BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

BRIGHT FUTURE FOR ETHIOPIANS !!!

Sunday, 12 January 2014

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ልጃቸው ተከሰሱ



የቀድሞ ፕሬዚዳንት  ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ልጃቸው ተከሰሱ
ቤት ያገኘላቸው የኮሚሽን ሠራተኛ  360ሺ ብር አልተከፈለውም ውል ፈርሶብኛል ያሉ ሌላ አከራይ የ2.4 ሚሊዮን ብር ካሣ ጠይቀዋል የፕሬዚዳንቱ ፅ/ቤት የሚከራከርለት የህግ ባለሙያ የለውም ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ የመኖሪያ ቤት አፈላልጐ ያከራያቸው የኮሚሽን ባለሙያ አቶ አንተነህ አሰፋ፤ 360 ሺ ብር የአገልግሎት ክፍያ አልተከፈለኝም ሲል በፕሬዚዳንቱና ልጃቸው ላይ ክስ መሠረተ፡፡ 

ክሱ፤ ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ የፕሬዚዳንቱን ጽ/ቤትና የጽ/ቤቱ ሃላፊ ወ/ሮ አማረች በካሎን፣ .............የጽ/ቤቱ ባልደረባ ወ/ሮ አምሣለ ፋንታሁንንና የፕሬዚዳንቱን ልጅ ወ/ሮ መና ግርማን እንደሚያካትት ታውቋል፡፡ 

ከሣሽ አቶ አንተነህ፤ ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም ለፍ/ቤት  በጽሑፍ ባቀረበው ማመልከቻ፤ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባለፈው መስከረም ወር ከስልጣን ሲወርዱ የገቡበትን ባለ 3 ፎቅ መኖሪያ ቤት አፈላልጐ በወር 400 ሺህ ብር እንዲከራዩ ማድረጉን ጠቅሶ፤ ለእሱ የሚገባው 360ሺ ብር የኮሚሽን ክፍያ እንዳልተከፈለው ገልጿል፡፡ የአገልግሎት ክፍያውን የመክፈል ሃላፊነት የማን እንደሆነ ለማወቅ መቸገሩን የጠቆመው ከሳሹ፤ ከ5ቱ ተከሣሾች ውስጥ ሃላፊነት ወስዶ ክፍያውን የሚፈጽመው ማን እንደሆነ ፍ/ቤቱ እንዲያጣራለት ጠይቋል፡፡ አስር በመቶ የኮሚሽን ክፍያው ከመስከረም ወር ጀምሮ ከሚታሰብ የ9 በመቶ ወለድና የክስ ሂደት ወጪዎች ጋር ተደምሮ ይከፈለው ዘንድም ለፍ/ቤቱ አመልክቷል፡፡ 

ክሱ የደረሰው የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ የህግ ድጋፍ ለመጠየቅ ለፍትህ ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ፤ ለኮሚሽን ባለሙያው ሊከፈል የሚገባው ገንዘብ፣ የመንግስትን ጥቅም ስለሚጐዳና ጽ/ቤቱም በራሱ ለመከራከር የህግ ባለሙያ ስለሌለው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወክሎ እንዲከራከርለት ጠይቋል፡፡ 

የመኖሪያ ቤት ፍለጋውን ከመጀመሩ በፊት የፕሬዚዳንቱ ወኪል ከሆነችው ከልጃቸው ወ/ሮ መና ግርማ ጋር የኮሚሽን ክፍያ ውል መፈራረሙን የጠቀሰው ከሳሹ፤ ክፍያውን በወቅቱ ባለማግኘቱ  ህዳር 16 ቀን 2006 ዓ.ም ለፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ፤ በ5 ቀን ውስጥ ክፍያው ካልተፈፀመ ክስ እንደሚመሰርት ማስጠንቀቁን አስታውሷል፡፡ ጉዳዩ የቀረበለት ፍ/ቤትም፤ ተከሣሾች መልሳቸውን የፊታችን ረቡዕ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ በማዘዝ የክሱን ቀጣይ ሂደት ለመስማት ለጥር 27 ቀጥሯል። በሌላ በኩል ቀደም ሲል በ530 ሺ ብር ቤታቸውን ለፕሬዚዳንቱ መኖሪያነት ለማከራየት ከተስማሙ በኋላ፣ ውል ፈርሶብኛል ያሉት አቶ ኤልያስ አረጋ፤ ቤቱን ለማሳደስና ለተያያዥ ጉዳዮች ያወጧቸውን የተለያዩ ወጪዎች በመጥቀስ፣ የ2.4 ሚሊዮን ብር ካሣ እንዲከፈላቸው ለፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት በደብዳቤ ያሳሰቡ ሲሆን ይህ ካልተፈፀመ ግን መብታቸውን በህግ ለማስከበር እንደሚገደዱ  ገልፀዋል፡፡ 

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፤ በአሁኑ ሰዓት በኃይሌ ገ/ስላሴ ጐዳና፣ ከአክሱም ሆቴል ጀርባ መንግስት በተከራየላቸው ባለሦስት ፎቅ መኖርያ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ቤቱ የመዋኛ ገንዳ ያለውና ባለብዙ ክፍሎች እንደሆነ ታውቋል፡፡ ቤቱ ከእሳቸው በፊት ለኬንያ ኤምባሲ ተከራይቶ ነበር፡፡  የመንግስት ባለስልጣናት በጡረታ ሲገለሉ የሚኖራቸውን መብት የሚደነግገው አዋጅ፤ ፕሬዚዳንቱ ከ4-5 መኝታ ክፍሎች ያሉት መኖርያ  ቤት እንደሚያገኝ ቢገልጽም የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት ለቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ፤ በጣም ውድና ከ20 ክፍሎች በላይ ያሉት መኖርያ ቤት መከራየቱ ሲያነጋግር መቆየቱ ይታወሳል፡፡  

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ልዩ አማካሪ አቶ አሰፋ ከሲቶን በጉዳዩ ዙርያ አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቀናቸው “ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ ስለሆነ ምላሽ ልሰጣችሁ አልችልም” ብለዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment