆም ትችላለች በማለት ነው። ይህ መሆኑ ቀርቶ ግን በሪፎርም ስም ተግባራዊ የሚሆን ፖሊሲ የተቃራኒውን የሚያደርግ ከሆነ ይህ ዐይነቱ ጥገናዊ-ለውጥ ሳይሆን ስለኢኮኖሚና ስለህብረት ሳይንስ የማይገባቸውን ህዝቦች ለማታላል ሆን ብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚቀነባበርና አንድን ህዝብ ወደ ድህነት የሚገፈትር አደገኛ ሴራ ወይም የሰይጣን ስራ ነው ማለት ይቻላል። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የኒዎ-ሊበራል የተቅዋም ማስተካከያ ፖሊሲ ተግባራዊ በሆነባቸው አገሮች በሙሉና በአገራችንም ሁኔታዎች በሙሉ ቀድሞ ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃጸሩ እየተበላሹ እንደመጡ ብዙ ጥናቶች ያሳያሉ። እንደዚህ ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በኢኮኖሚው ላይ ብቻ ሳይሆን አሉታዊ ተፅዕኖና ክስተት ያሳደረውና ያሰፈነው፣ በአጠቃላይ ሲታይ በህብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ የባህል ቀውስ በማስከተል በቀላሉ ሊወገድ የማይችል መዘዝ ተክሏል። ለምሳሌ የአገራችንን ሁኔታ ብቻ ስንመለከት በደርግም ሆነ በአፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ህዝቡ ደሀ ቢሆንም የተስፋፋ የቆሻሻ መኖሪያ ቦታና(Slums) በመቶ ሺህ የሚቆጠር ወጣት መንገድ ላይ እያደረ ምግቡን ከቆሻሻ ቦታ እየለቀመ የበላበት ጊዜ አይታወቅም።
በወያኔ ዘመን ግን ይህ ዐይነቱ የተቅዋም ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ወደህ የድህነቱ መጠን ብቻ ሳይሆን በቆሻሻ ቦታዎች የሚኖረውና የቆሻሻ መኖሪያ መንደሮች እየተስፋፉ እንደመጡ እንመለከታለን። ይህ ብቻ ሳይሆን በወያኔ የአገዛዝ ስር ግብረ ሰዶማዊነትና የወጣት ሴቶች በየመንገዱ እየቆሙ ሰውነታቸውን መሸጥ እየተለመደና የህብረተሰብአችንም አንድ አካል እየሆነ መጥቷል ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ አጸያፊ ድርጊት በአፄ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ የአገዛዝ ዘመን የሚታወቅ አልነበረም፤ ወይም በዚህ መልክ መረን የለቀቀና ህዝቡ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። ይህ አጸያፊ ድርጊት እየተስፋፋ በመምጣቱ የህብረተሰባችንን እሴትና ባህል በከፍተኛ ደረጃ ሊያናጋው በቅቷል። ከዚህ ስነንሳ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ የዓለም ባንክና የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ በሚባለው በደካማ አገሮች ላይ የሚጫነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጥገናዊ-ለውጥ ሳይሆን በመሰረቱ ድህነትን ፈልፋይና አንድን ህዝብ አቅመ-ቢስ አድርጎ ነፃነቱን በማሳጣት ባህሉንም በማውደም በውዥንብር ዓለም ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ነው። በድህነተና በውዥንብር ዓለም ውስጥ የሚኖር ህዝብ ደግሞ ራሱንም ለመከላከል ሆነ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በማዳበር የስልጣኔ ባለቤት ሊሆን በፍጹም አይችልም።
የወያኔ አገዛዝ የሲቪል መንግስት ወይስ ወታደራዊ አምባገነን!
በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች ያለውን ሁኔታ ስንመለከት በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በፀጥታውና በሚሊታሪው መሀከል ግልጽ የሆነ ልዩነትና የስራ ክፍፍል የለም። ከላይ ለማሳየት እንደፈለጉት የብዙ አፍሪካ አገሮች የህብረተሰብ አወቃቀር በቅኝና በእጅ አዙር አገዛዝ ስር ስለተመሰቃቀለና ዕድገቱም ስለተበላሸ ብዙ ነገሮች ተመሰጣጥረው ይገኛሉ። እንደ ምዕራቡ የካፒታሊስት ስርዓት ግልጽ የሆነ የፖለቲካ አወቃቀር፣ የመንግስት አመሰራረትና ሚና፣ እንዲሁም መንግስት ከኢኮኖሚው ጋር የሚኖረው ግኑኝነትና የሚከተለው ፖሊሲ ግልጽ አይደለም። በዚህም ምክንያት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገዛዞች በቅኝ አገዛዝ ዘመን ከተተከሉት ኢንስቲቱሽኖች ባለመላቀቃቸውና በውጭ ተፅዕኖ ስርም ስለወደቁ የመንግስት መኪናዎቻቸው ወደ አምባገነንነት እንዲቀየሩ ሆነዋል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ለብዙ የአፍሪካ አገዛዞች ወደ አምባገነንነት ማምራትና የውጭ ተገዢ መሆን በመሰረቱ ሰፋ ካለ ዕውቀትና ምሁራዊ እንቅስቃሴ ዕጦት ወይም አለመኖር ጋር የተያያዘ ነው። የተወሳሰበና በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ማለትም፣ በሊትሬቸር፣ በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በአርክቴክቸርና ውበት ባላቸው ከተማዎች የሚታይ ነገር ስለሌለ አገዛዞች አምባገነን የመሆን ኃይላቸው ከፍ ይላል። ከላይ የተዘረዘሩት ነገሮች አለመኖር ለውጭ ኃይሎችም በማመቸት በየአገሩ እየገቡ እንደፈለጉት መፈትፈትና አገዛዙን ማሳሳት ይችላሉ። በዚህም መሰረት የአገሬው ህዝብ በራሱ አገዛዝ ብቻ ሳይሆን በውጭ ኃይሎችም ይናቃል። በአገሩ የሚናቅ ህዝብ ደግሞ ውጭ አገርም በሚሄድበት ጊዜ ሊዝናና ግለሰብአዊ ነፃነት ሊሰማው በፍጹም አይችልም።
