በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በከፋ ዞን፣ ኣርሶ ኣደሮች ያለፍላጎታችን ማዳበሪያ እንድንገዛ እየተገደድን ነው ኣሉ። ማዳበሪያ ኣንቀበልም ያሉ በርካታ ኣርሶ ኣደሮች ደግሞ ከሚደርስባቸው እስራትና ወከባ በመሸሽ በየጥሻው እየተንከራተቱ ነው ተብሏል።
የግብርና እና ገጠር ልማት መ/ቤት በበኩሉ ከእውነት የራቀ የሐሰት መረጃ ነው ሲል ኣስተባብሏል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ብ/ክ/መንግስት፣ በከፋ ዞን በኣጠቃላይ እና በተለይም በቢጣ ወረዳ ኣርሶ ኣደሮች ያለፍላጎታቸው ዩሪያ እና ዳፕ የተባሉ የማዳበሪያ ዓይነቶችን እንዲገዙ እየተገደዱ ነው የሚሉት ኣንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የአካቢው ኗሪ እንደሚሉት ማዳበሪያ ኣንቀበልም ያሉ በርካታ ኣርሶ ኣደሮች ከሚደርስባቸው ወከባና እስራት ለመሸሽ ሲሉ በየጥሻው ለመንከራተት እየተገዱ ነው።
ማዳበሪያው ደግሞ ዋጋው ከአቅማችን በላይ ከመሆኑም ባሻገር ከመሬታችን ጋር የሚስማማ ኣይደለም ሲሉም ኣማሯል።
በከፋ ዞን የቢጣ ወረዳ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት መ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ዘሪሁን መንገሻ ግን የተባለው ሁሉ ከእውነት የራቀ የሀሰት መረጃ ነው ሲሉ ያስተባብላሉ። እንዲያውም ይላሉ ዶ/ር ዘሪሁን ማዳበሪያው ኣርሶ ኣደሩን ምርታማ ከማድረጉ የተነሳ በራሳቸው ጥያቄ ነው እየወሰዱ ያሉት።
ማዳበሪያው ከመሬቱ ጋር ኣለው ስለተባለው ችግር ከደቡብ ክልል ግብርና ጽ/ቤት የግብርና ኤክስቴንሺን ባለሙያው አቶ መስፍን እንዳለ ምናልባትም ችግሩ ከኣጠቃቀም ጉድለት ሊሆን እንደሚችል ነው የሚገምቱት።
ችግሩ አድማሱን ኣስፍቶ ከወረዳው ኣልፎ በዞን ደረጃ የሚታይ እስከሆነ ድረስ ምናልባት በክልል እና በኣገር ደረጃም ይኖር እንደሆን በሚል ወደ ፌደራሉ የግብርና ሚኒስቴርም ደውለን ነበር። ዶ/ር ዳኛቸው በየነ በግብርና ሚኒስቴር የግብርን ኤክስቴንሺን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው። እንደ ኣጠቃላይ ፖሊሲው በፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ጠቅሰው በኣንድ በተወሰነ ስፍራ የተከሰተ ችግር ካለ በክልሉ በኩል መጣራት ይኖርበታል የሚል እምነት ኣላቸው
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ስር ከሚገኙት 21 ዞኖች ኣንዱ የሆነው የከፋ ዞን ከአፈሩ ለምነት በተጨማሪም ከፍተኛ መጠን ያለው የቡና ምርት የሚገኝበት በመሆኑ ጭምር ይታወቃል።
ባሳለፍነው የምርት ዓመት ብቻ፣ በመዓከላዊው የስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃዎች መሰረት፣ ከዞኑ 10,352 ቶን ቡና ለገበያ የቀረበ ሲሆን ይህም የክልሉን የቡና ምርት 10,3 በመቶ እና በኣገር ደረጃም የኢትዮጵያን ዓመታዊ የቡና ምርት 4,6 በመቶ መሆኑ ነው።
No comments:
Post a Comment