ወደ ኢትዮጵያም ስንመጣ፣ ምንም እንኳ አገራችን በቅኝ ግዛት ስር ባትተዳደርም እ.አ ከ1945 ዓ.ም በኋላ በተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ የአገዛዝ አወቃቀር ሎጂክ ውስጥ እንድትካተት በመደረጓ ሰፊው ህዝብ ተፈጥሮአዊ መብቱ እንዲገፈፍ ሆኗል። ይህ ዐይነቱ ቢሮክራሲያዊ አወቃቀር በደርግ ዘመን እንዳለ ሲወሰድ፣ የወያኔ አገዛዝም ቀስ በቀስ እያለ ትንሽ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በማጥፋት የሚሊታሪውን፣ የፀጥታውንና የመንግስቱን ቢሮክራሲ በመቆጣጠር፣ ሲቪል የሚመስል በእርግጥ ደግሞ የሚሊታሪ አምባገነን መንግስት ለማዋቀር ችሏል።የሚሊታሪ ርዕዮተ-ዓለሙንና የአሰራር ስልቱን እንዳለ ወስዷል። ይህንን ማድረግ የቻለው ደግሞ ከአሜሪካንና ከእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም ጋር የጠበቀ ግኑኝነት በመመስረትና በፀረ-አሸባሪነት ካምፕ ውስጥ እንዲጠቃለል በመደረጉ ነው።
ለወያኔ ይበልጥ መጠናክር ደግሞ የምርጫ 97 ዓ.ም ውጤት የራሱን ሚና እንደተጫወተ የሚታወቅ ሲሆን፣ ራሱ ወያኔና ጠቅላላው የኢምፔርያሊስቱ ካምፕ በዚህ በመደናገጡ የግዴታ ወያኔ የበለጠ ሚሊታራይዝድ አንዲሆንና በአሜሪካን የወረራና የጦር ሎጂክ ስር ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል። ከመጀመሪያው የኢትዮጵያና የኤርትራ ጦር አንስቶ ሱማሌን እስከመውረር ድረስና በአልሻባብ በሚባለው የእስላም አክራሪ ላይ እንዲዘምት ማድረግ ወያኔን የበለጠ በዚህ ዐይነቱ የጦርነት ሎጂክ ውስጥ ለመክተትና አካባቢውን ዘለዓለማዊ የጦርነት አውድማ ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው። በዚህም መሰረት ወያኔ ጦሩንና የስለላ መዋቅሩን የበለጠ ዘመናዊ በማድረግ ተጠናክሮ አንዲወጣ አድርጎታል። ይህ ዐይነቱ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተንታኞች ግልጽ ያልሆነ የመንግስቱን መኪና የበለጠ ሚሊታራይዝ ማድረግና አምባገነንነትን ማስፋፋት ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ብዙ ደካማ አገሮችን የሱ ተቀጥያ መንግስታት(Vasal States) ከማድረግ ስትራቴጂ ጋር የተያያዘ ለመሆኑ መታወቅ አለበት።
በተለይም በእ.አ ከ1989 ዓ.ም ወዲህ የተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ ሁኔታና የምዕራቡ ዓለም በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ባልጠበቀው መልክ የቻይና ተጠናክሮ መውጣትና መጪው ኃያል መንግስት መሆን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በተለይም በአፍሪካ ምድር ውስጥ የሚከተለውን ስትራተጂ በአዲስ መልክ እንዲያዋቅር አስገድዶታል። ስለሆነም አፍሪኮም የተባለ ወራሪ ጦር በማቋቋምና በእስላም አክራሪዎች ስም በማሳበብ ጦርነትን በአፍሪካ ምድር ውስጥ ማስፋፋት ሲሆን፣ በዚያውም መሰረት የተለያዩ የአፍሪካ መንግስታትን ኦፊሰሮች ማስልጠንና በዚህ የጦርነት ሎጂክ ውስጥ እንዲካተቱ ማድረጉ ለወያኔም ሆነ ለሌሎች የአፍሪካ አገዛዞች እንዲጠናከሩ ዕድሉን ሰጥቷቸዋል። በዚህም መሰረት በጂቡቲ ትልቅ የጦር ካምፕ ሲኖረው፣ ኒጀርና ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው አልባ የጦር ካምፕ በማቋቋም ከዚያ እየተነሳ አሸባሪዎችን ለመደብደብ አስችሎታል። በመሆኑም ቁጥራቸው የማይታወቁ በተለይም ሱማሌ ውስጥ ብዙ ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ህፃናት እንደተገደሉና በየጊዜውም ንጹህ ዜጋዎች እንደሚገደሉ ይታወቃል። በዚህም መልክ ኦባማ ስልጣን ከያዘ ወዲህ አሸባሪዎች ያልሆኑ ከአምስት ሺህ በላይ የሚቆጠሩ ንጹህ ዜጋዎች በሱማሌ፣ በፓኪስታንና በየመን ተግድለዋል።
ከዚህ ስንነሳና የወያኔን ዕድገትና ዛሬ በሚሊታሪና በጸጥታ ኃይል መጠናከርን ስንመለከት ብዙ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት- ሁሉም ሳይንሳዊ ጥናቶች እንጂ ኮንስፓይረሲ ቲዎሪዎች አይደሉም- የወያኔን የመኖርና የኢትዮጵያን ህዝቦች ነፃነት ረግጦና የአገሪቱን ድህነት የበለጠ ጥልቀት እንዲኖረው ማድረግ ከአሜሪካን የረዥም ጊዜ ስትራቴጅና ደካማ አገሮችን በሱ ተፅዕኖ ስር ለማዋል ካወጣው ዕቅድ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። የዛሬው የወያኔ አገዛዝ በፍጹም ነፃ የሆነና የራሱን ነፃ የውጭ ፖለቲካ የሚከተል አይደለም። በአጭሩ የአሜሪካን መንግስት ስራ አስፈጻሚ ነው ማለት ይቻላል። የኢትዮጵያ ህዝብም የነፃነት ጥያቄ የመፈታቱና ያለመፈታቱ ጉዳይ ከዚህ አንፃር ነው መታየትና መተለም ያለበት።
ስለዚህም በአብዛኛዎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተንታኞች አልፎ አልፎ የሚቀርበው የፖለቲካ ሀተታ ህዝብን ለማዘናጋትና ትግሉ እንዲጨናገፍ ከማድረግ በስተቀር ሀቁን የሚነግረን አይደለም። ለምሳሌ የዓለም አቀፍን የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ አወቃቀር የሚተነትኑና በድህረ-ገጾች የሚቀርቡ ጽሁፎች እያሉ፣ የኢትዮጵያውያን ድህረ-ገጾችና አዘጋጆች ከነዚያ ትምህርት በመቅሰም ለምን ክሪቲካል የሆኑ ጽሁፎች እንዲቀርቡ ጥረት አያደርጉም? በአብዛኛዎቹ ሚዲያዎች ላይ ለምን በአገራችን ውስጥ ጣልቃ የሚገቡትንና ህብረተሰብአችንን የሚያዘበራርቁትን ጠጋ ብለው በመመልከትና በማጥናት ጽሁፎች እያቀረቡ እንድንወያይባቸው አያደርጉም? እስከዛሬ በሚካሄደው እምብዛም ክሪቲካል አመለካከት ባልያዘ አቀራረብ የኢትዮጵያን ህዝብ መጥቀም ይቻላል ወይ? በእርግጥስ በዚህ መልክ ለዕውነተኛ ነፃነት መታገልና ጠንካራ አገር መገንባት ይቻላል ወይ ? በሽታውን የደበቀ መድሀኒት አይገኝለትም እንደሚባለው ዛሬ በመሀከላችን ያለው አላስፈላጊ ጨዋነትና የፖለቲካ ትንተና አቀራረብ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰቆቃ ያራዝመዋል እንጂ ሊጠቅመው አይችልም። እንደዚህ ስል ግን ግልጽ የሆነ ፀረ-ኢምፔያሊስት ትግል እናካሂድ ማለቴ አይደለም። ክሪቲካል የሆነ ጥበብ የተሞላበት አቀራረብንም ከተጠቀምን የብዙ የዋህ ሰዎችን ጭንቅላት በማንቃት ለዲሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገውን ትግል መስመር ልናሲዘውና ልናፋጥነውም እንችላለን። እንደሚታወቀው አንድ ሰው ሲያመው በሽታው ከመጠናከሩ በፊት እንዲፈወስ ወይም እንዲሻለው ከፈለገ ቶሎ ብሎ ወደ ሀኪም ቤት መሄድ አለበት፤ የሀኪሙንም ምክር መስማት አለበት። በዚህ መልክ ብቻ ነው ከበሽታው ሊገላገል ወይም ሊፈወስ የሚችለው።
አምባገነንነትና የነፃነት ጥያቄ!
በአብዛኛዎቻችን ዘንድ እስካሁን ድረስ ያለው ዕምነትና ተቀባይነትም ያገኘው፣ በአገራችን ምድር ለነፃነት ዕጦት ዋናው ተጠያቂው የዛሬው የወያኔ አገዛዝ እንደሆነ ነው። ስለሆነም ይህ አገዛዝ ከወረደ ወዲያውኑ ነፃነታችንን እንቀዳጃለን የሚል ዕምነት በሁላችንም ጭንቅላት ውስጥ ሰፍኗል። ይሁንና ግን በአለፉት 22 ዐመታት ይህ አገዛዝ የአዋቀራቸው የሚሊታሪና የፀጥታ ኃይሎች፣ እነዚህን ተጠቅሞ የሰፊውን ህዝብ ነፃነት መግፈፍና ውስጥ ለውስጥም የማይስማሙትን ማሰርና እንዲያም ሲል መግድል፣ እነዚህ ሁሉ ዝም ብለው ካለምንም የርዕዮተ-ዓለም መሰረት የሚካሄዱ ሳይሆኑ በውጭው ኃይል ከውስጡ ጋር በማበርና በማጣናከር በህዝባችን ላይ የተጫኑ አደገኛ የመጨቆኛ መሳሪያዎች ናቸው። የወያኔ የመንግስት መኪና፣ የሚሊታሪው፣ የፀጥታውና የፖሊሱ አወቃቀር ካለውጭ ዕርዳታና ምክር እንዲሁም ስልጠና በራሱ ኃይል የተደራጀ ነው የሚል ሰው ካለ በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን እንደሚካሄድ አያውቅም ማለት ነው። ስለዚህም ለነፃነት የሚደረገው ትግል ብዙ የማይታሰቡ ጥያቄዎችን ይዞ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ አገዛዝ መገርሰስ ወይም መወገድ ብቻ አንድ ህዝብ ነፃነቱን ሊቀዳጅ እንደማይችል ከብዙ አገሮች ታሪክ የምንማረው ሀቅ ነው።
በተለይም ያለፈውን የሰላሳና አርባ ዐመታት የህዝቦችን የነፃነት ትግልና ጥም ስንመለከትና ስናጠና በአብዛኛው የሶስተኛው ዓለም አገሮች የህዝብ ነፃነት ተግባራዊ ሊሆን ያልቻለው የመንግስትና የመንግስት መኪናዎች ጥያቄ በገቢው ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ በሆነ መንገድ ስላልተፈቱና ለመፈታትም ስላልቻሉ ነው። አንደሚታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ ካፒታሊዝም ከተስፋፋና የበላይነትን ከተቀዳጀ ወዲህ ጭቆናዊ አገዛዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊስፋፋና አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ሚሊታራይዝድ በመሆን በዓለም አቀፍ የጭቆናና የአፈና ሰንሰለት ውስጥ ተዋቅረዋል፤ ተዋህደዋልም። የጥሬ-ሀብት ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ይህንን የተትረፈረፈ ጥሬ ሀብታቸውን እያወጡ በስርዓት ለመጠቀምና ህዝቦቻቸውን ከድህነት በማላቀቅ ስነ-ስርዓት ያለው ኑሮ ለመገንባትና ህዝቦቻቸውን ለማስከበር ያልቻሉት ከላይ በተዘረዘረው የሚሊታሪና የስለላ የጭቆና ሰንሰለት ውስጥ ስለተካተቱና በአሜሪካንና በተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊዝም የብዝበዛ ሎጂክ ውስጥ ተቀነባብረው ሀብታቸውን በስርዓት እንዳይጠቀሙ ስለተደረጉ ነው።
ስለሆነም በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የተዋቀረው የመንግስት መኪና በመሰረቱ የህዝቦች አለኝታና የሀብት ፈጣሪ መሳሪያ ወይንም መንገዱን የሚቀይስ ሳይሆን ድህነትን ፈልፋይ በመደረጉና፣ እያንዳንዱ አገዛዝ የራሱን ህዝብ ከውሻ በታች አድርጎ እንዲያይ በመደረጉም ነው። በሳይንስና በአንዳች ፍልስፍና ያልተዋቀሩ የመንግስታት መኪናዎች፣ ስነ-ምግባርና ሞራል የጎደላቸው፣ ማህበራዊ፣ ህብረተሰባዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳይሰማቸው በመደረጉ ወደ ተራ ታዛዥነት ተቀይረዋል። ወደ አገራችንም ስንመጣ የመንግስቱ መኪና አወቃቀር ከተቀሩት የአፍሪካ አገሮች እምብዛም አይለይም። ስለሆነም አንድ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለው ይህ ዐይነቱ እንደሰንሰለት የተያያዘ የጭቆና አገዛዝ ለዕውነተኛ ነፃነት እጦት ዋናው ምክንያት እንደሆነና የድህነትንም አፍላቂና የተስተካከለ ዕድገት እንዳይኖር የሚያግድ መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ ሲገባ ብቻ ለነፃነት የሚደረገው ትግል የተቃና ይሆናል። በሌላ አነጋገር፣ ለዕውነተኛ ነፃነት እታገላለሁ የሚል ሁሉ የመንግስታችንና የአብዛኛዎችን የአፍሪካ አገዛዞች አወቃቀር በሚገባ መገንዘብና እስካሁን በተካሄደው መንገድ ወደ ዕውነተኛው ነፃነት ማምራት እንደማይቻል መረዳት ይኖርበታል።እንዲያው በምርጫ ብቻ ወይም ደግሞ በውጭ ኃይል ታግዤ ስልጣን ቢያዝ የነፃነት ጥያቄም ሊመለስ ይችላል የሚለው እስከዚህም ከሳይንስ ጋር የማይጣጣም አደገኛ ግምት ብቻ ሳይሆን ፣ በተዘዋዋሪ የባርነቱ ዘመን እንዲቀጥል እንደማድረግ ይቆጠራል። በተጨማሪም ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለውም የሰላም ወይም የዕርቅ እንዲሁም የጦር ትግል እንደመፍትሄ ሊወሰዱ አይችሉም። ከዚህ ስንነሳ ይህ ከውጭው ጋር የተያያዘው ሰንሰለትና በውጭ ኃይል የተጫነብንና፣ አላፈናፍነን ያለንን ኃይል ከላያችን ላይ ማስወገድ እስካልቻልን ድረስ የኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነቱን ይቀዳጃል ማለት ዘበት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ርዕዮተ-ዓለማዊ መሰረቱንና አሳሳች አቀራረቡንም መረዳትና መመርመር የነፃነት ትግሉ አንድ አካል ሆኖ መታየት አለበት።
በፖለቲካ ትግል ውስጥም ዕውነተኛ ነፃነት ሌላን አገር በመለማመጥና አድኑኝ እያሉ ደብዳቤ በመጻፍና በመወትወት የሚገኝም እንዳይደለ መገንዘብ ያስፈልጋል። ዕውነተኛ ብሄራዊ-ነፃነትና ጠንካራ አገር መገንባት በልምምጥ የሚሆኑ ነገሮች አይደሉም። ዕውነተኛ ነፃነት የሚገኘው በሁሉም አቅጣኛ በሚካሄድ፣ በተለይም ደግሞ በዕውቀት ደረጃ በሚገለጽ ትግል ብቻ ነው ኃያልነትና መከበር የሚገኘው። ለምሳሌ ራሺያ ከ1989 ዓ.ም ወዲህ ትርምስምሱ በዚያው ቀጥሎ ቢሆንና አሜሪካኖች ስልጣን ላይ ያወጧቸው ወጣት ኃይሎች በዚያው ቢቆዩ ኖሮ ራሺያ ተመልሳ ነፃነቷን መቀዳጀት ባልቻለች ነበር። ለራሺያ ህዝብ ፕሬዚደንት ፑቲንን የመሰለ ሰው ስለጣለላትና፣ ህዝቡ በታሪክ ሂደት ውስጥም ከተቀዳጀው ዕውቀት ጋር ተደምሮ ዛሬ ራሺያ የተወሳሰቡ መሳሪያዎችን በመስራት ለመፈራትና ለመከበር ችላለች። በምዕራቡ ራሺያን ለመክበብና ለማዳከም የተደረገውና የሚደረገው ጥረት በየጊዜው እየከሸፈ ነው። ይሁንና ግልጽ ባልሆነ መንገድ አሸባሪዎች አልፈው አልፈው ጥቃት በማድረስ የራሺያን ሁኔታ ማወዛገብ ጀምረዋል። አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ በዚህ ዐይነቱ የአሸባሪዎች ድርጊት ውስጥ የምዕራቡ እጅ እንዳለበት ነው።
በተለይም ደግሞ ለሊበራል ዲሞክራሲና ለህግ የበላይነት ቆመናል የሚሉና በተሳሳተ ኢንፎርሜሽን የተወናበዱ ኃይሎችን በምክርም ሆነ በገንዘብ በመርዳት ምዕራቡ፣ በተለይም አሜሪካን ራሺያን ለማዳከምና በራሱ ተፆዕኖ ስር አድርጎ የተትረፈረውን ጥሬ-ሀብቷን ለመዝረፍ የማያደርገው ጥረት ይህ ነው አይባልም። ይሁንና ራሺያኖች እንደኛ ተላሎችና ደካሞች አይደሉም። ባላቸው ዕውቀትና የዲፕሎማሲና ፖለቲካዊ ጥበብ የምዕራቡን ተንኮል መቋቋም ይችላሉ። በተወሳሰበ የጦር መሳሪያቸውም ማስፈራራት ይችላሉ። ቻይናም ቢሆን ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ ቀስ በቀስ እየተጠናከረች የመጣችውና ዛሬ ሁለተኛዋ ኃያል መንግስት መሆን የቻለችው በመለማመጥ አይደለም። የታሪክን ሂደት በመረዳትና፣ ዕውነተኛ ነፃነት ሊገኝ የሚችለው በውጭ ቁጥጥር ስር እስከወደቁ ድረስ አለመሆኑን በመገንዘብ ነው። ስለዚህም ለነፃነት የሚደረገው ትግል በቁንጽል አስተሳሰብ የሚካሄድ አይደለም።
በኛ ምሁራንና ተቃዋሚ ነኝ በሚለው ዘንድ ያለው ችግር ለችግራችን ዋናው መፍትሄ ሊበራል ዲሞክራሲና ነፃ ገበያ ብቻ ነው ተብሎ በመወሰዱ የዓለምን ሁኔታ በየዋህነት መነጽር እንድንመለከትና፣ ትግላችንንን በተወሰነ አቅጣጫ ብቻ እንድናተኩር በመደረጉም ነው። የዓለም ገበያና ፖለቲካ መወዳደሪያ መድረኮች መሆናቸው ለብዙዎቻቸን ግልጽ አይደሉም። ወደድንም ጠላንም የዓለም ገበያ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን ጥቂት ሞኖፖሊስቶች የሚቆጣጠሩት ሲሆን፣ የምዕራቡ መንግስታት በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶችና ድርጅቶች የሞኖፖሊስቶችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ናቸው። ያለው ሂራርኪያዊና ዓለም አቀፋዊ የኢንስቲቱሽን አወቃቀር በዚህ ሎጂክ መሰረት ነው የተዋቀረው። ስለዚህም ስለ አምባገነንነትና አምባገነንነትን ስለመታገል ስናወራ ዛሬ ከምናደርገው ትግል ባሻገር የነገሩን ውስብስብነት ጠለቅ ብለን ማየት አለብን። በዚህ መልክ ብቻ ነው ለዕውነተኛ ነፃነት ለሚደረገው ትግል የየበኩላችንን አስተዋፅዖ ማድረግ የምንችለው።
ይህ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የሚችለውና፣ አገራችንም እንደ አገር መከበር የምትችለው የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ስትሆን ብቻ ነው። አንድ ህዝብ ለመኖርና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚያድግ ቴክኖሎጂ የሚያስፈልገው ብቻ ሳይሆን፣ ከውጭው ዓለም የሚመጣበትን ግፊት ሊቋቋም የሚችለው በቴክኖሎጂም ዕድገት አማካይነት ነው። እንደሚታወቀው አንድ ሁኔታ በተዓምር እስካልተፈጠረ ድረስ በተለያዩ አገሮች መሀከል ፍጥቻ መኖሩና፣ አንደኛው ሌላውን የሱ ተገዢ በማድረግ ነፃነቱን እንደሚወስን ይታወቃል። የኛ አለመገዛት ወይንም የዕውነተኛ ነፃነት መቀዳጀት ሊወሰን የሚችለው ማንኛውንም ዐይነት መሳሪያ መስራት የምንችል እስከሆን ድረስ ብቻ ነው። ወደዚያ ለመድረስ ግን በመጀመሪያ ደረጃ ቀስ በቀስ ቀላል የሆኑ የኢኮኖሚ ችግሮችን፣ የምግብን፣ የንጹህ ውሃን፣ የቤትን፣ የህክምናንና የትምህርትን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት መቻል አለብን። ጎን ለጎንም ስርዓት ባለው መልክ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠርና ማምረት መቻል አለብን። ለዚህ ደግሞ ዋናው ቁልፉ ከዕውቀት ባሻገር ፍላጎትና የአገር ወዳድ ስሜትነት ሲሆኑ፣ ለአንድ ዓላማ ለመታገል ጠንካራ መንግስታዊና ህዝባዊ አደረጃጀት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ። የአንድ አገር የመንግስት መኪና ለውጭ ኃይሎች ክፍት ከሆነና ውስጥ ሆነው የማያሰሩ ኃይሎች ኢንፎርሚሽን በማቀበል የአገራቸው ዕድገት ጠላት እስከሆኑ ድረስ ስለ ዕድገትና ስለመከበር በፍጹም ማውራት አይቻልም። ስለዚህም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከሁለት ነገሮች አንዱን መምረጥ መቻል አለበት። ወይ የኢትዮጵያ ህዝብ አገልጋይ፣ ካሊያም ደግሞ የውጭ ኃይል። በሁለት ቢላ መብላት እንደማይቻል ሁሉ፣ ከሁለት አንዱን መምረጥ የግዴታ ነው። በዚህ መልክ ኢትዮጵያዊነትን ካስቀደምንና ዕውቀትንና ቴክኖሎጂን እየኮረጅንና እየሰረቅን ወደ አገራችን ማስገባት ከቻልን የታሪክ ሚናችንን ተወጣን ማለት ነው።
ከዚህ ስንነሳ ማንኛውም ለነፃነት እታገላለሁ የሚል ኃይል ሁሉ አሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰፈነው አደገኛ የአገዛዝ መዋቅርና የጦርነት አካሄድ እንዴት አድርጎ ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነት እንደሚያመጣለት ማሳየት መቻል አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን አሁን በዓለም ላይ በሰፈነው የጎሎባል ካፒታሊስት የኢኮኖሚ ስርዓትና ብዙ አገሮች የነፃ ንግድንና የገበያን ኢኮኖሚ መርሆአቸው ባደረጉበት ወቅትና ተግባራዊ በሚያደርጉበት ሁኔታ ውስጥ እንዴ ተደርጎ አንድ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን መቀዳጀት እንደሚችል እያብራሩ ማሳየት ያስፈልጋል።
ስለሆነም የላይኛው ጥያቄ የፖለቲካን፣ የኢኮኖሚንና የማህበራዊ ነፃነት ወይም ዕኩልነት ጥያቄን እንድናብራራና፣ እነዚህ መሰረታዊ ነገሮች እንዴትስ ተራ በተራ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ማሳየት ያስፈልጋል። ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአንድ ህዝብ የፖለቲካ ነፃነት ህልም ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው በምርጫ ብቻ ወይም ተወካይነትን በማግኘትና በሱ አማካይነት መልስ ይገኛል ብሎ በመጠባበቅ አይደለም። ዕውነተኛ የፖለቲካ ነፃነት ከምርጫ ተሻግሮ የሚሄድና የህዝቡን በፖለቲካ ክንዋኔ ውስጥ መሳተፍንና፣ ለዚህ ደግሞ የንቃተ-ህሊናን ማደግንና መደራጀትን ይጠይቃል። የአንድ አገር ህዝብ፣ ቢያንስ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል የየፓርቲዎችን ፕሮግራምና ሃሳብ ሊረዳና ሊቆጣጠራቸውም የሚችለው የፓርቲዎችን ፕሮግራምና ርዕይ የመረዳት ዕውቀት ሲኖረው ብቻ ነው። ካለበለዚያ ማንኛውም ግለሰብ ወይም ፓርቲ ነኝ የሚል ይህንን ወይም ያኛውን ነገር እየያዘ በመነሳት እንደዚህ አደርጋለሁ በማለት ህዝብን የሚደልልበት ሁኔታ በመፍጠር ህዝቡ ዕውነተኛ የፖለቲካ ነፃነት እንዳይጎናጸፍ ያደርጋል።
ያለፉትን የአርባ ዐመት የፖለቲካ ትግልና ለዚህ ተብሎ የተደረገውን መስዋዕትነት በምንመረምርበት ጊዜ ቀድሞም ሆነ ዛሬ ስለ ፖለቲካ ያለን አስተሳሰብ እጅግ የተሳሳተ ይመስለኛል። በመጀመሪያ የፖለቲካ አስተሳሰባችን ከፍልስፍናና ከሳይንስ ውጭ ተነጥሎ ስለታየና በዚህም ላይ የተመሰረተ ስላልነበር ያነጣጠረው ስልጣንን ለመያዝ ብቻ ነበር። በዚህም ምክንያት የተነሳ ፖለቲካ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ግልጽነትና ህዝባዊነት ያለው ግዙፍ የሃሳብ መንቀሳቀሻ መድረክ መሆኑ ቀርቶ ወደ ምስጢራዊነትና ወደ ህቡዕነት ተለወጠ። ህቡዕነትና ምስጢራዊነት ደግሞ የግዴታ ለተንኮልና ለሽወዳ በራቸውን ክፍት አደረጉ። ፖለቲካ ተንኮል ወደ መስራትና መሸወድ፣ እንዲያም ሲል ቶሎ ብሎ የጠረጠሩትን ማጥፋት ተቀንሶ እንዲታይ ተደረገ። ይህ ዐይነቱ የትግል ዘዴ ደግሞ የግዴታ ነፃነትን የሚያፍንና በከፋፍለህ ግዛ ላይ የተመሰረተ ስለነበር የመጨረሻ መጨረሻ ወደ መጠራጠርና ወደ ርስ በርስ መጨራረስ አመራ። በሁለተኛ ደረጃ፣ ለፖለቲካ ለውጥ እንታገላለን ይሉ የነበሩትና ዛሬም ያሉት ኃይሎች ለፖለቲካ ለውጥ የሚደረገው ትግል ከፍተኛ ንቃተ-ህሊናንና የጭንቅላት ጂምናስቲክን እንደሚጠይቅ በፍጹም የተረዱ አልነበሩም፤ ዛሬም አይደሉም።
በታላላቅ ፈላስፋዎች ከፕላቶን እስከ አሪስቶተለስ፣ ከኩዛኑስ እስከ ላይብኒዝና፣ ሺለርና ካንት ድረስ ያሉትን የፖለቲካ ፈላስፋዎች ስራዎች ስንመለከት አጻጻፋቸው በሙሉ የሰውን አእምሮና መንፈስ በመረዳት ዙሪያ የሚሽከረከር ነበር። በነሱም ዕምነት የሰው ልጅ ችገር የግዴታ ከጭንቅላት በደንብ አለመታነፅ ወይም ከንቃተ-ህሊና ማነስ ጋር የተያያዘ ነው። ከፍተኛ ንቃተ-ህሊና በሌለበት ህብረተሰብ ውስጥ የፖለቲካ ትግል ብሎ መጀመር፣ ወይም ደግሞ ዕውቀትን ሳያካትቱ በዚያው መቀጠል የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ እንደ መጣስ ይቆጠራል፤ በነሱ ላይም ዘመቻ ማድረግ ነው። ምክንያቱም ህብረተሰብም ሆነ ተፈጥሮ የረሳቸው የሆኑ ውስጣዊ ህጎች ስላሏቸው፣ የሚካሄደው ትግል ቀስ ተብሎና ከታች ወደ ላይ መሆን ስላለበት ነው። ስለሆነም አንድን ህብረተሰብ ነፃ አወጣለሁ ብሎ ሲታሰብ ከመጀመሪያውኑ ትግሉን ለመጀመር የሚፈልገው ራሱን ነፃ ማውጣት አለበት። በየጊዜው ወደ ውስጥ ጭንቅላቱን በማየት የሚሰራቸውን ስራዎች መመርመር የሚችል መሆን አለበት። በዚህ መልክ ብቻ ታሪካዊ ተልዕኮውን ሊወጣ ይችላል።
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሂደትና የፓርቲዎች አደረጃጀት ስንመለከት ትላንትም ሆነ ዛሬ በሳይንስና በፍልስፍና ዙሪያ የሚሸከረከርና እነዚህን መሰረት ያደረገ አይደለም። እንደ ትላንትናው ዛሬም ቡዳናዊ ስሜት አይሎ ይገኛል። እንደ ትላንትናው ዛሬም ስለ ፖለቲካ የማያውቅና የማይገባው ወይም ለማወቅ ጥረት የማያደርግ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ እየገባ የሰውን ልብ ያደርቃል። ከመጠየቅ ይልቅ አውቃለሁ በማለት ፍጥጫ ይጀምራል። ምንም ዝግጅትና በህይወቱም ለፖለቲካ ትግል አስተዋፅዖ ሳያደርግ ፓርቲ ወደ መመስረት ያመራል። እንደሚታወቀው ለፖለቲካ ትግል ሲካሄድ አንድ ሰው ከአረጀና ከአፈጀ በኋላ አይደለም ስለ ፖለቲካ ትግል ማሰብና ማውራት እንዲሁም ገብቶ መሳተፍ ያለበት። ለፖለቲካ ለውጥ እታገላለሁ የሚል በ 15 እስከ 20 ዐመት ባለው ዕድሜው ውስጥ መጀመር ሲገባው፣ በመጀመሪያ ከፖለቲካ ጋር ከመተዋወቁ በፊት ከፍልስፍናና ከሳይንስ ወይም ከሊትሬቸር ጋር መተዋወቅ አለበት። በዚህ ከጀመረ ጭንቅላቱ ክፍት እየሆነና ህብረተሰብና ተፈጥሮን በመረዳት የሌላውንም አስተሳሰብ ለመቀበል ዝግጁ ይሆናል። ከአመጽ ይልቅ ውይይትንና ክርክርን ያሰቀድማል። ለኩርፊያና ለመቀየም ቦታ አይሰጣቸውም። እራሱንም የተፈጥሮና የህብረተሰቡ አካል አድርጎ በመቁጠር ለዕውነተኛ ህዝባዊ ነፃነትና ዕድገት ይታገላል። የብዙዎችን የአውሮፓ የጥንት የፖለቲካ ሰዎች ባዮግራፊ ስናነብ ይህንን ነው መገንዘብ የምንችለው። ዛሬም ቢሆን የብዙ አውሮፓ ፓርቲዎች አባል፣ ቢያንስ ባለሁበት አገር ለፖለቲካ እንታገላለን የሚሉ ቀደም ብለው ነው የሚጀምሩትና አባል የሆኑበትን ፓርቲ ፍልስፍናና ፕሮግራም በደንብ አብጠርጥረው የሚያውቁት። ለዚህም ነው ባለፉት 60 ዐመታት ተከታታይነት ያለው የፖለቲካ ስራ መስራት የተቻለው።
በኛ አገር ግን በጣም ጥቂቱ ካልሆነ በስተቀር አብዛኛዎቻችን ከአረጀንና ከገረጀፍን፣ ወይንም ደግሞ በወጣትነታችን ዘመን ጭንቅላታችንን የሚያበላሹ ብዙ ውትብትብ ነገሮች ሰርገው ከገቡ በኋላ ነው ስለ ፖለቲካ ትግል የጀመርነውና ዛሬም የምናካሄደው። ቀድሞ የነበረብን ችግር የታወቀ ቢሆንም፣- የህብረተሰባችን የዕውቀት ደረጃ ዝቅ ማለት- ከአርባ ዐመት የፖለቲካ ትግል በኋላ ብዙም የተማርን አይመስለኝም። አሁንም ቂም በቀለኝነት፣ ኩርፊያ፣ ተንኮልና የማያስፈልግ ምስጢራዊነት፣ ሃሳብን በግልጽ አውጥቶ አለመናገርና አለመከራከር፣ አውቃለሁ ባይነት… ወዘተ. መለያችን በመሆን ስራ አላሰራ እያሉን ነው። በዚህ ላይ ደግሞ በፍልስፍናቸውና በርዕያቸው ላይ ሳይሆን በግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ ስድብ እየወረደ የፖለቲካ አየሩን እየመረዘው ነው። ፖለቲካ ህበረተሰብአዊ ነፃነትን የሚያጎናጽፍ ከመሆኑ ይልቅ የመነታረኪያ መሳሪያ እየሆነ መጥቷል ብል የምሳሳት አይመስለኝም።
ስለሆነም ስለፖለቲካ ነፃነት እታገላለሁ የሚል ትልቅ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን እንደሚሸከም ተገንዝቦ በመጀመሪያ የጭንቅላት ስራ መስራት እንዳለበት መረዳት አለበት። የአንድ አገር ህዝብ ዕድልና ብሄራዊ ነፃነት በፖለቲካ ዙሪያ የሚሽከረከር ሰለሆነና በሱም ስለሚመካ ከፖለቲካ ግንዛቤ እጦት የሚሰራ ስህተት አንድን ህብረተሰብ እያወዛገበ ይኖራል።አንድ ህብረተሰብ ታሪክ የሚሰራበት መሆኑ ቀርቶ ቡድናዊ ስሜት በመዳበር ህብረተሰቡ የሚፈልገው የዕድገት ስራ እንዳይሰራ ያግዳል።
ይህ በራሱ ደግሞ ወደ ኢኮኖሚ ነፃነት ወይም የኢኮኖሚ ዕኩልነት (Economic Justice) ወደ ሚለው ያመራናል። እንደሚታወቀው በአገራችን ምድር በአለፉት 22 ዐመታት አዲስ ዐይነት ህብረተሰብአዊ የኢኮኖሚ ግኑኝነት (Production Relationship) ተፈጥሮአል። ይህ በአገራችን ምድር የተተከለው አዲሱ የኢኮኖሚ ስርዓት ከውጭው ዓለም ጋር በሺህ ድሮች ተሳስሮ ለኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት ሆኗል። ድህነትን ፈልፋይ ሆኗል። ዕውነተኛ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠር ዕገዳ አድርጓል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አገሪቱ በሯን ክፍት በማድረጓ የሊበራላይዜሽንና የግሎባላይዜሽን ሰለባ በመሆን የቆሻሻ መጣያ ሆናለች። ዛሬ ህዝባችን እጅግ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖረው። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የወያኔ አገዛዝና የፖሊሲ አውጭዎቹ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን ከስምንት ዐመት በፊት አመልክተዋል። እስካሁን ድረስ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ የሚባለው፣ የነፃ ንግድን አራማጅ ድርጅት ውስጥ በአባልነት ከገባች ወደ እስር ቤት ውስጥ እንደተወረወረችና፣ የህዝባችንም የነፃነት ፍላጎት መልስ እንዳያገኝ በሩ ሁሉ ይዘጋበታል ማለት ነው። ኢትዮጵያ የንግድ ድርጅቱ አባል ከሆነች የአሜሪካን ዓለም አቀፋዊ ኩባንያዎችና የዘር አምራች ድርጅቶች መጨፈሪያ በመሆን ህዝባችን ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዲገፈፍ ይደረጋል። አገራችን የአሜሪካ የስጋ፣ የእንቁላል፣ የዘርና ልዩ ልዩ ለዕድገት የማያመቹ ቆሻሻ መጣያ ስትሆን፣ በዚያውም መጠን የህዝባችን የማምረት ኃይል ይዳከማል። የምናልመው በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ብሄራዊ የውስጥ ገበያን መገንባቱ እንደ ውሃ ሽታ ይሆናል ማለት ነው። በዚህ መሰረት ኢኮኖሚያዊ ነፃነታችንን ማጣታችን ብቻ ሳይሆን፣ ብሄራዊ ነጻነታችንም ይገፈፋል። ስለሆነም ለነፃነት ትግል ሲደረግ ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ አወቃቀርና የምርት ግኑኝነት መስተካከልና ሰፊው ህዝብም የመሬት ባለቤት ሊሆን የሚችልበትና ቤትም ሰርቶ ተዝናንቶ ሊኖርበት የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት።
እንደሚታወቀው ወያኔ በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው እየተባለ በሚጠራው እየተመከረና እየታገዘ ተግባራዊ ያደረገውና የሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብሄራዊ ባህርይ የሌለውና ሰፋ ላለ፣ እርስ በርሱ የተሳሰረ የኢኮኖሚ ግንባታ አመቺ ያልሆነ ነው። ሰፋ ባለ የማኑፋክቱር፣ በምርምርና በዕድገት፣ እንዲሁም በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ያልተመሰረተ ስለሆነ እየሰፋ ሊመጣና አገሪቱን ሊያዳርስ የቻለ አይደለም። በየክልሎቹና በየከተማዎች እንዲሁም በየመንደሩ ዘመናዊ ኢንስቲቱሽን ባለመዘረጋቱ የአገሪቱን የተትረፈረፈ ሀብት ለማንቀሳቀስና ዕድገትን አምጥቶ ሰፊውን ህዝብ ከድህነት ማላቀቅ አልተቻለም። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ የተዝረከረክ አካሄድ ከቀጠለ ድህነቱ ጥልቀት ማግኘቱ ብቻ ሳይሆን አገራችን እንደ ህብረ-ብሄር ልትታይ በፍጽም አትችልም። ከዚህ አደጋ ለመላቀቅ የግዴታ ሁለንታዊ (Holistic) የሆነ ሰፊውን ህዝብና የአገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት የአካተተ የዕድገት ፈለግ መከተሉ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።
የአገራችንን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ችግር ልንቀርፍ የምንችለው በኒዎ-ክላሲካል ወይም በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ሞዴል ሳይሆን በጥንታዊው የሬናሳንስ የኢኮኖሚ ሞዴል ብቻ ነው። ከአገዛዞች መቀየር በኋላ በየአገሮች በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አቀነባባሪነት የሚወጡትና ተግባራዊ የሚሆኑት ፖሊሲዎች በሙሉ የቴክኖክራቶች ጫወታዎች እንጂ በምድር ላይ የሚታየውን የህዝቦችን ችግር መፍታት እንዳልቻሉ ነው የምናየው። በታሪክ ውስጥም ቴክኖክራሲያዊ የኢኮኖሚ ሞዴል የአንድን አገር ህዝብ ችግር የፈታበት ቦታና ጊዜ የለም። ቴክኖክራቶች ስለቁጥር እንጂ ስለ ሰው ልጅና ስለስልጣኔ ብዙም ስለማይገባቸው ተግባራዊ የሚያደርጉት ፖሊሲ በሙሉ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል እንጂ በፍጹም ሊፈታው አይችልም። በተጨማሪም የአገራችን የተወሳሰበ ችግር በአንድ ትልቅ ፕሮጀክትና ወይም ደግሞ እዚህና እዚያ በሚተከሉ ትናንሽ ፕሮጀክቶች ሊፈታ እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል። ኢኮኖሚያዊ ክንውን ከህብረ-ብሄር ግንባታ ጋር እስካልተያያዘ ድረስ ትርጉም ሊኖረው በፍጽም አይችልም። ስለሆነም ሰፊውን ህዝብ ያስቀደመና ለሁሉም የሚያመች ቆንጆ አገር ለመገንባት ከዚህ ከተክኖክራሲያዊ ሞዴል ባሻገር ማየትና ማለም ያስፈልጋል። በዚህ መልክ ብቻ ወደ ተፈለገው ዕውነተኛው ነፃነት ማምራት ይቻላል። የተከበረችና የምትፈራ አገርም መገንባት ይቻላል።
ስለሆነም አምባገነንነትን እቃወማለሁ፣ ነፃነትን አመጣለሁ ለሱም ጠበቃ የቆምኩ ነኝ የሚል ኃይል ሁሉ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተስፋፋው የተዛባ ስርዓትና ለብዙ ህዝቦችም ነጻነት ጠንቅ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ እንዴት ዕውነተኛ ነፃነት ሊመጣ እንደሚችልና ተግባራዊም እንደሚሆን ማስረዳት ያስፈልጋል። ይህንን ሳያሳዩና ሳያስተምሩ ነፃነት ነፃነት አየተባለ የሚደረገው ውትወታና ህዝብን ማደናበር ወደ ዕውነተኛው ነፃነት በፍጹም ሊያመራን አይችልም። ትግላችን ውስብስብ ስልሆነ ብዙ ጥያቄዎች በሳይንስ፣ በፍልስፍናና በቲዎሪ ደረጃ መብራራትና መልስ ማግኘት አለባቸው። ይህ ሲሆን ብቻ ለዕውነተኛ ነፃነት የቆመው ኃይል ማን እንደሆነ መታወቁ ብቻ ሳይሆን፣ የነፃነት ትግላችንም የተቃና ይሆናል ማለት ነው። መልካም ንባብ!!
fekadubekele@gmx.de
ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment